
ሚያዝያ 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግርማ የሽጥላ ለመላው እስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለ1443ኛው ሂጅራ የዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ግርማ የሽጥላ ያስተላለፉት መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-
“የምናውቀውና የምንተማመንበት ነገር ቢኖር በብሔር ፅንፈኝነት ካባ መጥተው እንደተሸነፉት ኹሉ፤ አሁንም ፅንፈኞች የመዘዙትን የግጭት አጀንዳ በወንድማማችነት ስሜት እንደምናሸንፋቸው እነሱም ያውቁታል፤ እኛም ቀድመን እናውቀዋለን”
የረመዳን ወር ታላቅ ወር ነው፡፡ የረመዳን ወር በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ከሌሎች ወሮች በተለዩ እጅጉን የሚወደድ የቁርዓን፣ የሶላት፣ የአዝካር፣ የሰደቃ፣ የዱዓ እና መልካም ተግባራት የሚፈፀሙበት ወር ነው። የዚህ ቅዱስ ወር ፍጻሜ ማብሰሪያ በኾነችው ኢድ አልፈጥር ወይም የረመዳን ፍቺ በእስልምና የዘመን አቆጣጠር “ሒጅራ” መሠረት የወርኃ ሻዕባን ፍፃሜ የመጀመሪያዋን ቀን ይከበራል፡፡ ኢድ አልፈጥር በዓል የፆም ፍቺ እና ለዐቅመ ደካሞች የሚደረግ እዝነትን አስተሳስሮ የያዘ ልዩ በዓል ነው፡፡
በቅዱሱ ረመዳን ወር መጨረሻ እና በሸዋል ወር የመጀመሪያ ቀን ላይ የሚለውን የጾም ወር ማጠናቀቂያ ታላቅ በዓል የኾነውን ኢድ አልፈጥር ሲከበር ዕለቱን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተሰባስበን በአንድነት የምናከብረው በዓል ነው፡፡ የቀደሙት ሀገራዊ እሴቶቻችን ጎልተው እንዲወጡ የምንሠራበትና የበግ ለምድ በመልበስ ተመሳስለው በውስጣዊ አንድነታችን ላይ አደጋ ሊጋርጡብን የሚሠሩትን ኀይሎች የምናሳፍርበት ዕለትም እንዲኾን መሥራት ይኖርብናል፡፡
ለመላው ዓለም ተምሳሌት በመኾን የምንታወቅበት የሃይማኖት፣ የቋንቋና የባህል ቱባ እሴቶች የመቻቻላችን እንጂ የተቃርኖ መነሻ ሊኾኑን አይችሉም ፤ አይገባምም፡፡ ኾነውብንም አያውቁም፡፡ ነገር ግን ብሔርን ካባ አድርገው እርስ በርስ ሊያባሉን የነበሩ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶቻችን ይህ አልሳካ ሲላቸውና ሲሸነፉ በሃይማኖት ፅንፈኝነት ለመታየት ጭምብላቸውን እያወለቁ ነው፡፡
በዒድ አልፈጥር በዓል ስግደት ከመስጂድ ወጥቶ በአደባባይ በሕብረትና በአንድነት እንደሚካሄድ ኹሉ ቀኑ ለሰላም፣ ለትብብር፣ ለአንድነት፣ ለሕብረት፣ ለመከባበር እና ለመተሳሰብ በአንድነት እንደምንቆም ለቀሪው ዓለም በገሃድ የምናስተምርበት ዕለት እንዲኾንም ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
በተያያዘም በረመዳን ልዩ ወር መጨረሻ አከባቢ ጎንደር ከተማ በቀብር ስፍራ በተፈጠረው ግጭት የተነሳ ክቡር የኾነው የሰው ህይወት በመጥፋቱ፣ የአካል ጉዳት በመድረሱና ንብረት በመውደሙ ኹላችንንም ያሳዘነ ጉዳይ ነው፡፡ በማንም ይኹን በምንም ኹኔታ ይፈፀም ድርጊቱ አሳዛኝ ብቻ ሳይኾን አሳፋሪም ነው፡፡ የኹለቱንም ዕምነቶች የማይወክልና ተቀባይነት የሌለው ከመኾኑም ባሻገር ባለቤቶቹ በግጭቱ ጥገኛ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚሠሩት ፅንፈኛ ኀይሎች ብቻ መኾናቸውን መገንዘብ ይገባል፡፡
አጥፊዎችን በሕግ ለመጠየቅ የኹለቱም የእምነት ተከታዮች ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ክልላችንና ሀገራችን ሰላም ይኾኑ ዘንድ ፅንፈኛን ማጋለጥ፣ ማዳከምና ማጥፋት የኹሉም ስልጡን ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡ ጥፋተኛን በሕግ እንዲዳኝ ለማድረግ የሚሠራው የማኅበረሰብ ትብብርም ሊቀጥል ይገባዋል፡፡
ከዚህ በፊት የነበረው ወንድማማችነት የበለጠ እንዲጠናከር የክርስትና ዕምነት ተከታዮች ይህን በዓል ስናከብር የነበረውን እሴት ተላብሰን የምናከብረውና አንድነታችንን የምናፀናበት እንዲኾን የተለመደውን ወንድማዊ ተግባር በመፈፀም ታሪካዊ አደራችሁን ትወጡ ዘንድ ወንድማዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የምናውቀውና የምንተማመንበት ነገር ቢኖር በብሔር ፅንፈኝነት ካባ መጥተው እንደተሸነፉት ኹሉ፤ አሁንም ፅንፈኞች የመዘዙትን የግጭት አጀንዳ በወንድማማችነት ስሜት እንደምናሸንፋቸው እነሱም ያውቁታል፤ እኛም ቀድመን እናውቀዋለን፡፡
በድጋሚ መልካም በዓል እንዲኾንላችሁ ከልብ እመኛለሁ።
ዒድ ሙባረክ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/