“ሙሽሪት ጎንደር ወደ ሙሽርነቷ ተመልሳለች”

539

ጎንደር: ሚያዝያ 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሚያምርባት መሞሸር፣ መዋብ፣ ማማር፣ መከበር፣ ዙፋኗን ማሳመር ነው። የሰላም እናት ሰላም ትወልዳለች፣ የፍቅር እናት ፍቅርን ትሰጣለች፣ የአንድነት እናት አንድነትን ታመጣለች፣ የክብር እናት ክብርን ታጎናጽፋለች።

የአሸናፊዎች እናት ድልን ታበስራለች። ፍቅር የምትወልድ፣ ሰላምን የምታሳድግ እናት ጥል አይስማማትም፣ መከፋት አይኾናትም፣ አይመጥናትምም።

ጃንተከል እያለ ማረፊያው፣ የሽማግሌ መቀመጫው፣ ቤተመንግሥቱ እያለ ብልኾቹ የነገሡበት፣ እምዬ ኢትዮጵያን በትህትና ያስተዳደሩበት፣ በፍቅር የመሩበት፣ የተበደለን ያስካሱበት፣ የበደለን እንዲክስ ያደረጉበት፣ ጥፋተኛን የቀጡበት፣ ደግ አድራጊን የሸለሙበት፣ ጀግናና ብልህን የሾሙበት፣ ሹመት የማይገባውን የሻሩበት፣ ግብር ያበሉበት፣ ደስታ ያሳዩበት፣ ዓለም የታየበት፣ እልፍኙ እያለ መኳንንቱ የተቀመጡበት፣ መሳፍንቱ የመከሩበት፣ ችሎቱ እያለ የተበደሉ አቤት ያሉበት፣ ነገሥታቱ ፍርድ የሰጡበት፣ ኹሉንም በእኩል ዓይን ያዩበት፣ የቤተ መንግሥቱ ዙሪያ ገባ ሳለ የጦር አበጋዞች በተጠንቀቅ የቆሙበት፣ ለሕዝብ ክብር፣ ለሠንደቅ ፍቅር ራሳቸውን የሰጡበት፣ ትጥቃቸውን አጥበቀው የኖሩበት። ስለ አንድነት የመከሩበት፣ ሀገር እንድትፀና ቃል የተጋቡበት፣ የማይፈታ የሀገር ውል ያሠሩበት።

ቤተ መቅደሱ እያለ ለምድር ሰላም የሚጸልዩ አበው ያሉበት፣ ፍትሕ አዋቂዎች የመሉበት፣ ምስጢራትን የመረመሩ ሊቃውንት የሚኖሩበት፣ መስጅዱ እያለ አዛን እየተባለ ሰላም የሚለመንበት፣ ሰውና ፈጣሪ የሚታረቅበት፣ ኹሉ ያላት አንዳችም ነገር ያልጎደላት እመቤት በየት በኩል ትጎድላለች? እንዴት ኾናስ ሰላም ታጣለች? በነበረው ጥበቧ፣ ዘመናትን በተሻገረው ባሕሏ ጠላትን አሳፍራ፣ ቀዬዋን አስከብራ ሰላሟን ትጠብቃለች፣ ጠላቶቿንም ትቀጣለች እንጂ። ኹሉም ያላት ኹሉንም መልካም ታደርጋለች።

የሀገር መሠረት፣ የፍቅር እናት፣ የአንድነት እመቤት፣ የታሪክ ማኅደር ፣ የጀግኖች ሀገር፣ ሥርዐት የሚጸናባት፣ ፍትሕ የሚሰጥባት፣ አንድነት የገነነባት፣ አይደፈሬነት ያየለባት፣ አርቆ አሳቢነት ከፍ ያደረጋት ጠላቶቿ በሚመኙላት ሳይኾን እርሷን በሚመጥናት ትኖራለች። ዝቅ ማለትን ሲመኙላት ከፍ ትላለች፣ መሸነፍን ሲመኙላት በድል አድራጊነት ትገሰግሳለች፣ በክብርና በዝና ትራመዳለች።

