
ሚያዝያ 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሞትን የሚያሸንፈው፣ ሕይወትን የሚሰጠው፣ ኹሉን የሚያደርገው፣ ኹሉን የሚችለው፣ በፍጥረታት መካከል፣ በዓለማት ኹሉ በሚታየውም፣ በማይታየውም፣ በሚዳሰሰውም በማይዳሰሰውም፣ በታሰበውም፣ ባልታሰበውም፣ በተደረሰበትም ባልተደረሰበትም ውስጥ የሚገኘው አምላክ ስለ ፍቅር ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ ሞትን በሞቱ ሊሽር፣ አዳምን በገነት ሊያኖር፣ ሲኦልን ባዶዋን ሊያስቀር፣ የተጨነቁትን ሊደርስላቸው፣ ያዘኑትን ሊያጽናናቸው፣ ተስፋ ያደረጉትን እውን ኾኖ ሊያሳያቸው፣ ትንቢት የተናገሩትን ትንቢታቸውን ሊፈጽምላቸው፣ በጨለማ ያሉትን ብርሃን ሊሰጣቸው፣ እርሱ በመስቀል ላይ ዋለ፣ በመቃብር አደረ፡፡ ለወትሮው መግደያ ኾኖ ሳለ ክርስቶስ የሞተበት መስቀል ግን ድኅነት ኾነ፡፡ ክርስቲያኖች ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ኃይላችን፣ መዳኛችን እያሉ ይመኩበታል፡፡ ለምን ካሉ ድኅነትን አግኝተውበታልና፡፡
ግርማ መለኮቱን ችሎ የሚያየው፣ የኃያልነቱን ልክ የሚመረምረው፣ የመለኮትነቱን ብርሃን የሚችለው የለም፡፡ ከአባቱ ሳይወጣ መጣ፣ ከአኗኗሩ ሳይለይ ወረደ፣ ኮሦስትነቱ ሳይለይ መጣ፣ ከአንድነቱም ሳይለይ ወረደ፣ ከዙፋኑም ሳይለይ በስጋ ልጅ አደረ፣ ከምልዓቱ ሳይወሰን በማሕጸን ተጸነሰ፣ በላይ ሳይጎድል በማሕጸን ተወሰነ፣ በታችም ሳይጨመርበት ተወለደ እንዳለ ሊቁ እርሱ በማይመረመር ጥበቡ የማይመረመር ጥበብ አደረገ፡፡ ጌታን የሰቀሉት ደስታቸው እጥፍ ድርብ ኾኗል፡፡ በጌታ መሰቀል ልባቸው የተነካው እናቱ ማርያምና ሌሎች ቅዱሳን እንባቸውን እያፈሰሱ፣ አንጀታቸውን እያላወሱ እያለቀሱ ነው፡፡
በመንግሥትህ አስበን፣ ይቅርም በለን የሚሉት በዝተዋል፣ አዳኛቸውን የገደሉት፣ የሚነካው የሌለውን፣ መንካት ቀርቶ ማየት የማይቻለው አምላክ ሰው ኾኗልና ነገሥታቱ ገረፉት፣ አስገረፉት፣ አዳፉት፣ ገፉት፣ በምድር ላይ ጣሉት፣ በመስቀል ላይ ሰቀሉት፡፡ ፀሐይ ብርሃኗን የጋረደችባት፣ ጨረቃ ደም የለበሰችባት፣ ከዋክብት የረገፉባት፣ መጋራጃዎች የተቀደዱባት፣ ቀን የጨለመባት ዕለተ አርብ አለፈች፡፡ ያቺ መከራ የታየባት ቀን አልፋለች፡፡
የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ጌታን ከሰቀሉ በኋላ ወደቤታቸው ገብተዋል፡፡ በቤታቸው ግን ሰላም አላገኙም፣ ተጨነቁ፡፡ ንጹሕ ደም አፍስሰዋልና፣ የፍጥረታትን ኹሉ ፈጣሪ፣ መሃሪና ይቅር ባይ የኾነውን ጌታ ገድለዋልና ሲጨነቁ አድረዋል፡፡ ዕለተ ቅዳሜ ቀዳሚት ሰንበት ተተክታለች፡፡ ክፉ ሥራቸው፣ ክፉ መሃላቸው አላስቀምጥ አላቸው፡፡ በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ በሚኖረው ቀን የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና ጌታ ኾይ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትኾናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት። ጲላጦስም ጠባቆች አሉአችሁ፤ ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው። እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ። ጌታን ገድለው ጲላጦስን ጌታ አሉት፡፡ የጲላጦስን ፈጣሪ፣ የዓለምን ኹሉ ገዢ ሰቅለው አላፊውን ጲላጦስን ጌታ አሉት፡፡ የዓለምን ፈጣሪ ጌታን አዋርደው ሞቶ የሚቀረውን፣ ምድራዊውን ገዢ፣ ለዚያውም በጊዜ የተገደበውን ጌታ አሉት፡፡ እነርሱም እንደተባሉት አደረጉ፡፡ መቃብሩን ያስጠብቁ ዘንድ ወደዱ፡፡ አስጠበቁትም፡፡ የጌታ መቃብር እየተጠበቀ ነው፣ ረቂቁን ጠብቀው ሊያስቀሩት፣ በመቃብር ሊያኖሩት፣ ስጋውን አበስብሰው፣ አጥንቱን ከስክሰው፣ አፈር አድርገው ሊያስቀምጡት ምኞት ነበራቸውና እያስጠበቁት ነው፡፡
