የሲዳማ ሕዝብ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል በይፋ ተከፈተ።

752

ሀዋሳ : ሚያዝያ 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሲዳማ ሕዝብ የጨረቃና ከዋክብትን አቀማመጥ በማጥናት አዲስ ዓመቱን ያከብራል። በዓሉም ፊቼ ጫምባላላ ነው።

ፊቼ ጫምባላላ የሲዳማ ሕዝብ ማንነቱን ከተረዳበት ጊዜ አንስቶ ሲከበር ቆይቷል ይባልለታል። ፊቼ ጫምባላላ ምንም እንኳን በዓሉ የሚከበርበት ቋሚ ቀን ባይኖረውም በአያንቱዎች ጥቆማ መሰረት በዓሉ የሚከበርበት ቀን ተወስኖ እንዲከበር ይደረጋል። ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር የፊቼ ጨምባላላ መለያ ባህሪና ትርጉም እንደሆኑ ይነገራል።

የሲዳማ ሕዝብ የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል የክልሉን ርእሰ መሥተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተከፍቷል። በነገው ዕለትም በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ ይታደማል ተብሏል።

ሰላምና ፍቅር፣ አንድነትና መከባበር ይበዛበታል፤ ማዕከልና ማጠንጠኛውም ሰውነት ነው የሚባልለት ፊቼ ጫምባላላ የተጣሉ ሰዎች ይታረቁበታል፤ ሐዘን ላይ የነበሩ ሰዎችም ማቅ ያወልቁበታል፤ ከቀያቸው ርቀው ያሉ ወደቀያቸው ተመልሰው ከወዳጅ ዘመድ ይገናኛሉ።

ሌላው የዚህ በዓል ልዩ ገፅ የኾነው ለዚህ በዓል ተብሎ እርድ አይፈጸምም፤ ስጋም አይበላም። ከፍ ሲልም ደግሞ እንስሳትን መምታት እንኳን ወረቀት ላይ ያላረፈ ማኅበረሰባዊ ክብርና ጥበቃ ያለው ውጉዝ ሕግ ነው። ላሞች ሳር የበዛበት መስክ ላይ ይሰማራሉ።

እንስሳቱም አርሶ አደሩም በዚህ የፊቼ ጫምባላላ ወቅት ማሳ ሄዶ ማረስ አባት ያቆየው ልጅ የወረሰውና ያፀናው ከልካይ አጥር አለው። እንደ ምክንያት የሚነሳውም የፊቼ ጫምባላላ በዓል የሲዳማ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለዱር ገደሉና ለዛፍ ቅጠሉ ኹሉ ለሰላምና እረፍት የመጣ ብሩህ ዕለት ነው ስለሚባል ነው።

ትርጉም፦
ፊቼ :- ፊቼ የአዲስ ዓመት በዓል ዋዜማው ነው።
ጫምባላላ:- የአዲስ ዓመት የመጀመሪያው ቀን።

ዛሬም ፊቼ በደማቅ መክፈቻ ሥነስርዓት ተበስሯል። ነገ ጫምባላላ ይቀጥላል።

ሲዳማ ከአንድ ዓመት ወደሌላው የሚሸጋገርበት ሂደት ሁሉቃ ይባላል። ሁሉቃ ማለት ከሸምበቆና ከእርጥብ ቅጠል ተሠርቶ የሚቆም ነገር ነው። ሁሉቃ በቤተሰብና በማኅበረሰብ ደረጃ የሚሠራ ሲሆን፤ አዲስ ዓመት ሲገባ ሰዎችና ከብቶች ይተላለፉበታል።

ከዘመን ዘመን ተሸጋገርን እንደማለት ነው። የሲዳማ ሕዝብ አዲስ ዓመትን ሲቀበል ዓመቱ የብልጽግና እንዲኾንላቸው “ፊቼ ጄጂ” ይላሉ። እደጊ፣ ተመንደጊ፣ ለምልሚ እንደማለት ነው።

የክልልነት ጥያቄውን መልስ በቅርቡ ያገኘው የሲዳማ ሕዝብ ብዙ ዓመታትን በዓሉን ሲያከብር ቢኖርም ክልል ከሆነ ወዲህ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሲስተጓጎል ቆይቶ ፊቼ ጨምባላላን በድምቀት ሲያከብር የመጀመሪያው ነው ። እኛም ለመላው የሲዳማና አጋር ሕዝብ እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን እንላለን።

ፊቼ ጇጂ !

ዘጋቢ፡-እንዳልካቸው አባቡ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በሚያውክ አካል ላይ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ተናገሩ። በጎንደር የተፈጠረውን ችግር ለማባባስ የሚጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አቶ ደሳለኝ አሳስበዋል።
Next article“ክልሉን የትርምስ ቀጣና ለማድረግ የሽብር ድርጊት በሚፈጠሩ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)