በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

156

አዲስ አበባ ፡ ሚያዝያ 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቀዋል።

አቶ ደመቀ ይህን ያሉት በቅርቡ አዲስ ከተሾሙት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላዉድ ጂቢዳር ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው።

አቶ ደመቀ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተሻሉ ሥራዎችን ማከናወኑን ለዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ያሉት አቶ ደመቀ፤ እንደ ዓለም ምግብ ፕሮግራም ያሉ ድርጅቶች ደግሞ ሁሉን አቀፍ ተደራሽ የኾነ ሰብአዊ እርዳታ በማድረግ የተጠናከረ ድጋፍ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን ነው ያሉት።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአማራ እና በአፋር ክልልሎች እንዲሁም ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

አቶ ደመቀ መንግሥት ያልተገደብ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግ ያሳለፈውን ውሳኔ በማክበር የተሻለ ድጋፍ እንዲደረግ እየሰራ መሆኑን አንስተው፣ የህወሓት ቡድን ግን አሁንም ሰብዓዊ እርዳታውን ለማስተጓጎል እየሞከረ ነው ብለዋል። ዓለም አቀፍ ለጋሽ አካላትም የቡድኑን አካሄድ ማውገዝ አለባቸው ነው ያሉት።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላዉድ ጂቢዳር በበኩላቸው የመንግሥትን ቁርጠኝነት በማድነቅ በቀጣይም አብሮ ለመሥራት በሙሉ ቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ከችግር ውስጥ ወጥቶ ወደ ተሻለ መንገድ እና እድገት መስመር መግባት ከራሷም በላይ ለሌሎች ሀገራትም ትልቅ ሚና ስላለው ከመንግሥት ጎን ኾነን ችግሩን ለማለፍ እንሰራለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የውስጥ መፈናቀል ካጋጠማቸው ዜጎቿ በተጨማሪ ከ9መቶ ሺህ በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች መሆኗን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።

የምግብ አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ኢትዮጵያ ስንዴን በከፍተኛ መጠን የማምረት አቅም ያላት ሀገር በመሆኗ ለዚህ ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፍ በድርቅ ወደ ተጎዱ አካባቢዎችም እንደሚያስፋፋ ተናግረዋል።

መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“የከፍታ ማማ ላይ ወጥተው የምናያቸው ሀገራት የከፍታቸው መነሻ ለኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ የሰጡት ከፍተኛ ትኩረት ነው” የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Next article“የኢድ-አልፈጥር በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መጠናቀቁን የፌዴራል ፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኀይል አስታወቀ።