
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሻጋሪው የደቡብ ወሎው አማራ ሳይንት እና ኮሬብ አካባቢ ነው፡፡ ወዲያ ማዶ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሰንሰለታማ ተራሮች ደረታቸውን ሰጥተው ይታያሉ፡፡ ወዲህ ማዶ ደግሞ የአቡነ ፍሊጶስ ትምህርት ቤት፣ ዘርዓይቆብ እና ግማደ መስቀሉ ለተወሰኑ ቀናት እረፍት ያደረጉባት ደብረ ኢንቁ ማሪያም ከፍ ብላ ትታያላች፡፡ በዚያ ምድረ በዳ ልምላሜዋን ላስተዋለ “ግሩም!” የምታሰኘው ንብ አዘሏ (ንብ አዝላ) ማሪያም ብዙም ሳትርቅ በቅርብ እርቀት ከደብሩ እግር ሥር ትገኛለች፡፡
ጣሊያኖች “አውት ሳይድ” ሲሉ የሰየሙት እስካሁንም ሀገሬው “አውሳይድ” እያለ የሚጠራው የአይገልዶ እልክ አስጨራሽ ተራራ በኩራት ይገማሸራል፡፡ ጸሐፊው ገሪማ ታፈረ “ጎንደሬ በጋሻው” በሚለው የታሪክ መጽሐፋቸው በዚህ አካባቢ አርበኞች የጣሊያንን ሰላቶ በጦርነት እንደተጫዎቱባቸው ነግረውናል፡፡
የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ከዓመት አንድ ቀን በዚህ አካባቢ መንፈሳዊ የጉዞ ተጋድሎን ያደርጋሉ፡፡ ሰማእቱን እያሰቡ በአብዛኛው ጉዞው የሚደረገው በምሽት ነው፡፡ አንዱ የሌላውን ኮቴ እያዳመጠ የሚደረገው ጉዞ አዕምሮ ላይ ተጣብቆ የሚቀር አስደሳች ትዝታ አለው፡፡ እንደክር በቀጠነችው መንገድ፤ ዙሪያው ገደል በሆነው የተራራ ሰንሰለት የበረታውን የፀሐይ ወበቅ በቀን መቋቋም ይከብዳል፡፡ በተለይም ወጣቶች በየዓመቱ ሚያዚያ 23 የሽውኃ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የንግስ በዓልን ለመታደም ሌሊት መጓዝን ልምድ አድርገውታል፡፡
ነፍስን የሚያድስ ነፋሻማ አየር በሚነፍስበት ሌሊት ጉልበታቸው እየተብረከረከ ያንን ቁልቁለት የሚንደረደሩት ወጣቶች ብጀና ወንዝ የሚደርሱት በላበት ተጠምቀው ነው፡፡ ልብሶቻቸውን አውልቀው እና ከብጀና ወንዝ ውኃ ውስጥ ተነክረው ላበታቸውን ያለቃልቃሉ፡፡ አሸዋ ባጠራው ውኃ ተለቃልቀው እንደገና እንደብረት የሚጠነክሩት ተጓዦቹ ለሌላ ትንፋሽ የሚያሳጥር የዳገት ላይ ጉዞ ራሳቸውን ያዘጋጃሉ፡፡
የበረታ እያበረታ የደከመ እያዘገመ ሰማይ እና ምድር መላቀቅ ሲጀምሩ በበርሃ አዕዋፍት የማለዳ ዝማሬ ታጅበው ከብጀና ወንዝ ወደ ሸውኃ ጊዮርጊስ ዳገቱን እና ጠመዝማዛውን መንገድ ይጀምሩታል፡፡ ያንን ተዓምረኛ ደብር ምእመናኑ “የነገሩትን የማይረሳ፤ የለመኑትን የማይነሳ” ይሉታል፤ የሽውኃ ጊዮርጊስ፡፡ ለመሆኑ የሽውኃው ጊዮርጊስ የት ነው የሚገኘው?
