ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥና የወንጀል ተግባራትን መንግሥት እንዲያስቆም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠየቀ፡፡

124

ሚያዝያ 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በወራቤ ከተማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት እና በፕሮቴስታንት አማኞች ቤተ አምልኮዎች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት እና በፕሮቴስታንት አማኞች ቤተ አምልኮዎች ላይ የተፈፀመውን ሕገ ወጥና የወንጀል ተግባር በእጅጉ እንደሚያወግዝ ገልጿል፡፡
ተግባሩ በየትኛውም ሃይማኖት ተቀባይነት የሌለው መኾኑንና በሕግ ሊያስጠይቅ የሚገባው ተግባር እንደኾነ ጉባኤው በጽኑ ያምናል ነው ያለው፡፡
ሚያዚያ 18/2014 ዓ.ም በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ የተፈፀመውን አስነዋሪ ተግባርን አስመልክቶ ጉባኤው በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ ተግባሩን አምርሮ በማውገዝ ጥፋትን በጥፋት፣ ወንጀልን በወንጀል ለማረም የሚደረግ ሙከራ እንዳይኖር ማስገንዘባችን ይታወሳል በማለት አብራርቷል፡፡ ይሁን እንጅ ትናንት በኾነው ኹሉ አዝነን ሳንጨርስ ይህ መከሠቱ በእጅጉ አሳዝኖናል ሲል ገልጿል፡፡
ኹሉም ሃይማኖቶች ሰላምን የሚሰብኩ፣ ትምህርትን የሚያስተምሩና ለሌሎች ስለመኖርና መስዋእትነት ስለመክፈል የሚገዳቸው እንደኾኑ የሚታወቅ ቢኾንም በሃይማኖት ስምና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚፈጸመው ሕገ ወጥነትና ወንጀል እንደኾነ ታውቆ መንግሥት ሕግና ሥርዐትን እንዲያስጠበቅ ጉባኤው አበክሮ ይጠይቃል ብሏል።
መንግሥት ሕግና ሥርዐትን ለማስፈፀም እንዲችል ቀደም ብሎ ያወጣቸውን ሕጎችን ኹሉ ተፈፃሚ ሊያደርግ ይገባል ነው ያለው መግለጫው፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙም ይሁን ሕዝበ ክርስቲያኑ ችግሮች እንዳይባባሱም አንዱ ሌላውን በመጠበቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ እየጠየቅን ችግር ፈጣሪዎችንም በማጋለጥና አሳልፎ ለሕግ አካላት መስጠት እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን ብሏል፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያው መልዕክት የሚላላኩ አካላትም በምትጽፉት ጽሑፍና በምታስተላልፉት መልዕክት ሀገራችሁንና ወገናችሁን ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጥ ኹሉንም ተግባር በማስተዋል እንድትከውኑ እየጠየቅን በሃይማኖት ስም የሚደረግ ጥላቻ ቅስቀሳን ባለማጋራት ኀላፊነታችሁን እንዲወጡ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል፡፡
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየልብ ወግ!
Next articleየደቡብ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በስልጤ ዞን በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዘ።