
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የጊዮን መፍለቂያ፣የጣና ገዳማትና አድባራት፣በጥበብ የረቀቁት የቅዱስ ላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት፣ የጎንደር አርባ አራቱ አድባራት፣ የተዋቡት አብያተ መንግሥታት፣ የጋፋት የኢንዱስትሪ መንደር፣ የምድር ልዩ ውበት የራስ ደጀን መገኛ፣ የአንኮበር ቤተ መንግሥት፣ የጎዜ መስጂድ፣ የሾንኬ መንደር፣ የንጉሥ ሚካኤል ቤተ መንግሥት፣ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቤተ መንግሥት፣ የንጉስ ሚካኤል ቤተ መንግሥት፣ የኦሪት መሰዋዕት ባለ አሻራዋ መርጡለ ማርያም ገዳም፣ የግማደ መስቀሉ መገኛ ግሸን ማርያም፣ የተድባበ ማርያም ፣ የዘንገና ሐይቅ፣ የሐይቅ እስጢፋኖስ ፣ ታይተው የማይጠገቡ፣ የዓይን እረፍት የነብስ ሀሴት የሚደረግበት አካባቢ ነው፡፡ አካባቢውን ዞር ዞር ብሎ ለተመለከተ ሁሉ ዕፁብ ድንቅ የሚያሰኙ ቅርሶች ሞልተውበታል፡፡
ታሪክ ያከበራቸው፣ ሃይማኖት ያጸናቸው፣ እሴት ያበለጸጋቸው፣ ባሕል ያስዋባቸው እልፍ ሃብቶች ሞልተውታል፡፡ ዙሪያውን በታሪክና በቅርስ የተከበበ ነው፡፡ የዓለም ጎብኚዎችን ዓይን ሲስብ ኖሯል፡፡ ኢትዮጵያ የምትኮራባቸው፣ የምትመካባቸው፣ የቀደመ ስልጣኔዋን እንካችሁ የምትልባቸው፣ ጥበቧን የምትገልጥባቸው፣ ኃያልነቷን የምታስመሰክርባቸው ታሪካዊና መንፈሳዊ ሥፍራዎች መገኛ ነው የአማራ ክልል፡፡
በመንፈሳዊ፣ ቁሳዊ፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ሀብቶች የበለጸገው የአማራ ክልል ባለው የቱሪዝም ሀብት ልክ ግን ተጠቃሚ አልሆነም፡፡ የብዙ ብዙ ሃብት ያለው፣ ተፈጥሮና የጀግንነቱ፣ የብልሃቱ፣ የአርቆ አሳቢነቱ፣ የደግነቱና የኢትዮጵያዊነቱ ፍሬ ታሪክ ያደለው ነው፡፡ በሰው ሠራሽና በተፈጥሯዊ ችግሮች የተፈተነው የአማራ ክልል ሊያዩት የጓጉለት የዓለም ሕዝቦች ሳያዩት ቀርተዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች ናፍቀውት ከርመዋል፡፡ የዓለም ሕዘቦች መጉረፊያ የነበረው ክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ጎብኚዎቹ ቀንሰውበታል፡፡
እንግዳ የለመደው እንግዳ ተቀባይ የሆነው ደግ ሕዝብ እንግዶች በመቅረታቸው ከፍቶታል፣ በቱሪዝም ለራሱና ለሀገሩ ያገኘው የነበረው ገቢም ቀንሶበታል፡፡ በአማራ ክልል በቱሪዝም ሃብት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያላቸው አካባቢዎች ዛሬ ላይ ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡ በተለይም በቱሪዝም እንቅስቃሴው ጥገኛ የነበሩት አካባቢዎች አሁን ላይ ክፉኛ ተጎድተዋል፡፡ የቱሪዝም እንቅስቃሴው በመዳከሙና በመቀዝቀዙ ምክንያት ክፉኛ ከተጎዱት አካባቢዎች መካከል ደግሞ ላል ይበላ በግንባር ቀደም ይጠቀሳል፡፡
ለወትሮው እንግዳ በመቀበልና በመሸኘት ጊዜ ያልነበራቸው የላል ይበላ ነዋሪዎች ዛሬ ላይ እንግዳ ናፍቋቸዋል፡፡ እንደ አብርሃምና ሣራ ያለ እንግዳ ማደር የማይቻላቸው የላል ይበላ ነዋሪዎች በእንግዶች መቅረት አዝነዋል፡፡ እንግዳ በማስተናገድ የምትደምቀው ከተማም በእንግዶች መቅረት ምክንያት ቀዝቅዛለች፡፡ እንግዶቼ ሆይ ከየት ናችሁ? የትስ ቀራችሁ ? እያለች ነው፡፡
ቀደም ሲል በኮሮና ቫይረስ፣ ቀጥሎም በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን ወረራ ምክንያት ጎብኚዎችን ያጣችው ላል ይበላ የኑሮ መሠረቷ ተናግቶባታል፡፡ በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት የመብራት እና የውኃ አገልግሎት ያጣችው ላል ይበላ ለችግር ተዳርጋለች፡፡ በከተማዋ ሢሠሩ የነበሩ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች መዘግየትና ይባስ ብሎ ማቆም የዜጎችን ሕይወት ከእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ አድርጎታል፡፡
የላል ይበላ የመብራት ኀይል መነሻ አላማጣ ነው፡፡ አላማጣ ከተማ ደግሞ በሽብር ቡድኑ ሥር መሆኗ ነዋሪዎቹ የመብራት ኀይል እንዳያገኙ አድርጓቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኀይልም ዋግ ኽምራንና ላል ይበላን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ የአላማጣን ነጻ መውጣት እጠብቃለሁ ብሏል፡፡ ምን አልባት ላል ይበላ ከአላማጣ ውጪ ተስፋ እንዳላትና ያን ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ገልጾ ነበር፡፡ለላል ይበላ የመብራት አገልግሎት ለማዳረስ የተገጠመው ጄኔሬተርም በነዳጅ አቅርቦት ምክንያት ረጅም ጊዜ ሳይሠራ ተቋርጧል፡፡ ይህች የዓለም ዓይን ማረፊያ የሆነች ከተማም ሕይወትን በጨለማ በርኖስ ውስጥ ተከባ መኖር ግድ ብሎባታል፡፡ እንግዶችን በማስተናገድ መልካም ሕይወት የለመደችው ላል ይበላ ዛሬ የለመደቻቸውን አጥታለች፡፡
