
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዒድ አልፈጥር የረመዳን ወር ፆም መፍቻ በዓል ነው፡፡ ዘንድሮ የዒድ አልፈጥር በዓል ለ1443ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡ ለመኾኑ የዒድ አልፈጥር በዓል ሃይማኖታዊ ዕሳቤው ምንድን ነው? እንዴትስ ይከወናል?
በአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የዳዓዋ ዘርፍ ኀላፊው ሸህ አሕመድ ዘይን ያሲንን ጠይቀናል፡፡ ሸህ አሕመድ ዘይን እንደሚሉት በዓሉ የበረከትና የምሥጋና በዓል ነው፡፡
ዒድ አልፈጥር የረመዳን ወር ፆም መፍቻ በዓል ነውና በዚኽ ዕለት ሕዝበ ሙስሊሙ አደባባይ ወጥቶ ወደ መስገጃ ቦታው በመሄድ ለዚኽ ላደረሰው አምላኩ በጸሎትና ስግደት ምሥጋና ያቀርባል፤ ከበረከቱም ይካፈላል ይላሉ፡፡
በዚኽ መሠረትም በኢስላማዊው ሕግ የተደነገጉና በዒድ ዕለት የሚከናወኑ ተግባራትን ያስረዳሉ ሸህ አሕመድ ዘይን፡፡
በዒድ ዋዜማ ሌሊቱን እንዲኹም ወደ ዒድ ሶላት ሲወጣ፣ “አሏሁ አክበር!” በማለት ፈጣሪውን ስሙን ከፍ ማድረግ ኢስላም የደነገገውን ተግባር ተፈጻሚ ያደረጋል፡፡
የዒድ አልፈጥር ሶላት ተሰግዶ ሲያበቃ የተክቢራው (ፈጣሪን የማመስገኛው) ጊዜ ይጠናቀቃል፡፡ ይኽ የሚደረገው፣ አሏህ (ሱ.ወ) ወደ ጾም በመምራት፣ የረመዳንን ወር ጾም ለማጠናቀቅ ስላበቃቸው፣ ለዋለላቸው ጸጋ እርሱን ለማመስገንና ደስታቸውን ለመግለጽ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የሃይማኖታዊ ትእዛዛትን በመፈጸም የሚገኝን በረከት ለመታደል በጋራ ወደ መስገጃ ቦታ በመሄድ ይሰገዳል ብለዋል፡፡
የዒድ ሶላትን በተመለከተ የእስልምና መርህ ሙስሊሞች ከሴቶችና ሕጻናት ጋር በመኾን በአንድነት ወጥተው ሶላት እንዲሰግዱ ያስተምራል፡፡
የመስገጃ ጊዜውም ፀሐይ ወጥታ ከፍ ካለችበት ቅጽበት ጀምሮ ከሰማይ መሐከል እስከምታዘነብልበት ጊዜ ያክል እንደኾነም ሸህ አሕመድ ነግረውናል፡፡
ሸህ አሕመድ እንዳብራሩት አፈጻጸሙም የዒድ ሶላት ኹለት “ረከዓ” ነው፤ ኢማሙ ሲያሰግድ ቁርዓን የሚያነበው ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲኾን ከሶላቱ በኋላም ኹለት “ኹጥባዎችን ” ያደርጋል፡፡
በዒድ ሶላት “አሏሁ አክበር” የሚለውን ቃል በእያንዳንዱ “ረከዓ” መጀመሪያ ላይ ደጋግሞ ማለት ያስፈልጋል፡፡
በመጀመሪያው “ረከዓ” ላይ “ፋቲሓን (ጸሎትን)” ማንበብ ሳይጀምር፣ ከመጀመሪያው የሶላት መግቢያ “ተክቢራ” ሌላ ስድስት ጊዜ “አሏሁ አክበር” ይላል፡፡ በኹለተኛው “ረከዓ” ላይ ደግሞ ከመጨረሻው “ሱጁድ (ስግደት)” ሲነሳና ሲቆም ከሚለው ተክቢራ ሌላ አምስት ጊዜ ‹‹አሏሁ አክበር›› ይባላል፡፡
የጾም ፍች ምጽዋት (ዘካተል ፊጥር) ሌላው ተግባር ነው፤ የቤተሰብ ጉብኝት እንደማለት ነው ይሉታል ሸህ አሕመድ፤ አሏህ (ሱ.ወ) በዒድ ዕለት ቀንና ሌሊቱን ከሚበላው የሚተርፍ ነገር ያለው ሰው ከሚመገበው ለሙስሊም ችግረኞች እንዲሰጥ ግዴታ ጥሎበታል ይላሉ፡፡
ሸህ አሕመድ የዒድ አልፈጥር በዓል ሲከበር ከዒድ ሶላት በፊት ግዴታ የኾውን ዘካ በማውጣት (በመስጠት) ለሚገባቸው በመስጠት ይገባል ብለዋል፡፡
ከዒድ ሶላት በኋላም የተቸገሩትን በማብላት እና በማጠጣት እንዲኹም ለሀገር ሰላም ዱዓ (ጸሎት) በማድረግ እንደሚከበር ነው ሸህ አሕመድ የተናገሩት፡፡ ይኽም ማንም በዒድ ዕለት ተቸግረው እንዳይውሉ ያደርጋቸዋል፤ በሚል ታስቦ በሃይማኖታዊ ትእዛዙ መሠረት የሚተገበር ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡
የዒድ አል ፈጥርን በዓል ስናከብር በረከቱን ለማግኘትም ኾነ ለፈጣሪም ምሥጋና ስናደርስ ሃይማኖታዊ ትእዛዛትን በመፈጸም መኾን አለበት ነው ያሉት ሸህ አሕመድ፡፡
መረዳዳት፣ ችግረኞችን መጎብኘት መዘንጋት የለበትም፤ ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የመልካም በዓል ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/