የሀገር መሠረት በሚያልፍ ወጀብ አይነቃነቅም፣ የሀገር ዋልታ በጠላት እጅ ተገፍቶ አይወድቅም፣ ዋልታና ማገር ደግፎ ያፀናል ሳያናውፅ አፅንቶ ያኖራል እንጂ ሸብረክ አይልም። ከቤተ መንግሥቱ ብልሃት እየመዘዘች፣ ከሽማግሌዎቿ ምክር እየተቀበለች፣ ከሃይማኖት አባቶች ተገሳፅን እየሰማች፣ በጀግኖቿ እየተጠበቀች፣ በብልሃቶቿ መሰናክሉን እየጠራረገች፣ መንገዷን እያቀናች፣ ፈተናዎቿን በድል እየተወጣች በሚመጥናት ጎዳና፣ በሚገባት ሠረገላ፣ በተዋበው ዙፋን ተቀምጣ፣ ከፍ ብላ ወደ ምትቀመጥበት ሰገነት ትገሰግሳለች። ሰገነቱ ለክብሯ የሚመጥናት፣ ታላቅነቷን የሚያጎላላት፣ ከፍታዋን የሚመሰክርላት ነው።

በነጫጭ እርግቦች እየተመራች፣ በማይዝሉ ልጆቿ እየተጠበቀች በሚገባት የሰላም ጎዳና፣ የክብር መንገድ ቄጤማ እያስነሰነሰች፣ ስጋጃ እያስነጠፈች፣ በመልካም ሽቱ እየተዋበች ትጓዛለች። ለክብሯ የሚመጥን፣ ለዝናዋ የሚኾን ይሄው ነውና።

ሰላም የወለደችውን፣ ፍቅር ያሳደገችውን እምዬ ጎንደርን ቀን ጥሏት ችግር ገጥሟት ጠላቶች የተሰቀለ ከበሯቸውን አውጥተው፣ የተቀመጠ ማሲንቋቸውን አንስተው ደለቁ፣ ሰርግና ምላሽ ኾነ እያሉ ቀያቸውን በደስታ አሞቁ። የሀገር መሠረት፣ የአንድነት ምልክት፣ የኢትዮጵያዊነት እናት ችግር ሲገጥማት አይዞሽ ልትባል ሲገባት፣ በሐዘኗ የሚደልቁት፣ ድግስ ደግሰው፣ ድንኳን ጥለው፣ ባልንጀራ ጠርተው የሚደሰቱት በረከቱ።

ከባሕር ማዶ ኾነው መከፋቷን የሚመኙት በደስታ ቦረቁ፣ በሐሴት ደመቁ። ክብሯ የሚገባቸው የሚወዷት፣ ሰላሟን የሚመኙላት ደግሞ ችግሯን እንድታልፍ ተረባረቡለት፣ መልካሙን ኹሉ ተመኙላት፣ አደረጉላት።

የነገሥታቱ ሀገር ጥበብ ያላት፣ እሴት የመላባት፣ ታሪክ ከፍ ብሎ የተቀረፀባት፣ ባሕል የካበተባት ጎንደር በቀደመው ጥበቧ የጠላቶቿን የሰርግ ድንኳን አስነቀለች፣ የሚደልቁትን ከበሮ አስተወች፣ የጠላቶቿን ደስታ በጥበቧ ነጠቀች። ጎንደር በራሷ ሠርግ ትደሰታለች፣ በጎረቤት ተዝካር ታዝናለች እንጂ ምቀኝነት የለባትም። ለምቀኞችም ቦታ የላትም። ሰላሟን መልሳ የጠላቶቿን ፈንጠዝያ ባዶ አደረገችው፣ ጠላቶቿ ሊሞቁት የነበረውን እሳት በጥበቧ አጠፋችው፣ ከሀገር ውስጥ እስከ ባሕር ማዶ ነገር ሲያጋንን የነበረውን ፣ በችግሯ ጮቤ የረገጠውን ጉድ ሠራችው።

የንግሥና ሥርዐት ሳይቸግረኝ፣ የማይናወፅ አንድነት እያለኝ፣ የፍቅር ካባ ሞልቶልኝ፣ የመፍረጃ ዙፋን በርክቶልኝ፣ የሽማግሌዎች መቀመጫ ጃንተከል ዋርካ እያለልኝ አዝኜ የምቀር፣ አንገቴን በሀፍረት የማቀረቅር ይመስላችኋል ወይ? አለቻቸው። ጥበብ ሳይቸግረኝ፣ ፍቅር ሳያጥረኝ፣ አንድነት ሳይርቀኝ በቤቴ ውስጥ ሐዘን ውሎ አያድርም ብላ አሳፈረቻቸው።

