
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የዘር መነሻ፣ የዓለም መዳረሻ፣ የስልጣኔ እመቤት፣ የሁሉም ንግሥት፣ የቅዱሳን እርስት፣ የጀግኖች እናት፣ ቀዳማዊት፣ ለምስክር የተቀመጠች፣ በኃይል የተከበረች፣ በእሳት የታጠረች፣ ከዘመን ዘመን በጽናት የተጓዘች፣ በማዕበል መብዛት፣ በውሽንፍር መበርከት ያልተናወጸች የጽናት ተምሳሌት፡፡ የገፏትን ጥላለች፣ የደፈሯትን ሰባብራለች፣ አንገቷን ሊያስደፏት የከጀሉትን አንገታቸውን አስደፍታለች፣ ቅስማቸውን ሠብራለች፣ ጦር ያዘመቱባትን ጦር አዝምታ ቀጥታ መልሳለች፡፡ ጦረኝነት ከእርሷ በላይ ላሳር መሆኑን አሳይታለች።
ጀግንነት አስከብሯታል፣ ጽናት ልዩ አድርጎ አኑሯታል፣ አንድነት ጠላቶቿን ከእግሯ ሥር እንዲኖሩ አድርጎላታል፡፡ ተሻግራ የሌላን ወሰን አትደፍርም፣ አሻግራም ወሰኗን አታስደፍርም፡፡ ለግፍ ትዘምታለች እንጂ በግፍ አትዘምትም። ለፍትሕ ትቆማለች፣ ለፍትሕ ትደማለች፣ ለእውነት ትደክማለች፣ አድሎዓዊነትን ከምድር ላይ ለማጥፋት ትጥራለች፡፡ እኩልነትን በምድር ላይ ለማስፈን ትታትራለች። በውስጧ የታቀፈቻቸውን ምስጢራት፣ የያዘቻቸውን ጥበባት የሚሹ ሁሉ በቀንና በማታ ፈልገዋታል፡፡ እርሷ ግን አታሳይም።
የት ነው ያለሽ? የትስ ትገኛለሽ? ሲሉ እግራቸው እስኪነቃ ድረስ ተጉዘዋል። ባሕር እየከፈሉ፣ የብስ እያቋረጡ፣ በረሃውን እየተጓዙ ኃያልነቷን ለማየት ታትረዋል፡፡ የዓለም የጥበብ ብርሃን የሚበራባት፣ የጨለማ በርኖስ የሚገፈፉባት፣ ፍትሕ የሚሰበክባት፣ ደግነት የመላባት ሀገር ሲሉ ይፈልጓታል፡፡ ብዙዎች ጥበቧን፣ ቀዳሚነቷን፣ ምስጢራዊነቷን፣ ረቂቅነቷን ያደንቁላታል፣ አይተውም በዓለም አደባባይ ይመሰክሩላታል፡፡ ሌሎች ያላትን ሁሉ ወስደው የእነርሱ ማድረግ ይመኛሉ፣ ያን ለማድረግም ይፍጨረጨራሉ፡፡
ከወንዛቸው ከግዮን የረዘመ፣ ኃያላን ነን ከሚሉት ሀገራት የቀደመ፣ በጽኑ መሠረት ላይ የቆመ፣ ዓለማትን ያስደነቀ፣ በፍጹም ጥበብ የረቀቀ፣ በማያረጁ ድርሳናት፣ በማይደበዝዙ ቀለማት የደመቀ ታሪክ አላቸውና ይቀኑባቸዋል፡፡ ታሪካቸውን ለማሳነስ፣ ክብራቸውን ለመቀነስ ቢጥሩም ላይቀንስ፣ ላያንስ ኾኖ ተሰርቷልና አልሆን አላቸው፡፡ የሂሳብ ቀመራት ምስጢሯን አይፈቷትም። የዓለማት ማሰሻዎች መርምረው አይደርሱባትም መኩሪያዋን ኢትዮጵያን።