እርሱ ግን ከሐሳባቸውም፣ ከሕይወታቸውም ከምንም ምንም በላይ ነውና፣ ጠብቆ የሚያስቀረው፣ ኾኖለት በመቃብር የሚያኖረው አይገኝም፡፡ ቃሉን ሊፈጽም፣ የረከሰውን ሊቀድስ፣ የሰውን ልጅ ወደ ቀደመ ክብሩ ሊመለስ መጣ እንጂ ሞትስ በእርሱ ላይ አይሰለጥንም፣ ሞት ሕይወት በኾነ አምላክ፣ ሕይዎት በኾነ ጌታ ላይ አይኾንለትም፡፡ ይህችን ቀን አበው ቀዳሚት ስዑር፣ ቅዳም ሱር፣ ቅዳም ሹር ይሏታል፡፡ ትርጓሜዋንም ሞት የተሻረባት ማለት ነው ይላሉ፡፡ ለሰው ልጆች ሲባል ሞት የተሻረባት፣ ዲያብሎስ ድል የተነሳባት፡፡ ይህችም ቀን የክርስቶስን መነሳት የሚሹ ክርስቲያኖች አንዳንዶች ሐሙስ እንደተመገቡ፣ ሌሎች አርብ እንደተመገቡ እስከ ትንሣኤው ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው ሳይዞር የሚጸልዩባት፣ የሚማጸኑባት ናትና ከሌሎች ቅዳሜዎች ኹሉ ይህችኛዋ በጾም የሚታለፍባት ስለኾነች የተሻረች ቅዳሜ እያሉም ይጠሯታል፡፡ አይ እርሷስ አልተሻረችም የተሻረውስ ሞት ነው እንጂ፣ እርሷስ ተከበረች እንጂ አልተሻረችም ይላሉ፡፡
ቀዳሚት ዘብርሃንም ይሏታል፡፡ ሲኦልም የበረበረባት ቀንም ስለኾነች ቅድስት ቅዳሜ ይሏታል፡፡ ዕለተ አርምሞም ትባላለች ይህችው ዕለት፡፡ የብርሃንን ቀን ለማየት መዘጋጃ ናት፡፡ ለበዓለ ትንሣኤው ቀን ዝግጅት የሚደረግባት ናት፡፡ ይህችም ቀን የተከበረች ናት ይሏታል፡፡ ቀድሞ ዓለምን በመፍጠር በማረፍ አከበራት፣ አሁን ደግሞ የዓለም መድኃኒት በሞቱ ቀደሳት፣ ቀድሞ በጸጋው ባረካት፣ አሁን በመስቀሉ አተማት እያሉ ይጠሯታል፡፡ አብረው የሚያጠፉት፣ አብረው ለማልማት ይጣላሉ፣ አብረው ሐጢያት የሚሠሩት፣ አብረው ንስሃ ለመግባት ይፈራሉ፣ አብረው ክፉ ነገር ያደረጉት አብረው መልካም ነገር ለማድረግ ይፈራሉ፣ ይጣላሉ፣ አብረው መልካም የሚያደርጉት፣ አብረው ጽሞና ጸሎት የሚያበዙት፣ ለተጠማ የሚያጠጡት፣ ለተቸገረ የሚደርሱት፣ ለተራበ የሚያበሉት አብረው ወደ መልካሙ ሥፍራ ያቀናሉ፡፡
በትንሣኤው ዋዜማ በዕለተ ቅዳሜ ካሕናት ልብሰ ተክሕኗቸውን ለብሰው፣ በክብር ልብስ ተጎናጽፈው፣ ቃጭል እያሰሙ፣ ቄጤማ በእጃቸው ጨብጠው ወደ ምዕመናን በመሄድ ሐጢያት በክርስቶስ ደም ተደመሰሰ፣ የጥል ግድግዳ ፈረሰ እያሉ ቄጠማ ይሰጣሉ፡፡ ይህች ቀን ሞት የተሻረባት ዲያብሎስን ረግጦ የጣለበት ናት ይሏታል፡፡ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ፣ ሲኦልን ይበረብረው ዘንድ ወደ ሲኦል ወረደ፣ ሲኦል ከጌታ ጋር ፊት ለፊት ተገናኘች መረራትም፣ ከንቱ አድርጓታልና መረራት፣ ሽሯታልና መረራት፣ ነፍሳትን ይዛ እንዳታስቀር አድርጓታልና መረራት፣ ሩቅ ብእሲ አገኘሁ ብላ ዋጠችው ስትውጠው ግን እግዚአብሔር ኾኖ አገኘችው መረራት፣ ሞት ኾይ መውጊያህ ወዴት አለ? ሲኦል መቃብር ኾይ ድል መንሳትህ ፣ ይዞ ማስቀረትህ ወዴት አለ? ይላሉ አበው፡፡
ክርስቶስ በዕለተ ቅዳሜ፣ በቅዳም ሱር በአካለ ስጋ በከርሰ መቃብር፣ በአለላ ነብስ በሲኦል፣ ፍያታዊ ዘየማን ጋር ገነት፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በሰማያዊ መንግሥቱ በክብር ዙፋን ላይ ነበር ይላሉ፡፡ ሲኦልን በረበራት፣ በውስጧ የነበሩትን ነብሳት ወደ ገነት ወሰዳቸው፡፡ እነኾ ሲኦል ተጨነቀች፣ በግዞት የያዘቻቸውን ነብሳት ተነጠቀች፡፡ ሲኦል እርቃኗን ኾነች፡፡ ʺሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” እንዳለ መጽሐፍ እንደርሱ ኹሉ ለፍቅር፣ ለትህትና፣ ለአንድነት የተነሱ ኹሉ በአሸናፊነት ይነሳሉ፡፡ በድል አድራጊነት ይኖራሉ፡፡
መልካም በዓል
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J