“የኢድ-አልፈጥር በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መጠናቀቁን የፌዴራል ፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኀይል አስታወቀ።

191

አዲስ አበባ ፡ ሚያዝያ 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል ፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኀይል የኢድ-አልፈጥር በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል።

ግብረ ኀይሉ የሰጠው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ለእስልምና ዕምነት ተከታዮች እንኳን ለኢድ-አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ እያለ የመልካም ምኞት መልዕክቱን ያስተላልፋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፈው ሳምንት ተከብሮ ያለፈው የፋሲካ በዓል እና በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ የተዘጋጀው ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሃ ግብር በሰላማዊ መንገድ ተካሂደው በሰላም ተጠናቋል።

በመሆኑም ከጥምር የፀጥታ አካላት የተሰጠውን መመሪያ ከግምት ውስጥ በማስገባት አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ላደረጋችሁ የሁሉም ሃይማኖት አባቶች፣ በዓሉን በኮሚቴነት ያስተባበራችሁና የመራችሁ አካላት፣ ምዕመናኑን በማስተናገድ ከፍተኛ ድርሻ የተወጣችሁ ወጣቶችና ሰላም ወዳዱ የሀገራችን ህዝብ እንዲሁም በዓላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ የራሳችሁን ድርሻ ላበረከታችሁ የፌዴራልና የክልል የፀጥታና ደኅንነት ኀይሎች በሙሉ የፌደራል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኀይል ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል።

ልክ እንደ ፋሲካ በዓል እና የኢፍጣር መርሃ ግብር ሁሉ የኢድ-አልፈጥር በዓልም በተመሳሳይ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ ግብረ ኃይሉ ዝግጅቱን አጠናቆ ተልዕኮውን በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች በቁርጠኝነት እየተወጣ ይገኛል።

ይሁን እንጂ መንግሥት ለበዓላቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ባለበት በዚህ ወቅት ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ አንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ህዝቡን ለማሳሳትና የእምነቶቹ ወግና ሥርዓት ከሚፈቅደው ውጪ ምዕመናኑን ወደ ግጭት ለማስገባት እንቅስቃሴ እያደረጉ እንዳሉ የጋራ ግብረ ኀይሉ ደርሶበታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ከቀብር ቦታ ጋር በተያያዘ በተወሰኑ የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ግጭት የተቀሰቀሰ ቢኾንም ግጭቱን በሃይማኖት ሽፋን ለማባባስ የሚደረገው ጥረት እኩይ ዓላማ ላላቸው ፀረ-ሰላም ኀይሎች ዕድል ስለሚፈጥር ሁሉም የሀይማኖት ተቋማት ይህንን ተገንዝባችሁ አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ እየተሠራ ያለውን ተግባር ማገዝ ይጠበቅባችኋል ።

በተመሳሳይ በስልጤ ዞን በወራቤ ከተማ ግጭቱን ለማባባስ በተናበበ በሚመስል አኳኋን በቤተ እምነት ላይ የደረሰው ቃጠሎ እና በክቡር የሰው ልጅ ህይወት ላይ የደረሰው ሞት የክርስትናንም ሆነ የእስልምናን እምነቶች የማይወክል ተግባር ነው።

በዚህ አጋጣሚ በጎንደርና በወራቤ ከተሞች በጠፋው ክቡር የሰው ልጅ ህይወት እና በእምነት ተቋማቱ ላይ በደረሰው ውድመት የጋራ ግብረ ኀይሉ የተሰማውን ልባዊ ሀዘን ይገልፃል።

ከዚሁ ሁከትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ ከሁለቱም ወገን በድርጊቱ ውስጥ የተሳተፉ እንዲሁም ከጀርባ ሆነው ግጭቱ እንዲባባስና ወደ ሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች እንዲዛመት ሲቀሰቅሱና ሲያነሳሱ የነበሩትን ፀረ-ሰላም ኀይሎችን የጋራ ግብረ ኀይሉ እያደነ ለሕግ ማቅረቡን እንደቀጠለ ይገኛል። የጋራ ግብረ ኀይሉ በዚህ ዙሪያ በቀጣይ ሰፊ መግለጫ ይሰጥበታል።

በየትኛውም እምነት ውስጥ ተደብቀው እምነቱ ከሚፈቅደው ውጭ የተለያዩ ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቡድኖችንና ግለሰቦችን ሕዝቡ ከውስጡ አውጥቶ በማጋለጥ ለፀጥታ አካላት አሳልፎ በመስጠት የተለመደውን ቀና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልና ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ የጋራ ግብረ ኀይሉ ጥሪውን ያቀርባል።

የሕዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ የፀረ-ሰላም ቡድኖችና ግለሰቦች ከዚህ እኩይ ድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ የፌደራል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኀይሉ የጀመረውን ህግ የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያረጋግጣል።

በድጋሜ እንኳን ለዒድ አል-ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ።

በዓሉ የሰላም፣ የጤና እና የፍቅር እንዲሆንላችሁ የጋራ ግብረ ኀይሉ ከልብ ይመኛል።
ዒድ-ሙባረክ !

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።
Next articleተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ የ1443ኛውን የኢድ- አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ለሕዝበ ሙስሊሙ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