
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጊዜ የማይቆጠርለት፣ ዘመን የማይበጅለት፣ ወሰን የማይወሰንልት፣ በዘመኑ ሽረት የሌለበት ኃያል አምላክ ዓለምን ያድን ዘንድ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ ተበድሎ የካሰ፣ ካሳ ሲገባው ደሙን ያፈሰሰ፣ ስጋውን የቆረሰ፣ መራራ ሀሞትን የቀመሰ፣ ልብሱ ብርሃናት ኾኖ ሳለ የመዘባባቻ ልብስ የለበሰ ከእርሱ ውጭ ማን አለ? የነቢያት ትንቢታቸው፣ የአዳምና የሔዋን ተስፋቸው፣ የፍጥረታት ሁሉ ጌታቸው፣ አዳኝና ጠባቂያቸው፡፡
ቀዳማዊ፣ ማዕከላዊ፣ ዳሕራዊ አልፋና ዖሜጋ የሆነ፣ ነፋሳት ሳይነፍሱ፣ ቀላያት ሳይፈስሱ፣ ብርሃናት ሳይመላለሱ፣ ሰማይና ምድር ሳይጸኑ፣ መላዕክት ለአገልግሎት ሳይፋጠኑ ከሁሉ አስቀድሞ የነበረ፣ በማይመረመር ጥበቡ ዓለምን የፈጠረ፣ ካለመኖር ወደ መኖር የቀየረ፣ ፍጥረታትን ሁሉ የሚያስብ፣ የሚመግብ፣ የሚሰበስብ፣ ጥላና ከለላ የሚሆናቸው፣ የልባቸውን መሻት የሚያውቅላቸው፣ የሚፈጽምላቸው፣ ዓለማትን በማይዳሰስ ጥበቡ የሚዳስሳቸው፣ በቅዱስ መንፈሱ የሚሞላቸው፣ በኃያልነቱ የሚገዛቸው አምላክ፡፡ ከነባቢት ነብስና፣ ከመዋቲ ስጋ ፣ ከተሰወረውና ከተገለጸው፣ በላይና በታች ካለው፣ ከሚዳሰሰው እና ከማይዳሰሰው አስቀድሞ ነበረ፡፡
ሁሉን አድራጊ፣ ሁሉንም አዋቂ፣ ሁሉን ቻይ፣ የትም የሚገኝ አምላክ ኃያልነቱን ያደንቁታል እንጂ አይመረምሩትም፣ ያመሰግኑታል እንጂ አይሟገቱትም፣ ሥራው እጹብ ድንቅ ነው፣ ባሕሪው ቸርና አዳኝ ነው፣ ለሚፈሩት ምህረቱ ለልጅ ልጅ ነው፣ እርሱ በሰጣቸው አንደበት አሜን የሚሉት፣ ተመስገን እያሉ የሚያመሰግኑት፣ አድርጉ ያላቸውን የሚያደርጉት፣ አድርጉ ያላላቸውን የማያደርጉት፣ ከሕጉ የማይወጡት፣ ትዕዛዛቱን የሚያከብሩት ያዘጋጀላቸውን መንግሥት ይወርሱታል፣
አበው እርሱ ወደታች የማይመረምሩት ጥልቅ፣ ወደ ላይ የማይደርሱበት ሩቅ፣ የማይጨብጡት ረቂቅ፣ በባሕሪው ሞት፣ በመንግሥቱ ሽረት የሌለበት፣ የሰላማችን፣ የሕይዎታችን ራስ፣ የመከበሪያችን ረቂቅ ልብስ ይሉታል፡፡
ለተራበው ዓለም የሚጠግብበትን ሕብስት ያፈራለችለት፣ ለደከመው ዓለም ምርኩዙን ያበቀለችለት፣ በሐጥያት ለከረፋው ዓለም ማዕዛ ክርስቶስን የወለደችለት፣ ለጨለመው ዓለም ብርሃንን የሰጠችው ፀሐይ ያወጣችለት፣ ምሥራቀ ምሥራቃት የሆነች እመቤት ይሏታል እናቱን ማርያምን፡፡