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ኤርሚያስ መኮንን ቱሪዝሙ ከኮሮና ቫይረስ ወረረሽኝ ጀምሮ ፈተና ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በቱሪዝም ፕሮቶኮል አማካኝነት መነቃቃት ጀምሮ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ቢሮ ኀላፊው መልካም እንቅስቃሴ ላይ በነበረበት ወቅት የጦርነቱ መከሰት ቱሪዝሙን መልሶ እንዳዳከመው ነው የተናገሩት፡፡ ቁልፍ የሚባሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች በጦርነቱ ወቅት ሰለባ እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡
ላል ይበላ ሁልጊዜ እንግዳ የማታጣና ሕዝቡም ኑሮውን የሚመራው በቱሪዝም ሀብት ነው ያሉት አቶ ኤርሚያስ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ አካባቢው ቱሪስት ሸሽቶታል ነው ያሉት፡፡
በጎብኚዎች መቅረት ምክንያት ላል ይበላ ክፉኛ ተጎድታለችም ብለዋል፡፡
አካባቢው ከሽብር ቡድኑ ነጻ ከወጣ በኋላ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ የልደት በዓል በብሔራዊ ደረጃ በላል ይበላ እንዲከበር ሠፊ ሥራ መሠራቱንም አስታውሰዋል፡፡ በበዓሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ጎብኚዎች መገኛታቸውን አስገንዝበዋ፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ ኢንባሲዎች አንባሳደሮች በበዓሉ ተገኝተው መልእክት እንዲያስተላልፉና ለየወከሉት ሀገር ላል ይበላ ሰላም መሆኑን መልእክት እንዲያስተላልፉ ጥረት ተደርጎ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
ላል ይበላ በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት የመሠረተ ልማት መዘረፍና መውደም ክፉኛ ስለጎዳው ለቱሪዝም እንቅስቃሴው መዳከም የራሱ የሆነ ታላቅ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
ልደትን በላል ይበላ ማክበር ቱሪዝሙን ለማነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው ያስታወሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ትልልቅ ውይይቶች በላል ይበላ እንዲደረጉ በማድረግ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ የማድረግ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ኢንባሲዎች ዜጎቻቸው ወደ ላል ይበላ ቢሄዱ ሰላም እንደሆነ እንዲገልጹ የማድረግ ሥራ መጀመራቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ቱሪዝሙን ማነቃቃት እና ወደ አካባቢው እንዲንቀሳቀስ የማድረግ ሥራ መሠራት አለበት ብለን እየሠራን ነውም ብለዋል፡፡
በጦርነት ምክንያት የወደሙ የጎብኚዎች መዳረሻዎችን በጀት ይዘው እየጠገኑ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡ የላል ይበላ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ላይ የተደረሰው የመጠገን ሥራ ስምምነት በመልካም ሁኔታ እንዲሄድ በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የመብራትና የውኃ አገልግሎት እንዲኖር የሚመለከታቸው አካላት እንዲሠሩ ግፊት እያደረጉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
አስጎብኚዎችና ሌሎች በቱሪዝም ሀብት በቀጥታ ሕይወተቻውን የሚመሩ ዜጎችና ተቋማት የከፋ ችግር እንዳይደርስባቸው የመሻገሪያ መንገዶችን የማመቻቸት ሥራ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በመሆን እየሠሩ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሀገራዊ ጥሪ ከተደረገላቸው በኋላ መነቃቃት እንዳለም ገልጸዋል፡፡
የቱሪዝም እንቅስቃሴው በላል ይበላ እና በደባርቅ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ከፍ ያለ በመኾኑ በክልሉ አካባቢ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩንም ተናግረዋል፡፡ የቱሪዝሙን ጉዳይ የአማራ ክልል መንግሥት በትኩረት ከሚሠራባቸው አጀንዳዎችና አቅጣጫዎች መካከል አንደኛው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ጊዜ ያደከማቸውን ሕብስቶች፣ የሀገር በረከቶች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ፣ ደህንነታቸው ተጠብቆ የሀብት ምንጭ ኾነው እንዲቀጥሉ እርስዎስ ምን እያደረጉ ነው? አካቢዎቹ ሰላም መሆናቸውን መስክረዋል? ለዓለም አስተዋውቀዋል? ወይስ ዝም ብለው ተመልክተዋል? ሀገር የሚጠቀመው፣ ለሕዝብ የሚደረሰው በየፈርጁ ነውና በየፈርጁ መትጋት መሥራትን አይርሱ፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/