የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በሚያውክ አካል ላይ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ተናገሩ። በጎንደር የተፈጠረውን ችግር ለማባባስ የሚጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አቶ ደሳለኝ አሳስበዋል።

247

ጎንደር: ሚያዝያ 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በጎንደር ተገኝተው ለአሚኮ እንዳሉት የተፈጠረው ችግር የኅብረተሰቡን አብሮነት ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ብለዋል። የተፈጸመው ድርጊት የጎንደር ባሕል፣ እሴት የማይመጥን በመኾኑ አሳዝኗል ነው ያሉት።

ድርጊቱ ከጎንደር እሴት፣ ባሕል፣ አብሮነትና ተደጋግፎ የመኖር ሂደት የወጣ ስለኾነ ቅስም ሰባሪ ድርጊት ነውም ብለውታል።

የጎንደርንም ኾነ የኢትዮጵያን ሕዝብ ክብር ዝቅ የሚያድርግና አብሮነትን ግምት ውስጥ ያላስገባ ድርጊት መኾኑንም አንስተዋል።

በትንሽ ነገር ግጭት ውስጥ መግባት ተገቢ እንዳልነበርም ገልጸዋል።

እሴቱ፣ መግባባቱና አብሮነቱ ታላቅ ስለኾነ ችግሩ እንዳይሰፋ ወጣቶች ፣ የሃይማኖት አባቶች እና መላው ማኅበረሰብ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመኾን መቼም ቢኾን አብሮነትን የሚነጥል ነገር ሊኖር አይገባም የሚል የፀና እምነት በመያዝ መሠራቱንም ተናግረዋል።

ሰላምና ደኅንት እንዲረጋገጥ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።

የሃይማኖት አባቶች ታላቅ ታሪክና እሴት አላቸው ያሉት አቶ ደሳለኝ ከየትኛው የሕግ አሠራር የተሻለ ልምድ ያላቸው በመኾኑ እነርሱን ይዘን ችግሩን በዘላቂነት እንፈታዋለን ብለን እየሠራን ነውም ብለዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በነበረው እሴትና ባሕል መሠረት ከሃይማኖት አባቶች ጋር እየመከሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

የኹለቱም ሃይማኖት አባቶች ችግሩን በነበረው ባሕልና እሴት እንፈታዋለን ብለውናልም ነው ያሉት።

መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀውናል ያንንም እያደረግን ነው ብለዋል።

አጥፊዎችን የማጣራት እና መረጃዎችን የመሰብሰብ ሥራ መሠራቱንም አስታውቀዋል።

“የተደራጀ እና የተጠናከረ የስምሪት አቅጣጫ አስቀምጠናል፤ አጥፊዎች እነማን ናቸው የሚለው የማጣራት ሥራ ተሠርቷል፣ መረጃዎች ተወስደዋል፣ በተገኘው መረጃ መሠረት ኦፕሬሽኑን እንሠራለንም” ነው ያሉት።

የተለያየ ዓላማ ያለው፣ የጎንደርን ሰላም የማይፈልግ አጥፊ አካል እንዳለም ተናግረዋል። “ከማኅበራዊ አንቂ ነኝ ባይ ጀምሮ ሀገር የሚያጠፋ አካል አለ፣ በምርምራ እያጣራን ከሕዝብና ከሀገር የሚበልጥ ስለሌለ አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለንም” ብለዋል።

የፀጥታ መዋቅሩ የራሱን ሥራ እየሠራ ይቀጥላል፣ የሕዝብ ለሕዝብ ሥራውንም ጎን ለጎን እናስቀጥላለን ነው ያሉት።

በጎንደር የተፈጠረውን ችግር ለማባባስ የሚጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

“ስለ ሰው ስብዕና መሥራት ሲገባ ለገንዘብ የሚሯሯጡ፣ ከሙታን ደም ገንዘብ ለመፈለግ የሚሠሩ አካላት ኢትዮጵያን ቢያስቡ የተሻለ ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ከሚያስቡ አካላት ጎን ኾነው ከሚሠሩት ይልቅ ኢትዮጵያን ተባብሮ ለመገንባት ከሚሠሩት ጋር ይተባበሩም ነው ያሉት።

አሁን ላይ የምንፈልገው የሚደግፈንና የጎደለውን የሚሞላ እንጂ ችግር የሚያባብስ አንፈልግም፤ በዚህ ጉዳይ የቆሙ ሰዎች የቀን ጉዳይ ካልኾነ በስተቀር እርምጃ እንወስዳለን፤ ከሕዝብና ከሀገር የሚቀድም አንዳች ነገር የለንምም ብለዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ጠብ አጫሪ መልዕክቶችን አወገዘ።
Next articleየሲዳማ ሕዝብ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል በይፋ ተከፈተ።