
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የትንሣኤ በዓልን በተለያየ ምክንያት በሰላም ለማክበር እድል ላጡ ሁሉ ተስፋ በመኾን በጋራ ማክበር እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የዘንድሮው የትንሣኤ በዓል አከባበር አቅመ ደካሞችን በመደገፍ፣ የተፈናቀሉትን በመርዳት መኾን አለበት ነው ያሉት።
በርካታ ወገኖች ከነበሩበት ሕይወት ወጥተው በየሜዳው ስለወደቁ በዓሉ ሲከበርም የአልባሳት፣ የምግብና ሌሎችንም እርዳታ ማድረግ ከምእመኑ እንደሚጠበቅም ነው ያሳሰቡት።
ብፁእነታቸው “ከቤተክርስቲያን የተማርነውን ተግባራዊ ማድረግ አለብን” ብለዋል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ጭፈራና ደስታ ማድረግ ሳይኾን የመደጋገፍ፣ የመጾምና የመጸለይ ወቅት እንደኾነም መክረዋል። የተፈናቀሉትን በመደገፍና የተቸገሩትን በመርዳት፣ የታመሙትን በመጠየቅ፣ በማረሚያ ቤት የሚገኙትን በመጎብኘት በዓሉ በተለየ መልኩ መከበር እንደሚገባው ብፁእነታቸው አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሰሜን ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ዋና ጸሐፊ መጋቢ ገብሬ አሰፋ በኢትዮጵያም ኾነ በውጭ፣ በማረሚያ ቤትም ኾነ በተፈናቃዮች ካምፕ ለሚገኙ ወገኖች ሁሉ ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በትንሣኤ በዓል እውነተኛ ፍቅርን ይቅርታና ምሕረትን መማር፣ ያለን ለሌሎች ማካፈልን፣ የሌሎችን ደስታ ማብዛት ከእግዚአብሔር የሚወሰድ አብነት መኾኑን ባስተላለፉት መልእክት አስረድተዋል። “የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ መነሳት ለሰው ልጆች ያለው ፋይዳ በጣም ብዙ ነው፤ በእውነትና በቅንነት እንድንኖር፣ ክፋትና ምቀኝነትን፣ ግፍና ጥላቻን መገዳደልን፣ ሴራን በማስወገድ በጽድቅ እንድንኖር ነው” ብለዋል።
የትንሣኤ ቀን ከመብላትና ከመጠጣት በላይ መኾኑን ለአፍታም መዘንጋት እንደሌለበት መጋቢ ገብሬ አስገንዝበዋል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት የወገንን እገዛ ለሚፈልጉ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። አቅመ ደካሞችን፣ በማረሚያ ቤት የሚገኙትን፣ የታመሙትን፣ የተፈናቀሉትን በመጠየቅና በመደገፍ ይህን ቀን መሻገር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር-ደሴ ካቶሊካዊ ሰበካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ማቴዎስ ለመላው ዓለም የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ከምንጊዜውም በላይ መረዳዳት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የእለት ጉርስ የጎደለባቸው በርካታ ወገኖች ስላሉ ሲተርፍ ሳይኾን ያለን ማካፈል ሃይማኖታዊ ግዴታ እንደኾነ ነው ያሳሰቡት።
“እግዚአብሔር እንዲያዝንልን እርስ በእርሳችን መደጋገፍ ይጠበቅብናል። እኛ እርስ በእርሳችን ካልተደጋገፍን ማን ይደርስልናል? በመኾኑም አንዱ አንዱን ለመደገፍ ልዩነቶችን ወደ ጎን ማድረግ ያስፈልጋል። የበቀል መንፈስ ከእኛ መውጣት አለበት” ብለዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/