“ሕዝቡ ጠላቶች የከፋ ነገር ሊያደርጉ እንደሚችሉ በማሰብ በአንድነት በመቆም እንደ ቀደመው ሁሉ መታገልና ማሸነፍ አለበት” ምሁራን

153

ጎንደር : ሚያዝያ 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከዘመን ዘመን ፈተናዎች የሚበዙበት፣ መከራዎች የሚፀኑበት፣ ጠላቶች የሚበረክቱበት፣ እርሱን ለማጥፋት ግንባር የሚፈጥሩበት ሕዝብ ነው – አማራ። ዳሩ ፈተናዎች ቢበረክቱም አርቆ አሳቢነት ፣ ጀግንነት ፣ አንድነት እና አይደፈሬነት ተችረውታል እና በየዘመናቱ የገጠሙትን ችግሮች በጥበብ አልፏቸዋል፣ በድል ተሻግሯቸዋል።

ከኢትዮጵያዊነት ልክ የማይነቃነቀው የአማራ ሕዝብ በፀና አቋሙ ምክንያት በየዘመናቱ ከውጭም ከውስጥም የሚነሱ ጠላቶች የክፋት እጃቸውን ቀስረውበታል። በጀግንነት የገነባውን ስሙን፣ በአሸናፊነት የቀረፀውን ገድሉን፣ በድል አድራጊነት የከተበውን ታሪኩን ሊያጠለሹና ሊያበላሹ አያሌ ነገሮችን አድርገዋል።

ዳሩ “ላያስችል አይሰጥም” እንዲሉ አበው እንደጠላቶቹ መብዛት የማሸነፊያውን መንገድም ተችሮታልና ጠላቶቹን እያሸነፈ ማዕበል በበዛበት ውቅያኖስ፣ ሞገድ በበዛበት ሐይቅ ያለ መናወጥ ወደ አሰበው ይጓዛል። ከትናንት የቀጠሉት ጠላቶቹ ዛሬም በአንድነት የቆመውን፣ ለሀገር የሚኖረውን፣ ሀገርና ሠንደቅ የሚያከብረውን፣ ፍትሕ አዋቂ፣ መብት ጠባቂ የኾነውን ሕዝብ ሊከፋፍሉት፣ ከክብሩ ዝቅ ሊያደርጉት ሲታትሩ ይታያሉ።

አሁን አሁን በቀየው የሚሠራቸው አጀብ የሚያሰኙ መልካም ሥራዎች መልካምነታቸውን ገልጦ የሚያሳይ፣ መርምሮ የሚናገር የለም። በሌላ በኩል ደግሞ በቀየው ትንሽ የጥል ጭላንጭል ከታየበት ኮረት የምታክለው ችግር እንደ ተራራ ገዝፋ ትቀርብበታለች።

በአማራ ቀዬ ክፉ ነገር ተሰማች ከተባለ ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች አጀንዳ አድርገው ይነጋገሩበታል። በአንፃሩ የአማራ ሕዝብ የሞተባቸው፣ የተሰቃየባቸውና በደልና መከራ የበዛባቸው ጉዳዮች ሲኾኑ ትንሹን ነገር ለማጉላት ሲሽቀዳደሙ የነበሩ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች፣ ድርጊቱን ለማውገዝ ሲረባረቡ የነበሩ ፖለቲከኞች ፣ ለመተንተን ቀዳሚ የሌላቸው ማኅበራዊ አንቂዎች በራቸውን ዘግተው ዝም ይላሉ።

ከሰሞኑ በታሪካዊቷ በጎንደር ከተማ የተከሰተው ችግር ለዚህ አንደኛው ማሳያ ነው። ለምን ?

