
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ ለትንሣኤ በዓል ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል።
የዘንድሮውን የትንሣኤ በዓል የምናከብረው ዳገቱን ለመውጣት የበለጠ አቅም እና ፈተና በሚጠይቅበት፣ ያሳለፍነው ኀይላችን የሚመጣው ደግሞ ብርታታችን እና የድል ችቧችን መሆኑን በምናረጋግጥበት ጊዜ ላይ ሆነን ነው።
በአንድ በኩል በተስፋ የክልላችንን እና የሀገራችንን ትንሣኤ አሻግረን እያየን ፣ በሌላ በኩል ከፊታችን የተደረደሩ ፈተናዎች ከትንሣኤው እንዳያስቀሩን ከባድ ትግል እያደረግን የምናከብረው በመሆኑ ካለፉት በዓላት ለየት ያደረግዋል።
በእርግጥ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ጌታችን ስለ ሕማማቱ፣ ስለ ስቅለቱና ስለ ትንሣኤው ቀድሞ የነገራቸውን እውን ሆኖ እስኪያዩት ድረስ በታላቅ ተስፋና በከባድ ተጋድሎ ውስጥ ማለፋቸውን እናውቃለን።
አሁን ክልላችንና ሀገራችን የተጋረጡባቸውን የውስጥ ባንዳ እና የውጭ ወራሪ በከባድ ተጋድሎ መቀልበስ የቻልን ቢሆንም የሀገራችንን ትንሣኤ ለማብሰር አሁንም ተጨማሪ ትግሎች ከፊት ለፊት ይጠብቁናል። አዎን፤ ከሞት በኋላ ትንሣኤ እንደሚመጣ፣ ከስቃይ በኋላ ደስታ እንደሚከተል፣ ከጨለማ ወዲያ ብርሃን እንደሚፈነጥቅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ተምረን ለሀገራችን የለውጥ ሂደት መሳካት ተስፋ እንደሰነቅን የብርሃን ወጋጋኑ የሚታይበት የተራራው አናት ላይ ደርሰናል።
ስለሆነም ዛሬም ሽፍቶች በመንገዳችን ላይ አደጋ እየጣሉ ትንሣኤያችንን እንዳናይ የቻሉትን ያደርጋሉ፤ እያደረጉም ነው። ወገኖቻችንን እየገደሉ፣ ከመኖሪያ ቀያቸው እያፈናቀሉ፣ ሰይጣናዊ ተልእኳቸውን እየደጋገሙም ነው። በዚህም ወገባችን ዝሎ ከትንሣኤ ጉዟችን እንድንሰናከል ይፈልጋሉ።
ዳሩ ግን ምንም ያህል የሞት በትራቸውን ቢሰነዝሩብንም ድርጊታቸው የክፋታቸውን ጥግ ከመግለጥ ውጭ በዚያ መንገድ የሚያሳኩት አንድም ዓላማ የለም። ምክንያቱም የጀመርነዉ ትግል ቀራንዮን አልፎ መቃብሩን ፈንቅሎ እስከ ትንሣኤ ብርሐን እንደሚጓዝ በቅርቡ ይገባቸዋልና፡፡
ለጊዜው የፈተኑን ቢመስሉም በመጨረሻ ኢትዮጵያዊነት አሸንፎ የሀገራችን ትንሣኤ ይበሠራል። ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን ግፍ እና መከራ በወንድማማችነት ስሜት ታግለን ድል ስንነሳቸው ያኔ እነሱ ከትንሣኤው ብርሃን ፊት የመቆም አቅም እንዳይኖራቸው ሆነው ይወድቃሉ። በእነዚህ ቀናት ብዙ ነገሮች ይለዋወጣሉ፤ ከማንጠብቃቸው አቅጣጫዎች ጭምር ፈተናዎች ይመጣሉ።
በክርስቶስ ዙሪያ ካሉት አንዳንዶች ውልደቱና እድገቱን፣ ትምህርትና ተዓምራቱን፣ ግርፋትና ስቅለቱን እያዩ እስከ መጨረሻዋ ሰዓት በጽናት ቆይተዋል፤ ቁጥራቸው ጥቂት ያልሆኑ ሰዎች ደግሞ ሄደው ሄደው ከትንሣኤው በፊት ባለው አንድ ሳምንት ውስጥ ከማመን ወደ አለማመን፣ ከመከተል ወደ መሸሽ፣ አንድ ገበታ ከመቁረስ አሳልፎ እስከመስጠት በደረሱ የስሜትና የድርጊት ለውጦች ውስጥ አልፈዋል።
ከትንሣኤው ዕለት በፊት ያለችውን ልዩ ቀን የዕምነቱ ተከታዮች ‹ቀዳም ስዑር የተሻረች ቅዳሜ› ይሏታል። ይህቺ ዕለት አወዛጋቢ ዕለት ናት። አወዛጋቢ ያደረጋት ብዙ ነገሮች ግልጽ ያልሆኑባት ቀን በመሆኗ ነው።
ድል ያደረገው ማነው? አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነውን? ለሥልጣናቸው ሲሉ ፈርደው ለሮማውያን የሰጡት ሊቀ ካህናት ቀያፋና ሐና ናቸውን? ወይስ በእሥራኤል ላይ ያላቸው ጥቅም እንዳይነካ ሲሉ የሞት ፍርድ የፈረዱበት ሮማውያን ናቸው? ወይስ ሁሉም ተባብረው ለሞት ያበቁት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ያሸነፈው?