ኢትዮጵያ አውቀናታል ሲሏት ያልታወቀች፣ ዳስሰናታል ሲሏት ያልተዳሰሰች፣ ምስጢሯን ፈትተናታል ሲሏት ያልተፈታች፣ ደርሰንባታል ሲሏት እጅግ የራቀች፣ ረቂቁን ለይተነዋል ሲሏት የበለጠ የረቀቀች ናት። ኢትዮጵያዊነት ይሉት ብርቱ አጥር የከለላት፣ ኢትዮጵያዊነት ይሉት ብርቱ ዙፋን ያከበራት፣ ኢትዮጵያዊነት ይሉት የማያረጅ ካባ ያስዋባት፣ ኢትዮጵያዊነት ይሉት ኃያል ክንድ ያስከበራት፣ ጠላቶቿን የረጋገጠላት፣ ኢትዮጵያዊነት ይሉት ብርቱ መንፈስ የዘመቱባትን ሁሉ አሸንፎ የመለሰላት፣ ኢትዮጵያዊነት ይሉት ብርቱ መንፈስ ለጥቁር ዘር መኩሪያ ያደረጋት፣ ከድል ላይ ድል እየጨመረች፣ ከታሪክ ላይ ታሪክ እየደራረበች፣ ከጠላቶቿ ልቃ እየወጣች፣ የተጠመደላትን ወጥመድ እየበጣጠሰች እንድትኖር አድርጓታል።
ጥቁሮች ይመኩባታል፣ የተስፋቸው ጀምበር የጨለመባቸው ተስፋ ያደርጉባታል፣ በጨለማ ውስጥ ያሉት ብርሃን ይሹባታል፣ ፍትሕ ያጡት ፍትሕ ይጠብቁባታል፣ እርሷም ተስፋ ላደረጉት ደርሳላቸዋለች፣ በጨለማ ውስጥ ለነበሩት ብርሃን ሆናላቸዋለች፣ በፍትሕ እጦት ለተሰቃዩት ፍትሕን ሰጥታቸዋለች፣ ኃያላንን ነን ያሉትን አደብ አስገዝታቸዋለች፣
ኢትዮጵያ ከሩቅ ከባሕር ማዶ የሚገነፍል፣ ከምድሯም የሚፈለፈል ባዳ በየዘመናቱ ተነስተውባታል። አንደኛው ላኪ ሌላኛው ተላኪ ሆነው መጥተውባታል። እርሷም በምትመካባቸው ልጆቿ፣ በምታምናቸው ጀግኖቿ ጠላቶቿን እንደአመጣጣቸው መልሳቸዋለች፣ ትመልሳቸዋለችም። ጠላት በሚመጣበት፣ በተነሳበት፣ ኢትዮጵያን ለመውረር በቋመጠበት ንፍቅ ሁሉ እየተጓዙ እንዳልነበር አድርገዋል።
በዓድዋ አናት ላይ በዓለም አደባባይ የተዋረደችው ኢጣሊያ ውርደቷን ልትመልስ፣ ሽንፈቷን ልታካክስ ስትዘጋጅ ከረመች። ዝግጅቷ በቀላሉ የሚጠናቀቅ አልነበረም። ለግማሽ ምዕተ ዓመት የተጠጋ ነበር እንጂ። ያቺ በታሪኳ ሽንፈት የሌለባትን ሀገር በምን መልኩ እናሸንፋት? የአባቶቻችን ታሪክስ እንዴት እናድስ? ክብራችን በምን መንገድ እንመልስ ? የሚለው ጥያቄ ዓመታትን ወስዶባቸዋል። የዝግጅቱና የምክሩ ዘመን አርባ ዓመታትን ወሰደ።
ኢትዮጵያውያንን በጦርነት ብቻ መርታት እንደማይቻል ዓድዋ አስተምሯቸዋል። በጥቁር ምድር በጦርነት የሚረታን፣ የሚቋቋመን የለም ብለው በሮም አደባባይ ያገሱት የኢጣልያ ወታደሮች ዓድዋ ውጧቸዋል፣ የኢትዮጵያውያን አርበኞች ክንድ አድቅቋቸዋል፣ ጎራዴ በልቷቸዋል። እነዚህ ክንዳቸው ነዲድ የሆነውን ኢትዮጵያውያንን ጦርነት ብቻ እንደማያሸንፋቸው ዓድዋ በደንብ አስተማራቸው።
ከጦርነቱ ጎን ለጎን ሕዝብ ከሕዝብ በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በአካባቢ እና በታሪክ ማከፋፈል ትልቁ መሣሪያችን ነው አሉ። አርባ ዓመታቱ ተቆጥረው ጊዜው ደረሰ። የኢጣልያ ሠራዊት ለወረራ ወደ ኢትዮጵያ መጣ። ኢትዮጵያ ከጠላቷ አንፃር የታጠቀችው ዘመናዊ መሣሪያ አልነበራትም። ዳሩ ልበ ሙሉ ጀግኖች አልተለዩዋትም።
በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ አባጠቅል ኃይለ ሥላሴ ተሰይመውበታል። ሀገራቸው ኢትዮጵያ በስልጣኔ ታብብ ዘንድ መታተር ጀምረዋል። አስቀድሞ በአልጋ ወራሽነት ቀጥሎም በንጉሥነት ልምድ ያካበቱት አባ ጠቅል ጠላት የሚበዛባትን ሀገር በብልሃት መምራት እንደሚገባ ተረድተዋል። ጦርነት የሚያመጣውን ኪሠራና ውድመት ያውቁታል እና ወደ ጦርነት ላለመግባት ብርቱ ጥረት አደረጉ። ዳሩ ሰላም ከአንድ ወገን ብቻ በሚመጣ ፍላጎት አይሰካም ነበርና ሳይሳካላቸው ቀረ።
የማይቀረው ጦርነት ተጀመረ፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች ከጠላት ጋር ተናነቁ። ጠላት አስቀድሞ አቅዶት በነበረው ስልት በጦርነት ሕግ በተከለከለ የመርዝ ጋዝ በመጠቀም በኢትዮጵያውያን ላይ ያዘንብ ጀመር። ኢትዮጵያውያንም ለሚወዷት ሀገራቸው፣ ለሚመኩባት ሠንደቃቸው ሲሉ በጀግንነት ተዋደቁ። ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቁትን በጎራዴ ይቀሉት ጀመር። ባንዳዎች መንገድ በመምራት፣ ወሬ በማቀበል እንዲያም ሲል ከጠላት ጋር በማበር ይዋጉ ነበር። የቁርጥ ቀን ልጆች ግን ነብሳቸውን ለእናት ኢትዮጵያ አሳልፈው ሰጡ። ሃይማኖት፣ ብሔር ምንም ሳይለያቸው ለእናት ሀገር በጋራ ዘመቱ፣ በጋራ ራሳቸውን ሰጡ።
በዚህ ጦርነት በኢትዮጵያ ወገን ሆነው የተሳተፉትና የጦርነት ውሎውን መዝግበው ያስቀሩት ኮሎኔል አልኸንድሮ ዴል ባዮ ጀግኖቹን ሲገልፁ ኢትዮጵያውያን የያዙት ሳንጃ፣ ጦር፣ ጎራዴ፣ አንዱ በአንዱ ላይ እየተሳካ ደም ለብሶ ሲወጣና የሚተራመስ የሰው ስብስብ ብቻ ምድሪቱን ሞልቷታል በማለት መዝግበዋል።
“ኢትዮጵያውያን ጠላት ሲያይልና ይበልጥ ሲያጠቃቸው ጀግንነታቸውና የውጊያ ስሜታቸው ይበልጥ ይጨምራል፣ ይባባሳል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት የሚተኮስባቸው ጥይት ምንም ሳያስጨንቃቸው ተወርውረው እየተንደረደሩ ወደ ጠላት ምሽግ በመሮጥ ጥይት እያፈተለከችበት የምትወጣበትን አፈሙዝ በመጨበጥ ከምንጩ ማድረቅ ነው ዋናው ዓላማቸው” ሲሉ ኮሎኔሉ መዝግበዋል። ኮሎኔሉ የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት አይተውና አብረው ኖረው ነው እንዲህ ያሰፈሩት።
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ለሚመጣ ሁሉ አይመለሱም። ሞትን ይንቃሉ፣ ለሀገር ክብርና ፍቅር ራሳቸውን አሳልፈው ይጥላሉ። በአንድነት ይቆማሉ። በአንድነት ጠላቶቻቸውን ይጥላሉ። ድል የማድረጋቸው፣ በአሸናፊነት የመኖራቸው ምስጢር አንድነታቸው ነው። አንድነት የማይነቃነቅ የኢትዮጵያ አጥር እንደሆነ ያውቃሉና።
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ለመጣ ጠላት ምንም አይነት ነገር አይመልሳቸውም። በታንክ የሚመታቸውን ጠላት ገስግሰው ሄደው በያዙት ጠመንጃ መትተው ይጥሉታል። “ቆራጦቹ የአቢሲኒያ ልጆች እየዘዘሉ ታንኩ ላይ ይሣፈራሉ። ከዚያ በአገኟት ቀዳዳ ሁሉ የጠመንጃቸውን አፈሙዝ ወደ ውስጥ በማስገባት በውስጥ ያሉትን በጥይት ይበሳሷቸዋል” ሲሉ ጀግንነታቸውን ገልፀዋል። ያ ነው የኢትዮጵያውያን ትክክለኛ ማንነት ለሀገር መሞት፣ ለሀገር መሰጠት። መከፋፈል፣ ወንድም በወንድሙ ላይ መነሳት በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቅ አይደለም። ኢትዮጵያን ያስከበሯት እነዚያ ጀግኖች ናቸው።
“በጎራዴያቸው እንደዘመኑ የስንዴ ማሳ አጨዳ አየሩን ይቀዝፉታል። እነዚያ ጥቁሮች ትእዛዙን ለመፈጸም በመጠቃታቸው አንጀታቸው እያረረ የከፍታ ቦታውን ለመያዝ ሽቅብ ዝግ ባለ ፍጥነት በረድፍ እየወጡ ነው። ከጠላት በኩል መሣሪያዎች ያለ ማቋረጥ እሳታቸውን ይተፋሉ። በዚህ መሃል ምንም ሊገታቸው ያልቻለው የዛች ምድር ልጆች ያላቸውን ጉልበት ሁሉ በመጠቀም ፊት ለፊት ወጡ። ፈጣን የሆኑትና ቀጠን ያሉት እነዚህ ጦረኞች በከፍተኛ ስሜት ያንን ተራራ ሽቅብ ይቧጥጣሉ። የሚዘንብብቻውን የጥይት ናዳም ከቁም ነገር ሳይቆጥሩት ይጓዛሉ። የእነዚህን የጥቁሮች የአፍሪካ ምድር ልጆች ወደ ፊት መገስገስን በጥይት ናዳ ለመግታት መሞከር ልክ የአንድን ወራጅ ውኃ ቁልቁል መፍሰስ በመድፍ ደብድቦ ለማቆም እንደመሞከር ይቆጠራል ።” በማለት ጀግኖችን ከማዕበል ጋር በማነፃፀር ገልጿቸዋል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን እንዲህ ናቸው።
ንጉሡ አባ ጠቅል ኃይለ ሥላሴ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ያደረገችውን ወረራ ለማስቆም ወደ አውሮፓ አቅንተው የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም ይገልጡ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ የወራሪውን ሠራዊት አምርሮ እየታገለው እንደሆነና ፈፅሞ ለቀኝ ገዢ እንደማይንበረከክ ይነግሩ ነበር። ኢጣሊያ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀብሎኛል። ሀገሪቱንም በሰላም በማስተዳደር እገኛለሁ ስትል ንጉሡን ትሞግት ነበር።