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ ዲን አገኘሁ ተስፋ (ዶ.ር) ጎንደር ኢትዮጵያዊ ለዛ ስላለውና ኢትዮጵያዊነት በፅናት ስላለበት ኢትዮጵያ ጠንካራ እንዳትኾን የሚሹ አካላት የጎንደርን ችግር ለማግዘፍ ፈልገዋል። ጎንደር ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚመጣ ኢትዮጵያዊ የሚኖርባት ከተማ ስለኾነች ይህ ደስ ያላላቸው ሰዎች ችግሯን ከፍ ለማድረግ እንደሚሯሯጡ ነው የገለጹት ።

የጎንደር ሕዝብ አይደለም እርስ በራሱ ከሩቅ ለሚመጣ ሰው እንኳን ክብር የሚሰጥ ደግ ሕዝብ መኾኑን ያነሱት ዶክተር አገኘሁ ከሰሞኑ የተፈፀመው ችግር የጎንደርን ሕዝብ የማይወክል ነውም ብለዋል።

ጎንደር ውስጥ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለጥል የሚነሳሱ አለመኾናቸውን የገለፁት ዶክተር አገኘሁ ለተነሳው ችግር ጥፋተኛ የኾኑትን አካላትን መንግሥት ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች በግፍ ይገደላሉ ፣ የሃይማኖት ተቋማት ይቃጠላሉ፣ ይዘረፋሉ፣ ይደፈራሉ፣ ብዙዎች ግን ትኩረት አይሰጣቸውም ። የሚያወግዝላቸውም የሚያዝንላቸውም አይታይም ። የጎንደርን ችግር ግን ሁሉም በተለየ አተያይ ተመልክተውታል ነው ያሉን። በየአቅጣጫው ኢትዮጵያ እንዳትኖር የሚፈልግ እንዳለም አመላክተዋል። ጎንደር ላይ የኾነውን ችግር የኢትዮጵያ ሚዲያዎች እና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በከፍተኛ ትኩረት ሽፋን ሰጥተውታል ለምን? የሚለውን መጠየቅና ዓላማውን መረዳት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

የግብፅ ሚዲያዎች በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ስለሚደርሱ ግፎች አላወሩም የሚሉት ምሁሩ በጎንደር ስለተፈፀመው ጉዳይ ግን በትኩረት አውርተዋል። ለምን ጎንደር ሲኾን? ሁላችንም የምንኖርባት ከተማ ስለኾነች ይሆን? ወይስ ሌላ ጉዳይ አለ የሚለውን መረዳት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል ።

ማኅበረሰቡ ራሱን አንድ አድርጎ የሚወረወሩበትን ችግሮች መመከት እንደሚገባው አመላክተዋል ። የጎንደር ሕዝብ ርህራሄ ያለው፣ የሚደንቅ ታሪክና እሴት ያለው ሕዝብ ሆኖ ሳለ መልካም እሴቱ እንዲበላሽ የሚፈልግ አለ ነው ያሉት። የቀደመው እንኳን ቢቀር ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የጎንደር ሕዝብ ለኢትዮጵያ መፅናት ላበረከተው አስተዋጽኦ ክብር ሊሰጠው ሲገባ ትንሽ ነገርን መነሻ በማድረግ ወደ አልተገባ መንገድ ለመውሰድ የሚፈልጉና የሕዝቡን ታላቅነት ዝቅ የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውንም አንስተዋል።

