
ባሕር ዳር : ሚያዝያ 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሰሞነ ሕማማት ከሞት በኋላ ዘላለማዊ ሕይዎት፣ ከመከራ ሌሊቶች የሚቀዱ የፍስሃ ጅረቶች፣ ከስደት የሚወረስ ርስት፣ ከበደል የበረታ ይቅርታ እና ከመጥፋት ያዳነ አሸናፊነት የተቸረበት የፈተና ወቅት ነው፡፡
በሰሞነ ሕማማት ከክር የቀጠነችው የአዳም የመዳን ተስፋው በመጨረሻዋ ስዓት በደም የጸናችበት ወቅት ናት፡፡
ሰሞነ ሕማማት ዓለም የመከራዋ ዳርቻ እና የትንሳኤዋ ብርሃን ዋዜማ ሆናለች፡፡ ሰሞነ ሕማማት በክርስቶስ ክርስቲያን ለሆኑ ኹሉ ሰማይና ምድር፤ ፈጣሪና ፍጡር እርቅ ያወረዱበት፤ ጨለማ በብርሃን የተገለጠበት የይቅርታ እና የሽግግር ሰሞን ናት፡፡
ሰሞነ ሕማማት ፋሲካ የሚባለው የቂጣ በዓል መቅረብ ምልክት ነው፡፡ ሳምንቱ የመከራ፣ የስቃይ እና የጨለማ ሳምንት ቢኾንም በፈተና ለሚጸና የትንሳኤውን ብርሃን ከማየት ግን አያግድም፡፡
ሰሞነ ሕማማት በባሕሪው በደል የሌለበት ክርስቶስ ስለሰው ልጅ ፍቅር ሲል ያለበደሉ የተበደለበት ሳምንት ቢኾንም የጨለማን ጽልመት እና የመቃብርን ጉልበት ከመስበር ያገደው ኃይል ግን አልነበረም፡፡
ሰሞነ ሕማማት ግን የመከራ ሳምንት ብቻ አልነበረችም፡፡ በዚኽ ሳምንት ስለአዳም በደል ክርስቶስ ክሶ ዓለም የዳነበት ሳምንት ነው፡፡ የአዳም የእዳ ደብዳቤ ተቀድዶ ለ5 ሺህ 500 ዘመን በጨለማ ግዞት የወደቁ ኹሉ ነጻ ይወጡ ዘንድ ዋጋ የተከፈለባት የመጨረሻዋ ሳምንት ናት፡፡
አዎ! በሰሞነ ሕማማት ፍጻሜ ክርስቶስ መቃብርን ድል አድርጎ ተነሳ፤ በጨለማ የኖሩ ሕዝቦችም የሕይዎት ብርሃን ወጣላቸው፡፡
ክርስትናን ከብዙዎች ቀድማ የተቀበለችው ጥንታዊቷ እና አማናዊቷ ኢትዮጵያ በሕገ ልቦና እና በሕገ ኦሪት ቀደም ብላ ተመላልሳበታለች፡፡
በሕገ ወንጌል የጸናችው አኹናዊቷ ኢትዮጵያ ደግሞ ሰሞነ ሕማማት ላይ የምትገኝ ትመስላለች የሚሉት በርካቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የፈተና ብርታት እና ጽናት ሰሞነ ሕማማቷ ላይ እንደምትገኝ አመላካች ነውም ብለው ያምናሉ፡፡
ሕማማት የሚለው ቃል ሕመምን፣ ስቃይን፣ መከራን እና ችግርን የሚገልጽ ነው ያሉን የሥነ መለኮት መምሕሩ መጋቢ አሰፋ ዓይቸው ናቸው፡፡ ሰሞነ ሕማማት ማለት ደግሞ የኢየሩሳሌም ሰዎች “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው” እያሉ እና ዘንባባ እያነጠፉ በሆሳዕና የተቀበሉትን ክርስቶስን “ይሰቀል፣ ይሰቀል፣ ይሰቀል” እያሉ እስካሰቀሉበት ዕለተ አርብ ድረስ ያለውን የክርስቶስን ስቃይ፣ መከራ እና ሞት የሚያመላክት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
እንደ ሥነ መለኮት መምሕሩ ማብራሪያ የክርስቶስን መምጣት አጥብቀው ይጠብቁ የነበሩት አይሁዳውያን ጥበቃቸው የአዳምን በደል በደሙ ክሶ ሰማያዊ ነጻነትን የሚያወርሳቸው እና ከጨለማ የሚያሻግራቸውን ክርስቶስን አልነበረም፡፡ ከዚያ ይልቅ እስራኤላውያንን ከሮማውያን የቅኝ አገዛዝ ነጻ የሚያወጣቸውን ፖለቲካዊ መሲህ ነበር የሚጠብቁት፡፡ የጠበቁት መሲህ ዓላማው የጠፋውን የሰውን ልጅ ዋጋ ከፍሎ መመለስ እንጂ አንዱን በሌላው ላይ ማሠልጠን አለመኾኑን ሲረዱ ወንጀለኛው በርባን ተፈትቶ ወንጀል የሌለበት ኢየሱስ እዲሰቀል በጩኸት ጠየቁ፡፡
መጋቢ አሰፋ እንዳሉት አይሁዳውያን በዘንባባ ምንጣፍ የተቀበሉት እና በመከራ ብዛት የሸኙት ክርስቶስ እውነተኛ መሲህ እንደነበር ለማወቅ ክቡር ነፍሱ ከክቡር ስጋው እስክትለይ ዘግይተዋል፡፡ ነገር የጨለመባቸው እና የእውነተኛውን መሲህ መምጣት የሚጠብቁት ግን በሞቱ ነጻ ወጥተዋል፡፡
የሥነ መለኮት መምሕሩ እንደሚሉት ዛሬም በኢትዮጵያ ርሃብን፣ ጦርነትን፣ ስደትን፣ መፈናቀልን፣ መገፋትን እና መገደልን ስናስብ ሰሞነ ሕማማቷ ላይ እንዳለች እንረዳለን፡፡
ትናንት አብረዋት የቆሙት ይሸሻሉ፣ ቃል የገቡት ያብላሉ እንዲኹም የደከመች የሚመስላቸው ጦር ያነሳሉ፤ ነገር ግን ይላሉ መጋቢ አሰፋ ይህ ኹሉ ከመከራ በኋላ የሚመጣውን የኢትዮጵያን ትንሳኤ አያግዱትም፡፡
እንደ መጋቢ አሰፋ ማብራሪያ መቃብርን ፈንቅሎ እና ሞትን በሞቱ ድል አድርጎ የተነሳው ክርስቶስ ያሳደዱትን የሚያሳድድበት እና የበደሉትን የሚበቀልበት ኃይል ነበረው፡፡ ከዚያ ይልቅ የበደሉትን በይቅርታ እና በንስሃ ጠራቸው፡፡
ኢትዮጵያውያንም የኢትዮጵያን ትንሳኤ የሚያዩበት ወቅት ሩቅ አይደለምና አኹን ያለፈ ታሪካቸው፣ የቀደመ በደላቸው እና የጠገገ ቁስላቸውን የሚያስታውሱበት እና ለበቀል የሚነሱበት ጊዜ አይደለም፡፡
ከዚያ ይልቅ በጋራ ቆመው፣ በፍቅር ተቃቅፈው እና በይቅርታ ተሻግረው የተስፋ ሀገራቸውን ትንሳኤ ሊጠብቁ ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/