“በጎንደር በተከሰተው ግጭት የተሳተፉ ተጠርጣሪ አካላት በአካባቢው ሕዝብ እና በጸጥታ ኀይሉ የጋራ ጥረት በቁጥጥር ስር ውለዋል”የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት

135

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥቷል። የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) በሰጡት መግለጫ በጎንደር የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ በግጭቱ የተሳተፉ ተጠርጣሪ አካላትን በአካባቢው ሕዝብ እና በጸጥታ ኀይሉ የጋራ ጥረት በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) ክስተቱን ተከትሎ በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የሁሉም እምነት ተከታዮች ድርጊቱን ከማውገዝ ባለፈ ግጭቱ ወደ ሌሎችም አካባቢዎች እንዳይሰፋ ጥረት እያደረጉ ስለመኾናቸውም ተናግረዋል፡፡
ድርጊቱን ማውገዝ ሲገባቸው ግጭቱ ሃይማኖታዊ ገጽታ እንዲይዝ እና እንዲባባስ ያልተረጋገጡ እና ሆን ተብሎ የተፈበረኩ መረጃዎችን፣ የጥላቻ ንግግሮችን በማሰራጨት ግጭት እና ሁከት እንዲቀሰቀስ ሙከራ እያደረጉ ያሉ ኀይሎች ስለመኖራቸውም አንስተዋል፡፡
በአንድ በኩል አብያተክርስቲያናትን በሌላ በኩል መስጊዶችን የጥቃት ሰለባ ለማድረግ ሙከራዎች እየታዩ እንደሆነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ቀደም ብሎ በመልካም የማኅበራዊ አንቂነት የሚታወቁ የማኅበራዊ አንቂዎች ግራና ቀኝ ቁመው ቃላት ሲወራወሩ ተስተውሏል፤ ይህም አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡
ጽንፈኛ ኀይሎች የሚያተርፉት ከግጭት በመኾኑ ሕዝበ ቡስሊሙን ከክርስትና ወንድም እና እህቶቹ ለማጋጨት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
በዚህ እንቅስቃሴ በማወቅም ኾነ ባለማወቅ እየተሳተፉ ያሉ አካላት ከዚህ እኩይ ድርጊት እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡
ችግሮች በተፈጠሩባቸው አካባቢዎችም መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እያዋለ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩን ወደተለያዩ ቦታዎች ለማስፋት የሚደረግን እንቅስቃሴ መንግሥት እንደማይታገስም አስገንዝበዋል፡፡
በፌደራል እና በክልል ኀይሎች ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነም ተገልጿል።
መላው ሕዝብ መገንዘብ ያለበት በጎንደር የተከሰተውን አሳዛኝ ክስተት ወደሌሎች አካባቢ በተለይም አጸያፊ በሆነ መልኩ ወደ ወራቤ ግጭቱን ለማስፋፋት የሚደረግ እንቅስቃሴ የእስልምናንም የክርስትናንም ሃይማኖት ተከታዮች አይወክልም ብለዋል፡፡
ክስተቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ተላላኪዎቻቸው ጋር ተባብረው የከፈቱት ሀገር የማተራመስ ዘመቻ ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡
የጸጥታ ኀይሎች የእነዚህን ጠላቶች ሀገር የማተራመስ ሴራ ሲያከሽፉባቸው የቀራቸውን ችግር መፍጠሪያ የሃይማኖት ካርድ መምዘዛቸውን ነው ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት። ይህም በሕዝቡ እና በጸጥታ ኀይሉ በሳል እንቅስቃሴ እንደሚከሽፍ ነው የተናገሩት፡፡
በታሪካዊ ጠላቶች ታግዘው በሀገር ውስጥ ያሉ እኩይ ተግባራትን የሚፈጽሙ ኀይሎችን መንግሥት በፍጥነት አንድ በአንድ በቁጥጥር ሥር እንደሚያውላቸው ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ወቅት ሙስሊሙ ቤተክርስቲያኖችን ክርስቲያኑም መስጊዶችን በመጠበቅ የቆየ የጋራ እሴትን ማጎልበት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል በጦርነት የወደሙ አካባቢዎችን ለመገንባት እና አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለማመንጨት እየጣረ ባለበት በዚህ ወቅት ክልሉ
በሃይማኖት፣ በብሔር እና መሰል ጉዳዮች ከጎረቤት ክልሎች ጋር አለመረጋጋት እንዲገጥመው ጠላት እየሠራ ስለመኾኑም አንስተዋል፡፡
በምስጋናው ብርሃኔ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleቺርቤዋ ማንዚ 15-8-2014 ም.አ(አሚኮ)
Next articleሰላም የመጀመሪያም የመጨረሻም አማራጭ መኾኑን በመገንዘብ ኹሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳሰበ፡፡