ጃንሆይም ” የለም ሕዝቡ ለሀገሩ ነፃነት በአርበኝነት እየተዋደቀ ነው። አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍልም በአርበኞች እጅ ይገኛል ” አሉ። እውነቱን ለማጣራት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዑክ ላከ። የልዑክ ቡድኑን እየመሩ የመጡት ደግሞ ፈረንሳዊው ሙሴ ፖል ነበሩ። አኒህ ሰውም በአርበኝነት ሥራቸው አስፈሪ ከነበሩት ከራስ አሞራው ውብነህ ተሰማ ጋር ተገናኙ። ራስ አሞራው ውብነህም ተቀብለው አስተናገዷቸው።
ራስ አሞራውም የልዕኩ ቡድኑ የአርበኞች እና የጠላትን እንቅስቃሴ እንዲቃኝ ፈቀዱለት። ከቅኝታቸው በኋላ ራስ አሞራው ጠየቋቸው። ያን ቃላቸውንም በማስታወሻ ይዘው አስቀሩ። የልዑኩ መሪ ሙሴ ፖል ” አሁን እርስዎ እንዳስቃኙን እውነት እና ውሸት ለመለየት ችለናል። እውነቴን ነው ኢጣሊያ ከዛፍ ላይ ተንጠልጥላ እንዳለች ጦጣ፣ ከገደል አፋፍ ላይ እንደተቀመጠች ዝንጀሮ ከተማና ምሽግ ላይ ተወስኗል። የእናንተ ሀገር ኢትዮጵያ ጥንት በታሪክ ፊት የሥልጣኔ ጮራ ነበረች። ዛሬ ደግሞ ለአርበኝነት ሙያ ቀዳሚ መምህርት ሆና አገኘኋት። ከዚህ በኋላም የእናንተ የአርበኝነት ተጋድሎ አጋዥ እንደሚፈጥርላችሁ አልጠራጠርም። ” አሉ
ኢትዮጵያውያን ጀግኖችም በጀግንነታቸው ነፀነታቸውን ተጎናፅፈው ሀገራቸውን ነፃ አውጥተው ጠላትን ዳግም አሳፍረው ታሪክ ሠሩ። የንጉሡ ወደ ውጭ መሄድ ሀገራቸውን አላስተዋቸውም። ልዩነት አልበገራቸውም ሀገር የሚሉት ገመድ አስተሳስሯቸው በአንድነት ኖሩ እንጂ።
ደምና አጥንት ያፀናትን አባቶች በጀግንነት ያቆዩዋትን ሀገር ዛሬም በጀግንነት ማፅናት፣ በአንድነት መማቆም ግድ ይላል። መከፋፈሉና መጋጨቱ የአባቶችን ዋጋ ዝቅ ማድረግ፣ ለጠላትም መመቸት ነው። ኢትዮጵያዊ ደግሞ ለወዳጅ እንጂ ለጠላት የተመቸ ባሕሪ የለውም። ለጠላት የማንመች እንሁን። ያን ጊዜ ክፉዎች ያፍራሉ። ጠላቶች ይጠፋሉ። ኢትዮጵያውያን ኢጣልያን ያሸነፉት ተለያይተው ሳይሆን አንድ ኾነው ነው። ዛሬም አንድ በመኾን ከውስጥም ከውጭም የሚነሱትን ጠላቶች በስክነት እና በአንድነት መመለስ ግድ ይላል። ማሸነፊያው የፀና አንድነት እና የበረታ ኢትዮጵያዊነት ነው።
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/