በይሁዳ ድርጊት ቀያፋና ሐና ስቀዋል፣ ሮማውያን ቀልደዋል። ይሁዳ የሠራው ነገር ስሕተት መሆኑን ዘግይቶ ቢናገርም በእነ ቀያፋና በሮማውያን ዘንድ ለውጥ አላመጣም። አልተፀፀቱም፤ አልተገረሙም።
ቅዳሜ እንዲህ ያለችው ቀን ነበረች። አወዛጋቢ ቀን። ደግሞም እጅግ ረዥም ጊዜ ነበረች። የመከራ ቀን ረዥም ነው እንደሚባለው። ሮማውያን የእሥራኤል ነገር አለቀ ብለው ደመደሙ። አይሁድ የወንጌል ነገር አበቃላት ብለው ፈጸሙ።
አማኞች ግን በሁለት ሐሳብ ተወጥረው ቀሩ። በአንድ በኩል በውዥንብር፣ በሌላ በኩል በተስፋ።
እምነታቸው ወደ ተስፋ እንዳይወስዳቸው ውዥንብሩ ይጠልፋቸዋል። ውዥንብሩ ጠልፎ እንዳያስቀራቸው እምነታቸው ተስፋ ይጭርባቸዋል።
ክልላችን አሁን ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ ከስቅለት በኋላ እና ከትንሣኤ በፊት ያለችውን ቅዳሜ ይመስላል። በውዥንብርና በተስፋ መካከል የምትዋዥቀውን ቅዳሜ።
በአንድ በኩል ሀገር ማጥፋት የሚፈልጉት ሮማውያን፣ የገዛ ሀገራቸውን ለጊዜያዊ ጥቅም ብለው ከሚያፈርሱት የአይሁድ ማኅበር ጋር ሆነው የፈጠሩት ግንባር አሸንፎ ይሆን? ተብሎ የሚገመትና ጥርጣሬ የሚያስገባ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በውስጡ ባለው እምነት ለመጽናት የሚጥር።
ቅዳሜ ከጠዋት ወደ ተሲዓት፣ ከተሲዓት ወደ ምሽት እየተራዘመ ሲሄድ እሑድ እስከመጨረሻው የቀረች መስላ ነበር። የሞት ቀን ሲረዝም የትንሣኤ ሌሊት መቼም የማይደርስ መስሎ ነበር። ግን እንደዚያ አልሆነም። ምን ቢረዝም ቅዳሜ ያልቃል፤ የሐሰት ጉም ምንም ያህል አየሩን ቢሞላው፣ የእውነት ፀሐይ ስትወጣ ይተናል። ክልላችን እና አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ከከበቧት መከራዎች፣ ግድያዎች፣ ውዥንብሮችና ጩኸቶች በላይ ናት፤ በእርግጥ እንደ ቀዳም ስዑር የውዥንብሩ ጊዜ የረዘመ መስሎ ይሰማል፤ ምን ቢረዝም ግን መጨረሻ አለው። ሳይጨርስ ይጨረሳል።
የይሁዳ የውስጥ ተንኮል፣ የነሊቀ ካህናት ቀያፋ የቡድን ሥራ፣ የሮማውያንም ሀገር የማፍረስ ዓላማ እሑድ እኩለ ሌሊት ብትንትኑ ወጣ። ክርስቶስ ሞትና መቃብርን ድል አድርጎ ሲነሣ፣ ታሪኩ ሁሉ ተቀየረ። ያለቀ የመሰለው ነገር ሁሉ እንደገና ተጀመረ። የተዘጋው መቃብር ተከፈተ፤ የተቆረጠው ተስፋ ተቀጠለ። አሸናፊዎቹ ተሸናፊ ሆኑ። የተዘጋው መቃብር፣ የታተመውም ማኅተም ከንቱ ሆኖ ቀረ።
ቅዳሜ ተሻረች። ስሟም ‹የተሻረችው ቅዳሜ› ተባለ።
የትንሣኤዋ እሑድ ግን ተሾመች። ቅዳሜ አበቃች። እሑድ ግን ይሄው እስከ ዛሬ እንደቀጠለች ናት። በየዓመቱም በድምቀትና በእልልታ እናከብራታለን።
የአገራችን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው። የተወሩት የሐሰት ወሬዎች ሁሉ እውነት ይመስላሉ። ያለነው ቅዳሜ ውስጥ ስለሆነ። ነገ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ሲሆን ግን እነዚህ አየሩን የሞሉት ወሬዎች ሁሉ ሐሰት መሆናቸውን ዓለም ሁሉ ያያል። የተፈጸሙብን ግፎችና፣ የተደረጉብን ስቅላቶች ሁሉ ኢትዮጵያን ለማቆም ያሰቡ መሆናቸውን ትውልድ ሁሉ በግልጥ ይረዳል።
ከፈተና በኋላ ድል እንዳለ አምነን ፈተናችንን ለማሸነፍ እና ካሰብነው የድል ማማ ለመድረስ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል፡፡ ድል ያለፈተና አይመጣም፤ ፈተናም ቢሆን በድል መቀየሩ አይቀርም፡፡ ይህ ዑደት የሚኖርና የሚቀጥል ቢሆንም ፈተናን በድል ለውጦ ውጤት ለማስመዝገብ ልዩ ጥበብ እና አስተውሎት ይጠይቃልና በዚህ መሰረት ለታላቁ ድል እንዘጋጅ።
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/