
ደሴ፡ ሚያዝያ 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከማንኛውም ሃይማኖት አስተምህሮ ውጭ የተደረገው አስነዋሪ ተግባር ሀገርና ሕዝብን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ በጋራ ሆነን እንታገላለን ሲሉ የደሴ ከተማ የሐይማኖት አባቶችና ሕዝባዊ ተቋማት ሕብረት አስታወቁ።
የደሴ ከተማ ሐይማኖት አባቶችና ሕዝባዊ ተቋም በጎንደር የተፈፀመውን ጥቃት በማውገዝ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተወካይ መላከብርሃናት ገብረጻዲቅ አስፋው እንደገለጹት በጎንደር ከተማ የተፈፀመው ጥቃት የማንንም ሃይማኖት የማይወክል አስነዋሪና ፀያፍ ተግባር ነው፡፡
የየትኛውም ሀይማኖት ሀገር እንዲፈርስ የሚፈቅድ አስተምህሮ እንደሌለው ጠቁመው፤ ክፉ ማሰብ እንኳ በየሃይማኖቱ የተጠላና የተወገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
ሁሉም ከዚህ አስነዋሪ ተግባር መጠንቀቅ እንደሚገባው ጠቅሰው፤ “ተንኮለኞች ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰሩ መኾኑን በመገንዘብ አገር በሴረኞች እንዳትፈርስ በጋራ ልንቆም ይገባል” ብለዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሕዝባዊ መጅሊስ ፕሬዚዳንት ሸህ እንድሪስ በሽር በበኩላቸው “በጎንደር ከተማ የተፈጸመው ጥቃት ከሁላችንም ሃይማኖት የወጣ አሳፋሪ ተግባር ነው” “የደረሰውን ጉዳት አጥብቀን እናወግዛለን፣ በየትኛውም ሃይማኖት ላይ ጥቃት እንዲፈጸምም አንፈቅድም፣ በጋራ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ እንሰራለን” ብለዋል።
“መንግስት አጥፊዎችን ነጥሎ ለሕግ በማቅረብ የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አለበት” ያሉት ሸህ እንድሪስ “በተለያዩ አካባቢዎች ተጨማሪ ጥፋት እንዳይመጣ ሕዝቡ መጠንቀቅና ከመንግስት ጋር መስራት ይገባዋል” ሲሉ አስገንዝበዋል።
”በጎንደር የደረሰው ጉዳት የማንንም ሃይማኖት የማይወክል፣ አጥብቀን የምናወግዘው ድርጊት ነው” ያሉት ደግሞ የደሴ መካነየሱስ ቤተክርስቲያን መሪ ቄስ መስፍን ጌታሁን ናቸው፡፡
ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉም በየሃይማኖቱ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።
የደሴ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቆሞስ አባ ማቲያስ ፍሊጶስ በበኩላቸው “እምነትን ሽፋን አድርገው በመካከላችን የተደበቁ ሴረኞችን አጋልጠን በመስጠት አንድነታችንን አጠናክረን ኢትዮጵያን ማዳን አለብን” ብለዋል።
“ተንኮል እንዲቆም ሁላችንም መጸለይና መስራት እንዲሁም የሰላም መሳሪያና ተምሳሌት ልንሆን ይገባል” ሲሉም አመልክተዋል።
”ኀብረተሰቡ አንድነቱን አጠንክሮ አካባቢውን በንቃት ሊጠብቅ ይገባል እንጅ በአሳፋሪ ተግባር መሳተፍ የለበትም” ያሉት ደግሞ የደሴ ቃለህይወት ቤተክርስቲያን አስተባባሪ ወንጌላዊ መላኩ ብርሃኑ ናቸው፡፡
የደሴ ከተማ ሴት ነጋዴዎች ተወካይ ወይዘሮ ዕፀገነት ታደስ በበኩላቸው “በጎንደር የደረሰው ጉዳት ሁላችንንም አሳፍሮናል፤ አሳዝኖናልም” ብለዋል፡፡
“እንዲህ አይነት የታሪክ ጠባሳ እንዳይደገም በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ በተለይ ሴቶች ቤተሰቦቻችንን በመምከር ኢትዮጵያን መታደግ ይገባናል” ሲሉ አመልክተዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የደሴ ከተማ የሃይማኖትና ሕዝባዊ ተቋማት በጎንደር የተፈጸመውን ድርጊት የሚያወግዝ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/