
የጎንደር ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ምክር ቤት የሰጠው መግለጫ ቀጥሎ ይቀርባል።
በከተማ አስተዳደራችን በአራዳ ክፍለ ከተማ ላይ በተፈጠረው ግጭት በምንም ሁኔታ የሁለቱን እምነት ተከታይ ማኅበረሰብን የማይወክል ጥፋት ተፈጽሟል። ጥፋቱ የተፈፀመው በጥቂት ጽንፈኛና አክራሪ ግለሰቦች የተከበሩትን የሁለቱን እምነት ተከታዮች ወደ ለየለት ግጭት ለማስገባት ሆን ተብሎ ለግጭት የማያበቃ ምክንያትን በመምዘዝ ጥፋት እንዲፈጠር የተቀነባበረና የተመራ ሴራ ነው።
በዚህ እኩይ ተግባር ከሁለቱም የእምነት ተከታዮች የህይዎትና አካል መጉደል እንዲሁም የንብረት መቃጠልና ዘረፋ አጋጥሟል። በተፈጠረው ግጭት በንጹሃን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የከተማ አስተዳደሩ ጥልቅ ሐዘን የተሰማው መሆኑን እየገለጽን ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን እንመኛለን።
ይህ ቡድን የፈለገው ጎንደርን ማቃጠል፣ መዝረፍና ማዋረድ ሲሆን ይህ ክፉ ተልዕኳቸው በፀጥታ መዋቅሩ፣ በሁለቱም የእምነት አባቶችና ወጣቶች እንዲሁም በሀገር ሺማግሌዎች ጥረት የፈለጉት ጥፋት ሳይደርስ መቆጣጠር ተችሏል።
በተፈጠረው ችግር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው የተገኙ ሙስሊሞች እንደ ነበሩና የእምነቱ አባቶችም ጉዳት ሳይደርስባቸው ለፀጥታ አካላት ያስረከቡ መሆኑ፣ በተመሳሳይም በመስጂድ ውስጥ የተጠለሉ የክርስትና አማኞች እንደነበሩና ከጥቃት የዳኑ መሆኑ ተረጋግጧል። ይህ ልምድ ደግሞ የዛሬ ሳይሆን ትናንትም የእምነት ተቋማትና አባቶች የችግር ጊዜ ታማኝ መሸሸጊያ (መጠለያ) ዋስትና መተማመኛ መሆኑ ታውቆ ያደረ በመሆኑ አንደኛው በሌላኛው በእጅጉ የሚያምን አንድና ያው የሚባል የሕብረተሰብ ክፍል በመሆናቸው ነው።
የጎንደር ሕዝብ ታሪክ መረዳዳት፣ መከባበር፣ መቻቻልና መፋቀር በፋሲካ ሙስሊሞች የሚያስተባብሩበት በኢድም ክርስቲያን ወንድሞች የሚያግዙበት እንጅ ዛሬ በጥቂት የጥፋት ቡድኖች የተመራው ጥፋት በፍፁም የጎንደርን ልክ የሚመጥንና የሚወክል ባለመሆኑ መላው ሕዝብ በአገኘው አጋጣሚ እያወገዘው ይገኛል።
የተፈጠረውን ቃጠሎም ሕዝቡ በነቂስ በመውጣት በከፍተኛ ርብርብ መቆጣጠር ችሏል።
አሁን አካባቢው ሙሉ በሙሉ ከፀጥታ መዋቅርና ከአካባቢው ነዋሪ ጋር ትብብር በማድረግ የተረጋጋ ሰላም ለመፍጠር በሁሉም አካባቢ ስምሪትና ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል። ሁሉም የጎንደር ሕዝብ ለከተማችን መረጋጋት ከፀጥታ አካሉ ጎን በመሰለፍ ቀንደኛና የጥፋት ኀይል የሆኑ በህይዎትና በአካል ጉዳት እንዲሁም በዘረፋ የተሰማሩት እየተለቀሙና እየተያዙ በመሆኑ ለዚህም ሕዝቡ የተለመደውን ንቁ ተሳትፎ በማድረጉ ማመስገን እንፈልጋለን።
በቀጣይም ቀሪ የጥፋት ኀይሎችንም አጋልጦ ለፀጥታ መዋቅሩ እንዲያስረክብ የተለመደው ትብብራችሁ እንዲቀጥል፤ በብሎክ አደረጃጀታችሁም አካባቢያችሁንና ሰፈራችሁን የንግድ ተቋማትን እንዲሁም የእምነት ተቋሞችን በመጠበቅ ከተማችን ከጥፋት እንድናድን ጥሪ እናስተላልፋለን።
ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ከዚህ እኩይ ተግባራቸው የማይታረሙ አጥፊዎችን ሕግ ለማስከበር በጭራሺ የማንታገስ መሆኑን እየገለጽን በሁከቱ የደረሰውን ጥፋት የምርመራ ቡድኑ እያጣራ ስለሆነ መረጃው እንደተጠናቀቀ ለሕዝባችን የምናሳውቅ በመሆኑ እስከዚያው በትዕግስት እንድትጠብቁን እያሳወቅን አካባቢያችን በንቃት እንድንከታተል በድጋሜ እናሳስባለን።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ምክር ቤት
ሚያዝያ 18/2014 ዓ.ም
ጎንደር