እነኾ ሙሽሪት ጎንደር ወደ ሙሽረነቷ ተመልሳለች። ወደ ሰላሟ ተመልሳለች። በማለዳ ተነስተን የጎንደርን ከተማ ቃኝተናቸዋል፤ ተመላልሰንባቸዋል። ከነዋሪዎቹ ጋርም ተገናኝተን ስለ ሰላሟ አውግተናል።

ስማቸውን ያልነገሩን እናት ጎንደር ሰላም ናት፣ ፍቅር ላይ ናት። ፍቅር ወርዷል፣ ጎንደር ሰላም አይደለም እያሉ የሚያራግቡ ሰዎች ልቦና ይስጣቸው ጎንደራችን ሰላም ናት ብለውናል። አብረን የምንኖር ሰዎች፣ አብረን በልተን ጠጥተን የኖርን፣ ምንም የሚለየን ነገር የለም። ወደፊትም አብረን ነን ነው ያሉን።

ተስፋለም ብርሃን የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ አሁን ሰላም ነው፣ ወንድማማቾች ነን፣ በፍቅር ነው የምንኖረው ነው ያሉን። ተፈጥሮ የነበረው ችግር ማንንም የማይመጥን ነበርም ብለውናል። ጎንደር ላይ ሰላም እንደሌለ የሚያናፍሱ አካላት ይታቀቡልን፣ ለዘመናት አብረን ነው የኖርነው አሁንም በፍቅር እየኖርን ነው፣ አብሮ የመኖራችን ምስጢር አሁን የተጀመረ ሳይኾን ዘመናትን የተሻገረ ነው ብለውናል።

ሐጂ ጣሂር አማን አደም በፍቅር የምንኖር፣ በመካከላችን ልዩነት የለም ነው ያሉት። አንድነታችን እንጂ ልዩነታችን አናውቀውም ብለውናል። ጎንደር ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ተመልሳለች፣ ልጆቻችን በጋራ ነው የምናሳድገው፣ ከሰሞኑ የታየውን ጉዳይ ድጋሜ እንዳይከሰት መንግሥት በትኩረት መሥራት አለበት ብለዋል ሐጂ። ከሰሞኑ ተከስቶ የነበረው ችግር አስደንጋጭ እንደነበርና ማንንም እንደማይወክል ነው የተናገሩት።

ስማቸውን ያልነገሩን ሌላ አባት ጎንደር የኹሉም ሀገር ናት ነው ያሉን። አጥፊዎችን በትብብር ማጥፋት እና በአብሮነታችን መቀጠል ይገባናልም ብለውናል።

መንግሥት ሰላም የማምጣት ሚናውን መወጣት አለበት፣ በውይይት ኹሉንም እንፈተዋለንም ነው ያሉን። ጎንደር ሰላም በመኾኗ ደስ ብሎናል ብለዋል።

ሌላኛው የጎንደር ነዋሪ አብርሃም ይብር ከተማዋ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ናት ነው ያለን። የክፉዎች ሴራና ሥራ መክኗልም ብሏል።

ነዋሪዎቹ ሰላም መኾናችንን እናብሥራችሁ ብለውናል።

በማለዳ ተነስተን በጥንታዊቷ ከተማ ጎዳናዎች በሰላም እየተመላለስን፣ የጎንደርን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልክተናል። የጎንደር ነዋሪዎች በጎዳናዎቹ በሰላም እየተንቀሳቀሱ ነው። መደበኛ ሥራቸውንም እየከወኑ ነው።

“ይዜምልሻል ይቀኙልሻል፣
ኹሌም አዲስ ነሽ ጎንደር ይሉሻል” እንዳለች ባለዜማዋ ጎንደር ኹሌም አዲስ ናት፣ ጎንደር ኹሌም ልዩ ናት፣ የታሪክ ማማ ናት።

“ኧረ ገዳሙ ኧረ ገዳሙ
አይደበዝዝም ጎንደር ቀለሙ” እንደተባለ የጎንደር ቀለም አይደበዝዝም። እንደደመቀ እንደረቀቀ ይኖራል እንጂ።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ -ከጎንደር

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሽህ 443ኛ የኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ” የአማራ ክልል መንግሥት
Next article“ዒድ አልፈጥር በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተሰባስበን በአንድነት የምናከብረው ታላቅ በዓል ነው” አቶ ግርማ የሽጥላ