ሕዝቡ ጠላቶች የከፋ ነገር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማሰብ እንዳለበትና በአንድነት በመቆም እንደ ቀደመው ሀሉ መታገልና ማሸነፍ እንዳለበት ነው የተናገሩት። የጎንደር ሕዝብ ታላቅ ኀላፊነት ያለበት መኾኑንም አመላክተዋል ። የአማራ ክልል መንግሥትም ለሕግ የበላይነት መከበር መሥራት እንደሚገባው ነው የተናገሩት። መንግሥት እውነተኛ ለውጥ ፈልጎ ከኾነ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለውን የጎንደር ሕዝብ ሊያከብረው እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሕዝቡ ሀገርን የመታደግ ታሪካዊ ኀላፊነት እንዳለበትም ገልጸዋል ። ፅንፍ ይዘው የሚጓዙ ሰዎችም አካሄዳቸውን አስተካክለው ወደ ሚጠቅመው መንገድ መመለስ እንደሚገባቸው ነው ያመላከቱት ። መንግሥት ሰላምን ለማስፈን ሀሰተኛ ሚዲያዎችን የሚጠይቅበትና እርምጃ የሚወስድበት አሠራር ሊኖረው እንደሚገባም ተናግረዋል ። ማኅበራዊ አንቂ ነን የሚሉ ግጭት ጎሳሚ ሰዎች በቃችሁ ሊባሉ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የጎንደር እና የአካባቢው ሕዝብ የሀገር መኖር ወሳኝነትን የሚረዳና ከመንደርተኝነት አስተሳሰብ ወጣ ያለ ሀገራዊ አስተሳሰብ ያለው በመኾኑ ችግሮች እንደበዙበትም ገልጸዋል። አማራ ከዘር ሀሳብ ከፍ ያለ አስተሳሰብ ያለው፣ ሰውን በሰውነቱ የሚያይ በመኾኑ ችግሮች እንደተበራከቱበትም ተናግረዋል። ከፍ ያለ አስተሳሰብ ያለው ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ደካማ እንድትኾን ለሚፈልጉ አካላት የተወደደ አለመኾኑንም አንስተዋል። የጎንደር ሕዝብ ደረጃው ዝቅ እንዲል የሚሠራ ብዙ ሴራ አለ፣ ሕዝቡ በቀደመው ጥበቡ መጓዝ አለበት ነው ያሉት።

በአማራ ክልል የሚፈጠሩ ችግሮችን በውስጥም በውጭም የሚገኙ አካላት የተናበቡ እስኪመስል ድረስ እያራገቡ እንደሚሠሩም አስረድተዋል።

ሌላኛው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለማቀፍ ግንኙነት መምህሩ ዶክተር ባምላክ ይደግ አንድን ሀገር ለማፅናት የፖለቲካ ባሕል ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል። አሁን ላይ የአማራ ሕዝብና የአማራ ክልል መንግሥት ተቋም ሊገነቡ ይገባል የሚሉት መምህሩ ከሌሎች ጋር በጋራ ሊያኖራቸው በሚችል መልኩ የፖለቲካ ባሕል ሊኖራቸው እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት። በአማራ ክልል የሚፈጠረው ችግር ከፍ እንዲል የሚያደርገው የአማራ ፖለቲካ በሚፈለገው ልክ አለማደጉ መኾኑንም ነው ያነሱት።

በኢትዮጵያ የሚነሱ ችግሮች ከቦታ ቦታ የተለያየ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ያነሱት መምህሩ በአማራ ክልል የሚፈጠሩ ችግሮች ከመጠናቸው በላይ ከፍ ብለው እንደሚነገሩ አንስተዋል። የአማራ ሕዝብ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና በኢትዮጵያ እንዲጠላ የሚያደርግ የሃሰት ትርክት ስለተሠራበት በአማራ ክልል ኮሽ ባለ ቁጥር ነገሮች እንደሚገኑ ገልጸዋል። የአማራ ሕዝብ እንዲጠላ የሚሠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ግለሰቦች እና ቡድኖች መኖራቸውንም አመላክተዋል ። ሕዝብና መንግሥት ተቀራራርበው መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

በየአካባቢው የሚነሱ ችግሮችን በአካባቢው ባሕልና ስልት መሠረት መመለስ እንደሚገባ ነው ያመላከቱት። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአፍራሽ አስተሳሰብ ወጥቶ በሰከነ መንገድ ጠላቶች ከዘረጉበት ወጥመድ ማምለጥ እንዳለበትም አመላክተዋል።

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየገበያውን ፍላጎት ያገናዘበ ዕውቀትና ክህሎት ያለው፣ የሰለጠነ እና ተወዳዳሪ የሰው ኀይል እያፈራ መኾኑን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
Next articleʺየገፏትን ጥላለች፣ የደፈሯትን ሰባብራለች”