
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 6/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኮምቦልቻ ከተማ በሚገኘው የቦርከና ወንዝ ድልድይ ላይ ያለው ከፍተኛ የተሽከርካሪዎች ፍሰት ለእንግልትና ለስጋት እንደዳረጋቸው ተገልጋዮች ተናገሩ፡፡
ኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ከተማ ከመሆኗ ባለፈ የሀገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች መተላለፊያ መሆኗን ተከትሎ በከተማዋ የተሽከርካሪዎች ፍሰት ጨምሯል፡፡ ጠባብ መንገዷ እና በከተማዋ ያለው አንድ ድልድይ ከትራፊክ ፍሰቱ ጋር አለመመጣጠን ደግሞ በተለይ በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓታት ነዋሪዎችን እና አሽከርካሪዎችን እያጉላላ ነው፡፡ አሽከርካሪዎች ለአብመድ እንደተናገሩትም እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው ሰዓታት ቦርከናን ለመሻገር እስከ አንድ ሰዓት ይቆማሉ።
አብመድ ከስፍራው ተገኝቶ እንደተመለከተውም የከተማዋ መንገድ ጠባብና አካፋይ የሌለው ከመሆኑ ባሻገር በከተማዋ መሃል ላይ የሚገኘው የቦርከና ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ አንድ ብቻ መሆኑም ለእንቅስቃሴ ችግር ፈጥሯል፡፡ የትራፊክ ፍሰቱ ከፍተኛ ስለሆነ ፊት ለፊት የሚመጣ ተሽከርካሪ ቦታ እስኪለቅ ድረስ ከባድ ተሽከርካሪዎች ጭምር በድልድዩ ላይ ቆመው ይቆያሉ። ይህ ደግሞ የድልድዩን ዕድሜ ያሳጥረዋል፡፡
የቦርከና ድልድይ በ1928 እስከ 1933 ዓ.ም በነበረው የጣሊያን ወረራ ወቅት የተሰራ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ድልድዩ የሚያገናኘው ከቦርከና ማዶ ለማዶ የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎችን ብቻ አይደለም፤ ከአዲስ አበባ-ደሴ-ወልዲያ- ትግራይ መተላለፊያም ነው፡፡ ድልድዩ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ከመስጠቱ የተነሳ ስንጥቅ እየተፈጠረበት እንደሆነም ታዝበናል፡፡ የከተማዋ ብቸኛ መተላለፊያ በመሆኑ ጉዳት ከደረሰበት የከተማዋ ነዋሪዎች አይገናኙም፤ ከተማዋን እንደመተላለፊያነት በመጠቀም ከአዲስ አበባ-ደሴ-ትግራይ የሚደረገው ጉዞም ይቋረጣል።
የትራፊክ ፍሰቱን ሲቆጣጠሩ ያገኘናቸው በከተማ አስተዳደሩ የመንገድ ትራፊክ ማረጋገጫ ዋና የስራ ሂደት ሽፍት ኃላፊና ሞተረኛ ትራፊክ ዋና ሳጅን ኤፍሬም ቅጣው የመንገዱ ጥበት እና ድልድዩ አንድ ብቻ መሆን ለሥራቸው ፈታኝ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ “መንገዱ አካፋይ ካልተሰራለት የትራፊክ ጫናውን መቀነስ አይቻልም” ያሉት ዋና ሳጅን ኤፍሬም ተጨማሪ ድልድዮችንና የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳድር የመንገድ ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ቡድን መሪ አቶ ግርማ ከበደ በከተማዋ 1 ሺህ 770 የሚደርሱ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) እና ታክሲዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህንና ሌሎች ከባድ ተሽከርካሪዎችን የሚመጥን መንገድ ለመስራት በዝግጅት ላይ እንደሆኑም ነው የገለጹት፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር አህመድ የሱፍ የመንገዱና የድልድዩ ችግር የከተማዋ ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ ጥያቄ እንደሆነ ተናገረዋል፡፡
ቦርከናን የሚያሻግሩ ድልድዮችን ለመስራት በጥናት ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል። አንደኛው ድልድይ በከተማዋ ቀበሌ 01 በሚባለው አካባቢ እንደሚገነባና ይህም የነባሩን ድልድይ ጫና እንደሚቀንስ ነው ምክትል ከንቲባው የተናገሩት፡፡ ሁለተኛውን ድልድይ ደግሞ በደሴ መግቢያ ወይም በኢንዱስትሪ መንደሩ አካባቢ ለመስራት እንደታቀደ ነው የተገለጸው፡፡
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