ʺጎለጎታን አስደንጋጭ ድምጽ አናወጻት፣ ዓለምን ብርሃን መላት”

220

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጨረቃ ቂሟን ረስታለች፣ ከዋክብት ሰማይን አስውበውታል፣ የጭንቅ ቀናት አልፈዋል፣ የዓለም መድኃኒት ከሙታን ተለይቶ ተነስቷል፣ ሕያው የሆነ አምላክ ከሙታን ጋር አይገኝም፣ መቃብሩን የከፈተው የለም፤ መግነዙንም የፈታው አልነበረም፣ ይልቁንስ የካህናት አለቆች ያስቀመጧቸው የመቃብር ጠባቂዎች በመቃብሩ ዙሪያ ነበሩ፡፡ መነሳቱን ግን አላዩም፡፡ የማየት አቅምም አልነበራቸውም፡፡ እርሱን መቃብር አያስቀረውም፣ መግነዝ አያስረውም፣ እርሱን ዓለም አይወስነውም፣ ዘመን አይቆጣጠረውም፡፡ በኀይሉ ሁሉን አደረገ፡፡

ዓለም በብርሃን ተመላች፣ እልልታን አደረሰች፣ ዝማሬውን አቀረበች፣ የሰማይ መላእክት ከምድር አሸዋ በዝተው ጌታን አመሰገኑት፣ በፊት በኋላው፣ በግራና በቀኙ ስለ ክብሩ ረበቡለት፣ የሰው ልጆች መሃሪና ይቅር ባይ ቸር አምላክ ኾይ ክብርና ምስጋና ለአንተ ይሁን እያሉ ምስጋና አቀረቡለት፡፡

ʺየምትሄዱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም
ጌታችን ተነስቷል በመቃብር የለም” ይሉታል፡፡ እርሱ በመቃብር የለም፣ መቃብሩ ባዶውን ቀርቷል፣ እርሱ ከሙታን ተለይቷል፡፡ እንደ እርሱ በኃይሉ ከመቃብር የተነሳ የለም፡፡ አልነበረም፡፡ ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ ከዋክብት ሰማዩን አደመቁት፣ ደም የለበሰችው ጨረቃ ቂሟን ረስታ፣ ፊቷን አፍክታ ማብራት ጀምራለች፡፡ ኢየሩሳሌምን ከወደ ጎለጎታ በኩል አስደንጋጭ ድምጽ አናወጻት፣ ብርሃን ከበባት፣ ክርስቶስ በራሱ ኃይልን ስልጣን ፈጥኖ ተነሳ፡፡ ምድር በብርሃን ተመላች፣ የማይጠፋውን ብርሃን አየች፡፡
ዓለም በብርሃን ተመላች፣ በቁራኝነት የነበሩት ነብሳት በደስታ ተመሉ፣ ተስፋ ያደረጉት፣ ለዘመናት የጠበቁት አምላከቸው አድኗቸዋልና ደስታቸው ወሰን አጣ፡፡

ከብርሃናት ሁሉ የበለጠ ብርሃን እያበራ ልብሰ መንግሥቱን ለብሱ መጣ፡፡ በተወለደ ጊዜ የድንግል ማርያምን ማሕተመ ድንግልና እንዳለወጠ ሁሉ፤ በትንሣኤውም ከሕቱም መቃብር መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፍቱልኝ ሳይል በመላእክት ታጅቦ በክብር ተነሳ፡፡

የሰቀሉት አፈሩ፣ ሰቀልነው፣ ገደልነው፣ ገድለንም ቀበርነው፣ በመቃብር አስረን እናስቀረዋለን ያሉት ሁሉ ደነገጡ፣ ራዱ፡፡ ኃያሉ አምላክ ተነስቷልና ግራው ገባቸው፣ አሁን አይዙትም፣ አሁን አይገርፉትም፣ አሁን አይወግሩትም፣ አሁን በጦር አይወጉትም፣ አሁን መራራ ሐሞት አያጠጡትም፣ አሁን መከራ አያበዙበትም፣ እርሱ ከሙታን ተለይቶ፣ መቃብሩን በኃይሉ ከፍቶ ተነስቷልና፡፡ ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር የነበሩት፣ ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ተባብረዋል፣ የገደሉት፣ ያስገደሉት፣ የወጉትና ያስወጉት አንገታቸውን ደፍተዋል፣ ዓለምን የፈጠረው፣ ከሁሉም በፊት የነበረው፣ ሁሉንም አሳልፎ የሚኖረው ኃያል ጌታ በኃያል ክብር በምድር ላይ አበራ፡፡

ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። እነሆ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። ጠባቂዎቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ሆኑ። መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱና ከሙታን ተነሣ፤ እነሆም ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። እነሆም ነገርኋችሁ። በፍርሃትና በታላቅ ደስታም ፈጥነው ከመቃብር ሄዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሊያወሩ ሮጡ። እነሆም ኢየሱስ አገኛቸውና ደስ ይበላችሁ አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ። አትፍሩ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ፤ በዚያም ያዩኛል አላቸው። ሲሄዱም ሳሉ እነሆ ከጠባቆቹ አንዳንድ ወደ ከተማ መጥተው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩ።
ጠባቂዎቹ እኛ ተኝተን ሳለ ደቀመዛሙርቱ መጥተው ሰረቁት በሉ እያሉ ማስወራት ጀመሩ፡፡ እነርሱ ግን እንደሚነሳም አስቀድመው አስበዋል፣ ለዚያም ነው ይጠብቁት ዘንድ የወደዱ፡፡ በጥበቃ ግን አላስቀሩትም፡፡ በኃይሉ መነሳቱንም አውቀዋል፣ ነገር ግን ክህደትን ባሕሪያቸው አድርገዋልና፣ ኃያልነቱን ላለመመስከር ስለፈለጉ ደቀመዛሙርቱ ወስደውት ነው ብለው ማስወራት ፈለጉ፡፡
ገዳዮቹ መድረሻው ጠፋባቸው፡፡ አፈሩ፣ አንገታቸውን ደፉ፡፡

የማይሆንላቸውን ነበርና ያደረጉት መሄጃ አጡ፡፡ መግደላዊት ማርያም እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም አለቻቸው። ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤ ዝቅም ብሎ ቢመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፤ ነገር ግን አልገባም። ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፣ ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ።

በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፣ አየም፣ አመነም፤ እነሆ ጌታ ተነስቷል፣ ምድርም በብርሃን ተሞልቷል፣ እልልታው በዝቷል፣ ምስጋናው ከፍ ብሏል፡፡ የመነሳቱን ብሥራት የሰሙት፣ እያለቀሱ የጠበቁት፣ እየጾሙና እየሰገዱ ትንሣኤውን የናፈቁት ክርስቲያኖች የጌታቸው መነሳት ብስራትን ሰምተዋልና፣ እልል እያሉ፣ በእጃቸው እያጨበጨቡ፣ እያሸበሸቡ እያመሰገኑት ነው፡፡

ጳጳሳቱ፣ ኤጵስ ቆጶሳቱ፣ ቀሳውስቱ፣ ዲያቆናቱ፣ መነኮሳቱ፣ ምዕምናኑ ሁሉም በየአብያተ ክርስቲያናቱና ገዳማቱ አጸድ ሥር ተጠልለው የመነሳቱን ነገር ሲያስቡ አድረዋል፣ በጌታ መነሳትም ምስጋናን አቅርበዋል፡፡ ምስጋና ለአንተ ይሁን እያሉ አቅርበዋል፣ እርሱም ተነስቷል፡፡

የትንሣኤው ብሥራት ተሰምቷል፡፡ በትንሣኤው ቀንም የትንሣኤውን ነገር እያሰቡ፣ እያመሰገኑት፣ በደስታና በእልልታ ይውላሉ፡፡ ጌታ ተነስቷልና፣ ሞት ተሸንፏል፣ ጌታ ተነስቷልና ሐዘን የለም፣ ጌታ ተነስቷልና መከራ የለም፣ ጌታ ተነስቷልና ለቅሶ የለም፡፡ ጌታ ተነስቷልና እልልታ፣ ሀሴት፣ ምስጋና ከፍ ይላል፡፡

ʺእነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” እንዳለ ጌታ ክርስቲያኖች የማይለያቸውን፣ የሚወዳቸውን፣ ከፍ ከፍም ያደረጋቸውን አምላካቸውን እያመሰገኑ ትንሣኤውን ያከብሩታል፡፡
መልካም የንትሣኤ በዓል፡፡

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት ከሦስት ሺህ በላይ የሕግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ ወሰነ።
Next articleሕማማቱ ግን የትንሳኤውን ብርሃን አያግዱትም !