
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል አገልግሎት በ20 ሄክታር መሬት ላይ በሶስት ተከታታይ ምዕራፍ እንዲገነባ እቅድ ተይዞለት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ከሶስት ዓመታት በፊት ነው። የመጀመሪያው ዙር ግንባታ 100 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት በአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ተቋራጭነት ተሠርቶ በ2012 ዓ.ም ሥራ ጀምሯል። ወደቡ በኢትዮጵያ ስምንተኛው የወደብ አገልግሎት ሲኾን በአማራ ክልል ደግሞ ከመተማና ከኮምቦልቻ ቀጥሎ ሶስተኛው ነው።
ከወደብና ተርሚናሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው አጠቃላይ ከታቀደው 20 ሄክታር መሬት ውስጥ በመጀመሪያው ዙር 2 ነጥብ 35 ሄክታሩ ብቻ ነው የለማው። የወለል ንጣፉም በአፈር የተሠራ ነው። ከለማው የወደቡ ክፍል ውስጥ 1 ነጥብ 75 ሄክታሩ ለኮንቴነር ማስተናገጃ የሚውል ሲኾን ቀሪው ግማሽ ሄክታር ላይ ደግሞ ቢሮዎችና የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ሕንፃዎች አርፈውበታል።
የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ተስፉየ አያሌው እንደገለጹት ወደቡ ሥራ መጀመሩ ለአካባቢውና ለክልሉ የኢኮኖሚ መነቃቃት ፈጥሯል። በተለይም ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ላይ የሚገኙ አስመጭና ላኪዎች አዲስ አበባና ሞጆ ድረስ በመሄድ ይደርስባቸው የነበረውን የጊዜና የገንዘብ ብክነት የሚቀንስ እንደኾነ ተናግረዋል።
ገቢና ወጭ እቃዎችን በማሳለጥም ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ሥራ የበኩሉን እያበረከተ ነው። እንደ አቶ ተስፋየ ገለፃ ወደቡ በ2013 ዓ.ም በዘጠኝ ወር ውስጥ 6ሺህ 897 ገቢና ወጭ ኮንቴነሮችን አስተናግዷል። ይህም ከፍተኛ መጠን ያለው ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ በተለይም የመጋዝን ጥበት መኖሩ የደንበኞች የቅሬታ ምንጭ እንደነበር ተናግረዋል።
በ2014 የበጀት ዓመት 1ሺህ 520 ኮንቴነሮችን ያስተናገደ ሲኾን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ዘጠኝ ወራት ጋር ሲነጻጸር የ74 በመቶ ቅናሽ መኖሩን አቶ ተስፉየ ተናግረዋል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከሚሌ -ጭፍራ – ወልዲያ የሚያደርሱ መንገዶች በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የተወረሩ መኾናቸው ነው ብለዋል። አካባቢው ከወረራ ነፃ ከወጣ በኋላም አሸባሪ ቡድኑ በጨረቲ ወንዝ ድልድይ ላይ ጉዳት በማድረሱ መንገዱ ለትራፊክ ዝግ እንደነበርና የሚስተናገዱ ኮንቴነሮችም በአዲስ አበባ በኩል ዞረው በከፍተኛ ወጭ ይመጡ እንደነበር ተናግረዋል።
ሥራ አስኪያጁ አሁን ላይ የጨረቲ ድልድይ ተጠግኖ ለትራፊክ ክፍት ስለኾነ በዚሁ የጉዞ መስመር የሚመጡ ኮንቴነሮችን መቀበል እንደጀመሩም አስገንዝበዋል።
ተገንብቶ ወደ ሥራ የገባው የደረቅ ወደቡ የመጀመሪያው ዙር የሥራ እንቅስቃሴ ጥሩ እንደነበር የገለጡት አቶ ተስፉየ “ሁለተኛ ዙር ግንባታውን ለማስቀጠልም በጀት ተይዞለታል” ብለዋል።
በዚህ ዓመት ይጀመራል የተባለው የማስፋፊያ ግንባታ:-
✍️20ሺህ 635 ሜትር ኪዩብ የኮንቴነር መቀመጫ
✍️6ሺህ 800 ሜትር ስኩየር የፍተሻ ቦታ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ 12 የሚሆኑ የጥበቃ ማማዎች
✍️3 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የዙሪያ አጥር እና ሙቀት እና እርጥበት የሚያጠቃቸው እቃዎች የሚቀመጡበት ሰፊ መጋዘን አካቶ የሚገነባ ነው ብለዋል።
ከታቀደው 20 ሄክታር መሬት ውስጥ ገና ያልለማው 17 ነጥብ 65 ሄክታር መሬት ሙሉ በሙሉ ካሳ የተከፈለበት ነው ያሉት አቶ ተስፋየ አሁንም ድረስ ገና በቦታው ላይ የሚኖሩ አርሶ አደሮች እንዳሉ ጠቁመዋል።
“ወሰን የማስከበር ሥራው እንዲጠናቀቅ እስከ ክልል መስተዳድር በተጠየቀው ጥያቄ መሰረት ለልማት ተነሽዎች አስፈላጊውን ትክ ቦታ ተሰጥተው በቅርብ እንዲነሡ ስምምነት ላይ ተደርሷል” ሲሉም አቶ ተስፉየ ገልጸዋል።
ሁለተኛ ዙር ግንባታውንም በተያዘው የ2014 በጀት ዓመት ለመጀመር የማስተር ፕላንና የአዋጭነት ጥናቱ ተጠናቅቆ የግንባታ ጨረታ ሂደት ላይ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል አገልግሎት አሁን ባለበት ሁኔታ ለ50 ሠራተኞች ቀጥተኛ የሥራ እድል ፈጥሯል። ቀጥተኛ ባልኾነ መልኩ ደግሞ በርካታ ወጣቶች ከደረቅ ወደቡ ጋር ተያይዘው ከመጡ የኢኮኖሚ መነቃቃቶች ተጠቃሚ ናቸው ብለዋል አቶ ተስፉየ። ከዚህ በተጨማሪም ደረቅ ወደቡ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን በመወጣት ረገድ ሰፊ እንቅስቃሴ ያደርጋል ያሉ ሲኾን ለአብነትም በሰባት ሚሊዮን ብር ወጭ የንፁህ መጠጥ ውኃ ለአካባቢው ነዋሪዎች እየቀረበ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ወጣት ሙሉቀን ታደሰ በወደቡ የጥበቃ ባለሙያ ሲኾን በመኖሪያ አካባቢው ስለተፈጠረለት የሥራ እድል ሲያጫውተን “እኔን እና ሌሎች ወጣቶች በቤተሰቦቻችን አቅራቢያ ሥራ አግኝተናል፤ ሻይ እና ቡና የሚሸጡ እህቶቻችንም ጥሩ ገበያ አግኝተዋል” ብሏል። ሌሎች ያነጋገርናቸው ሰራተኞችም በቀጥተኛ ቅጥር በወደቡ ከሚሠሩት ወጣቶች በላይ ቀጥተኛ ባልኾነ መንገድ ከወደቡ የኢኮኖሚ ጥቅም የሚያገኙ ሰወች ብዙ እንደኾኑ አስረድተዋል።
የወደቡ ሁለተኛ ዙር ግንባታ ሲጀመርም ለአካባቢው፣ ለክልሉና ለሀገር ተጨማሪ የሥራ እድልና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ እንዳላቸው ሠራተኞች ነግረውናል፡፡
ዘጋቢ፡-አሚናዳብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/