እርሱ ፍጥረታትን ከፈጠረበት፣ ምድርንና ሰማይን ካስዋበበት ጥበቡ ይልቅ ሰው ኾኖ፣ ሞቶ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ እጅግ ይልቃል ይላሉ አበው፡፡ ለምን ካሉ የማይሞተው ሞቷልና፤ ሞትን ድል ይነሳ ዘንድ ሞቷልና፡፡ በደል ያልተገኘበት፣ ንጹሕና ቸር አምላክ የአዳምን እዳ በደል ሊሽር ወደ ምድር ጊዜ በመጣ በምድራውያን ነገሥታት ተጠላ፡፡ ገፉት አዳፉት፡፡ መከራም አበዙበት፡፡ ራሱንም አሳልፎ ሰጠ፡፡
ክርስቶስ መከራ የሚቀበልበት፣ በቀራንዮ አደባባይ ሞቶ ሞትን ድል የሚነሳበት ዕለተ አርብ ደረሰች፡፡ መላእክት በፍርሃትና በምስጋና የሚሰግዱለትን መከራ አበዙበት፡፡ እርሱ ግን የሚሆነውን አስቀድሞ ያውቃልና የሚሆነውን እያሰበ ዝም አለ፡፡ የኢየሱስን ትህትና እና ትዕግሥት ያዩት አበው ይሔን ያህል ትሕትና እንደምን ያለ ትሕትና ነው፣ ይሔን ያህል ትዕግሥት እንደምን ያለ ትዕግስት ነው፣ ይሔን ያህል ዝምታ እንደምን ያለ ዝምታ ነው፣ ይሔን ያህል ቸርነት እንደምን ያለ ቸርነት ነው፣ ይሔን ያህል ሰውን ማፍቀር እንደምን ያለ ፍቅር ነው እያሉ ያመሰግኑታል፡፡
የእርሱ ሞት ብርሃን ገለጠ፣ የእርሱ ሞት ሕይወት ሰጠ፡፡ በቀራንዮ ተፈጸመ አለ፡፡ የአዳም የመከራ ዘመን ተፈጽሟልና፡፡ ቃሉንም ፈጽሟልና፣ እርሱ ሞትን ድል አድርጎ የሚነሳ ነውና፡፡ ከርሰ መቃብር ይዞ አላስቀረውም፣ መግነዝም አስሮ አልያዘውም በፈቃዱ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ በኃይሉ ከሙታን ተለይቶ ተነሳ፡፡ በዚህ ቀን ደስታ ኾነ፡፡ ክብረ መንግሥቱን ለብሶ ተነሳ፡፡ ክርስቲያኖች የኃያል አምላካቸውን ሞትና ትንሣኤ ያስባሉ፡፡ እነሆ ሕማመቱን እያሰቡ ነው፡፡ ትንሣኤውንም እየጠበቁ ነው፡፡
በዕለተ አርብ፣ በስቀለቱ ቀን ያለቀሱት በዕለተ እሁድ በትንሣኤው ቀን ይደሰታሉ፣ ይስቃሉ፣ ጌታ ሲነሳ ደስታ አለና፣ ጌታ ሲነሳ በረከት ሞልቷልና፣ ጌታ ሲነሳ በደል ተሸሯልና፣ ጌታ ሲነሳ የመዳን ቀን መጥቷልና፡፡ ጌታ ሲነሳ፣ አዳም ነጻ ወጥቷልና፣ ጌታ ሲነሳ የጨለመው ዓለም በብርሃን ተመልቷልና፡፡ እነሆ ሕማሙ እየታሰበ፣ የትንሳኤው ቀን እየተጠበቀ ነው፡፡ ክርስቲያኖች ትንሳኤው የሚታሰብበትን፣ ብርሃን በዓለም የበራበትን ቀን እየጠበቁት ነው፡፡
በትንሣኤው ቀን ልጆች ከወላጆቻቸው፣ ወላጆች ከልጆቻቸው፣ ጉረቤት ከጎረቤቱ ጋር በደስታ ያከብራሉ፡፡ በዚያ ቀን ያዘኑት ይደሰታሉ፣ የተራቡት ይጠግባሉ፣ የተጠሙት ይረካሉ፣ የታረዙት ይለብሳሉ፡፡ በዚያን ቀን ደስታ ይሆናል፡፡
