በመድኃኒት አቅርቦት እየተፈተነ ያለው የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል የድጋፍ ጥሪ

178

ሚያዝያ 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ባለቤቱን ለማሳከም በሰቆጣ ከተማ የሚገኘው ተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል ማልዶ ተገኝቷል። የባለቤቱን ቅደመ ወሊድ ክትትል አገልግሎት ለማግኘት እስከ አራት ቀናት በቀጠሮ መመላለሱን ነግሮናል፤ ወጣት ንጋቱ መንግሥቴ፡፡ ከተገልጋዩ ቁጥር መብዛት የተነሳ ከስድስት ሰዓታት በኋላ ነበር የሕክምና አግልግሎት ያገኙት። ከምርመራ በኋላም ባለቤቱ የሚያስፈልጋት መድኃኒት በሆስፒታሉ ስለማይገኝ ከውጭ እንዲገዛ ተገድዷል፤ ይኽም ለከፍተኛ ወጭ እንደዳረገው ነው ወጣት ንጋቱ የነገረን፡፡

ሌላኛዋ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ያነጋገራቸው ወይዘሮ አሰፉ ገላየ በሆስፒታሉ ተመላላሽ ታካሚ ናቸው፤ ወይዘሮ አሰፉ የታዘዝላቸው መድኃኒት ከሆስፒታሉ መድኃኒት ቤት ባለመገኘቱ በተደጋጋሚ ከውጭ ለመግዛት ተገድደዋል፡፡ ለከፍተኛ ወጭ መዳረጋቸውን ነው በምሬት የሚያነሱት፡፡ ከተገልጋዩ ቁጥር መብዛት የተነሳ በሰዓቱ አገልግሎቱን ማግኘት አለመቻላቸውንም ነግረውናል፡፡

የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ፋሲካ ንጋቴ ሆስፒታሉ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት አንዱ መኾኑን አንስተዋል፡፡ እናም የውስጥ ገቢው በመቆሙ እና በወረራው በአካባቢው በተፈጠረ ችግር ምክንያት ጤና መድኅን ማስከፈል ባለመቻሉ እና በራስ አቅም መድኃኒት ማሟላት አልተቻለም፡፡ እናም ተገልጋዩ ከውጭ እንዲገዛ ተገዷል ብለዋል፡፡

አቶ ፋሲካ በተለይ ሕይወት አድን የሚባሉ መድኃኒቶች እጥረት በሆስፒታሉ ከፍተኛ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡

አኹን ላይ ሕጻናት በምግብ እጥረት ምክንያት እየተጎዱ መኾናቸውን ያነሱት ሥራ አስኪያጁ አልሚ ምግብ ማቅረብ አልተቻለም ነው ያሉት፡፡ ለጊዜው በድጋፍ መልክ በሚላክላቸው መድኃኒት አገልግሎት እየሰጡ መኾኑን ገልጸዋል።

ሆስፒታሉ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ውጭ በሪፈር የሚመጡ ተገልጋዮችን እና ተፈናቃዮችን ጭምር አገልግሎት የሚሰጥ ስለኾነ የቦታ እጥረት ስላለ ውጭ ላይ ጭምር አገልግሎት እየሰጡ መኾኑን አቶ ፋሲካ ተናግረዋል፡፡ ችግሩን በራስ አቅም መፍታት ባለመቻሉ የሚመለከተው አካል ኹሉ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

‹‹በክልሉ የምትገኙ ሆስፒታሎችም ካላችኹ መድኃኒት አካፍሉን›› ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና ግብዓት አቅርቦት የመድኃኒት ሥርጭትና ክትትል ዳይሬክቶሬት የክሊኒካል ፋርማሲ ባለሙያ ማርየ የኋላ የሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን የጥፋት ሰለባ የኾነው የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል ያለበትን ችግር ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአሸባሪው ቡድን ወረራ በክልሉ የጤና ተቋማት ላይ የፈጠረውን ውስብስብ ችግር ያነሱት ባለሙያው የተቋማቱ አገልግሎት ግብዓት እንዲሟላ ከአጋር አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ነግረውናል፡፡ ነገር ግን ችግሩ አኹንም ከአቅም በላይ በመኾኑ በጎ አድራጊ ግለሰቦች፣ ተቋማት እና ድርጅቶች ያላሰለሰ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበኢትዮጵያ ለሚታየው የሰብዓዊ ጉዳት ግማሽ ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ የሚረዳ መርሃ ግብር ይፋ ሆነ።
Next articleበእንግሊዙ ዘጋርዲያን ጋዜጣ ለማጭበርበሪያነት የዋለው የዋግኽምራ ተፈናቃይ እናቶች ምስል እውነታ ተጋለጠ።