
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) እውነት እና ፍቅር ከአዕምሮ በላይ የሆነ ውድ ዋጋ ተከፍሎባቸው ዳኑ፡፡ የማያልፉ የሚመስሉት ሕማማተ ሌሊቶች በመለኮታዊ ጽናት የዶሮ ጩኽትን ተሻገሩ፡፡ ቀዳሚው አዳም በሁለተኛው አዳም ስቅላት እና ሞት ዘላለማዊ ሕይዎትን አገኘ፡፡
ከሮማዊያን ባርነት እና ግዛት ነጻ የሚያወጣቸውን ፖለቲካዊ መሲህ የሚጠብቁት እስራኤላዊያን ዘ-ስጋ ዳግም በድለው እንኳን በደሙ ከሃጢያት ባርነት ለዘላለሙ ነጻ የሚያወጣቸው እስራኤላዊ ዘ-ነፍስ አገኙ፡፡ በሃጢያት የጠፋችው ዓለም በምህረቱ እና በቸርነቱ ዳነች፡፡ ሕግ ሥለመተላለፉ ሞት የተፈረደበት ቀዳሚው አዳም ሕግን በደሙ ባጸናው ሁለተኛው አዳም ነጻ ወጣ፡፡
ምህረቱ ፍጹም፣ ይቅርታው ዘላለማዊ፣ ርህራሄው የእውነት፣ አባትነቱ የሁሉም እና አዳኝነቱ ለሁሉም የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ በፍቅር እና በትህትና ዝቅ ብሎ ዓለምን ዳግም ወደ ከፍታዋ መለሳት፡፡
በእስትንፋሱ የተፈጠረችው ዓለም በደሙ ከዘላለማዊ ሞት አርነት ወጣች፡፡ የክርስቶስ ስቅላቱ፣ ሞቱ እና ትንሣኤው እንደ ውኃ ፈሳሽ፤ እንደ አደጋ ደራሽ አልነበሩምና ለአዳም የተገባለት ቃል አንድም ሳይጎድል ተፈጸመ፡፡ ይህንን ማድረግ ከቶውንስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ውጭ ማን ይችል ነበር፡፡
በልደቱ ንጉስ ተወልዷል፤ አለቅነትም በጫንቃው ነውና ደስ ይበላችሁ የተባለላቸው በክርስቶስ ክርስቲያን፣ በወልድ ውሉድ እና በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊያን የሆኑ ሁሉ በስቅላቱ እና ሞቱ የእዳ ደብዳቤያቸው ተቀደደ፡፡
የሃጢያት ውኃ ጎድሎ የጽድቅ ውኃ በክርስቶስ ደምና ስጋ ዳግም መሙላቱን ለማብሰር “በለምለሟ ቅዳሜ” ካህናት በጠዋት ቄጠማ ይዘው ይዞራሉ፡፡ ቄጠማውንም ለምእመናኑ እያቀበሉ “ጌታችን ተመረመረ ዳቢሎስ ታሰረ” ሲሉ ያበስሯቸዋል፡፡ ቄጠማውም እስከ ትንሣኤው ሌሊት ድረስ ከምዕመናኑ ጭንቅላት ላይ ታስሮ ይውላል፡፡
በቀራኒዮ ስቅላቱ የተከፈቱት መካነ መቃብሮች እንደ አዲስ በጎለጎታ ንጉሳቸውን በከፈን ተቀበሉ፡፡ ግን የጎለጎታ መካነ መቃብር ይህንን መለኮታዊ ኅይል ያለውን የክርስቶስ ስጋ 5 ሺህ 500 ዘመን ቀርቶ 5 ቀን እንኳን የመሸከም አቅም አልነበረውም፡፡
በሦስት መዐልት እና በሦስት ሌሊት ክርስቶስ በፈቃዱ ነፍሱን ከስጋው እንደለየ ሁሉ፣ መግነዝ ፍቱልኝ የመቃብር ድንጋይ ፈንቅሉልኝ ሳይል በኃይል እንደሚነሳ እውን ሆነ፡፡
የማትጾመው ቅዳሜ ንጉሷ በመቃብር ውስጥ አድሯልና ኦሪትን ሽራ ሐዲስን አሃዱ ማለቷን ተከትሎ “ቅዳሜ ስዑር” ተባለች፡፡ በዚች እለት የክርስቶስን መከራ የሚያስቡት ክርስቲያኖች ከወትሮው በተለየ በጾም ያሳልፏታልና “የተሻረችው ቅዳሜ” ሲሉም ይጠሯታል፡፡
ይህች ቅዳሜ “ቅዱስ ቅዳሜ” የሚል ስያሜም አላት፡፡ በሥጋ መካነ መቃብር ውስጥ ቢያርፍባትም፤ በነፋሱ ግን ለ5 ሺህ 500 ዘመን የተጋዙ ነፍሶችን በርብሮ በማውጣት ሲኦልን ባዶ አድርጎባታልና፡፡ በዚያ የነበሩ ሁሉ የዘላለም ሕይዎት ስለታደላቸውም ቅድስት ቅዳሜ ሲሉ ይጠሯታል፡፡ እንግዲህ የሚቀረው ነገር ቢኖር “እግዚአብሔር ይነሣል ጠላቶቹም ይበተናሉ” እንዳለ መጽሐፍ ትንሣኤውን ማየት ነውና መልካም ትንሣዔ ብለናል፡፡
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/