በትንሣኤው ቀን መከፋት የለም፡፡ በትንሣኤው ቀን ማዘን እና መቆዘም የለም፡፡ ይሁንና በትንሣኤው ቀን ቤት የሌላቸው፣ ሀብትና ንብረታቸው ከእጃቸው የተወሰደባቸው፣ መደሰትን ይሹ የነበሩት፣ ከልጆቻቸው ጋር የሚያከብሩት ሀዘን ሊገባቸው ነው፡፡ የትንሳኤው ቀን በሚታሰብበት በዚህ ሰሞን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው፣ በመጠለያ ውስጥ የሚኖሩ እልፍ ወገኖች አሉና፡፡ ሀዘን በማይታወቅበት ቀን ሊያዝኑ ነው፣ ለቅሶ በማይገባበት ቀን ሊያለቅሱ ነወ፡፡ በትንሳኤው ቀን ከጤፍ እንጀራ ላይ የሚያፈስሱት እርጎ እየናፈቃቸው፣ በትንሳኤው ቀን የሚቆርጡት ጮማ ውል እያላቸው፣ የሚቆርሱት ዳቦ እየታወሳቸው፣ የሚጠጡት ጠጅና ጠላ ማዕዛው እየጠራቸው፣ ቤትና ማዕረጋቸው እየወዘወዛቸው በዓመት በዓል የሰው እጅ እያዩ ሊያከብሩ ነውና አቤቱ ደስታችን መልስልን፣ ቤታችን አጽናልን እያሉ ነው፡፡
መልካሙ ጊዜ እየታወሳቸው፣ በበዓለ ትንሣኤ የሚያደርጉት ሁሉ እየመጣባቸው ሀዘን ገብቷቸዋል፡፡ እናንተ መስጠት የተቸራችሁ፣ ደግነት የበዛላችሁ ኢትዮጵያውያን ሆይ
በበዓለ ትንሣኤ እንዳያለቅሱ፣ የተቸገሩት ወደ አሉበት ገስግሱ። የተፈናቀሉት፣ ሀብትና ንብረታቸውን የተዘረፉት ብቻ ሳይሆኑ በየቦታው የተቸገሩ፣ ጦም ውለው ጦም የሚያድሩ አሉና አስቧቸው፣ በትንሣኤው ቀን እንዳይቸገሩ፣ መልካሙን ቀን እያሰቡ እንዳያለቅሱ እጃችሁን ዘርጉላቸው፣ ደግፏቸው፣ አለሁ በሏቸው፡፡
“በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው።ʺ እንዳለ መጽሐፍ መስጠት የሚገባበት፣ የተወደደው ቀን አሁን ነው፡፡ መልካሙን ነገር አድርጎ መልካሙን የመቀበልና የመዳን ቀንም አሁን ነውና፣ በተወደደች ቀን ተከፍተው እንዳይውሉ፣ እንዳያዝኑ የተወደደውን ሥራ እናድርግ፡፡ መዳንና ደስታ ይመጣ ዘንድ በተወደደችው ቀን ከተቸገሩት ጋር እናክብር፡፡
“ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።” እንዳለ ሁሉም ድሆችን ባለጠጎች እናድርግ፣ የተከፉትን እናጽናና፣ የታረዙትን እናልብስ፣ የተራቡትን እናጉርስ፡፡
ዘወትር ለመደሰት፣ በዘመን ሁሉ ለመርካት፣ በረከተና ረድኤል ለመቀበል በታላቁ ቀን ታላቅ ነገርን እናድርግ፡፡ ሰማይና ምድር በሚደሰቱበት ቀን ያዘኑትን እናስደስት፡፡ ለተቸገሩት እንድረስ፡፡ በዓለ ትንሣኤው የሚታሰበው ኃያሉ ጌታ የታረዙትን አልብሱ፣ የተራቡትን አጉርሱ ብሏልና ያለውን ለመፈጸም፣ ቃሉንም ለማክበር ተፋጠኑ፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/