የሽውኃ ጊዮርጊስ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ሀገረ ሰብከት ሰዴ ሙጃ ወረዳ ደስመን ቀበሌ ውስጥ ሽዋ ጊዮርጊስ በምትባል አካባቢ ይገኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ በአብርሃ ወአጽብሐ ዘመነ መንግሥት በ332 ዓ.ም እንደተመሠረተ ይነገራል፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ መሥራች ሀገር አቅኝው ሃብተ ኢየሱስ እደነበሩ ታሪኩ ይነግረናል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው አሁን ከሚገኝበት አቅራቢያ ቢሆንም የቃጭል ተዓምራትን እያሰማ አሁን ያለበት ቦታ ላይ እንዲታነጽ አድርጓል ይባላል፡፡
የሽውኃው ጊዮርጊስ ስያሜውን አስመልክቶ ሁለት ምክንያቶች ተያይዘው ይቀርባሉ፡፡ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያኑን ያሳነጹት ሃብተ ኢየሱስ የመጡት ከሽዋ ስለሆነ እና ታቦቱም ከሽዋ የመጣ በመሆኑ እርሱን ለማውሳት የሽውኃ ተባለ ይላሉ፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ እንደዛሬው ሳይሆን አካባቢው በደን የተሸፈነ እና በርካታ የውኃ ምንጮች ያሉበት በመሆኑ ስያሜው ከዚያ የመጣ ነበር ይላሉ አባቶች፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ውጭ የማይታይ እና ሥውር ጸበሎችም አሉት ይባላል፡፡ ስማቸውም መነኩሲት፣ መንክር፣ ንብ እና መናን ይባላሉ፡፡
የሽውኃው ጊዮርጊስ የሚገኝበት መልካ ምድር ወጣ ገባ የበዛበት እና አድካሚ የእግር ጉዞ ያለበት በርሃማ አካባቢ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አስቸጋሪ መልካ ምድራዊ አቀማመጡ፣ በርሃማነቱ እና አድካሚ የእግር ጉዞው በየዓመቱ ሚያዚያ 23 የሚከበረውን ዓመታዊ የንግስ በዓል የበዛውን ምዕመን ከመታደም አያግደውም፡፡ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር የሚሰባሰቡት የእምነቱ ተከታዮች ፈተናውን በጽናት፣ እንግልቱን በትዕግስት እና ድካሙን በእረፍት እያስታገሱ ደጁ ይደርሳሉ፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያም የሽውኃው ጊዮርጊስ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።
የመምሪያው ኀላፊ አቶ ወንዴ መሰረት የሽውኃው ጊዮርጊስ የጥንታዊ ታሪካዊ ባለቤትና የቅርስ መገኛ በመሆኑ ቦታው የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን የተጀመሩ የማስተዋወቅ ሥራዎች አሉ ብለዋል። ቦታው ለቱሪስት መዳረሻነት ምቹ ነው ያሉት ኀላፊው በቀጣይ የተያዙ እቅዶችን ዞኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሳር ክዳን የነበረው ቤተ ክርስቲያኑ ከመላው ዓለም በንግሱ ላይ በሚገኙ ምዕመናን ድጋፍ በቅርብ ጊዜ ዘመናዊ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተሰርቶለታል፡፡ ከአራቱም አቅጣጫ ወደ ደጁ የሚጎርፉት ምዕመናኑ በስለት የሚያስገቡለት ሃብት በበርሃ ውስጥ የከተመ ማረፊያ አድርጎታል፡፡ ዘንድሮም ንግሱን በተለየ ሁኔታ ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል፡፡
ሚያዚያ 23 ለዘመናት የተለያዩ ጓደኛሞች ያንን በርሃ በጋራ የማቋረጥ እድል በድጋሜ ያገኛሉ፡፡ የልጅነት ጓደኛሞች የቆየ ትዝታቸውን እንደገና ያወሳሉ፡፡ ኑ! የሰማእቱን ንግስ በጋራ እናክብር ተብላችኋል!
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/