
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የቆየው ሥርዓት ተወግዶ አዲሱ ሥርዓት ይተካ ዘንድ ከሰሞነ ሕማማት ዕለተ ሐሙስ ተመራጭ ኾና ተገኘች፡፡ በዚህች እለት እግዚያብሔር ወልድ ከአሮጌው ብሉ ኪዳን ወደ ሐዲሱ ኪዳን የሰው ልጆች ይሸጋገሩ ዘንድ ሥርዓት የሠራበት ዕለት ነው፡፡ የሰው ልጆች ዝቅ ማለትን፤ አንዱ ለሌላው ዝቅ ብሎ እግሩን እስከማጠብ የደረሰ ትህትና እንዲያሳይ አብነት የተጣለበት እለትም ነው።
ጸሎተ ሐሙስ ከሰሞነ ሕማማት ቀናት የምትለይበት እግኢያብሔር ወልድ በጌቴ ሰማኔ በአትክልት ሥፍራ ጸሎት በማድረግ ተከታዮቹ እንዲሁ እንዲያደርጉ ያስተማረበት ዕለት በመኾኗም ነው፡፡ ይህች ዕለት የተለያዩ ምስጢራትም ተከናውነውባታል፡፡
የምስጢር ሐሙስ እየተባለች የምትጠራው ይህች ዕለት ሥርዓተ ቁርባን የተፈጸመባት ልዩ ቀንም ናት፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 26 ከቁጥር 26 ላይ እንደሚያትተው ከብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን ሽግግር የተደረገባት እለት መኾኗን ገልጾ እለቷ የሐዲስ ኪዳን ሳምንት ተብላ እንደምትጠራ ያስረዳል፡፡
እግዚአብሔር ወልድ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን እራት የበላባት በመኾኗም ከሐዲስ ኪዳን ቀናት ልዩ ዕለት እንደኾነች ነው የሚገለጸው፡፡ ‟ክርስቶስ ሐጸበ እግረ ሐዋሪያቲሁ” ይላሉ ሊቃውንቱ እግዚያብሔር ወልድ ፍጹም ትህትናውን ለማሳየት የሐዋርያትን እግር በማጠብ ዝቅ ብሎ ከፍ ማለትን፣ ነፃነትን ያወጀባት ዕለትም ናት ጸሎተ ሐሙስ፡፡
በዚህች ዕለት ጸሎተ አኩቴት ተጸልዮ እና ወንጌል ተነቦ በዚህች የእግዚአብሔር ወልድ እግር ማጠቡ ተምሳሌት ተደርጎ ይከናወናል፡፡ በዚህ እጥበት ታዲያ ከውኃ በተጨማሪ የወይራ እና የወይን ቅጠል ግልጋሎት ላይ ይውላሉ፡፡
እግዚአብሔር ወልድ የሰው ልጆችን ነፃነት ለማወጅ ጽኑ መከራን መቀበሉ በወይራ ቅጠሉ ሲመሰል፤ ደሙን አፍስሶ ባሪያ የነበረውን የሰው ልጅ በደሙ ነጻ ማድረጉን በወይን ቅጠሉ ይመሰላል፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ደቀመዛሙርቶቹን እራት ባበላበት በዚህች ዕለት እነኾ ስለናንተ የሚሰጠው ስጋየ፤ እነኾ ስለናንተ የሚፈሰው ደሜ ብሎ ከህብስቱ እና ከወይኑ ይቃመሱ ዘንድ ያደለበት እና እነሱም እንዲሁ ሥርዓት ሠርተው ይከውኑ ዘንድ በዚህች ዕለት እንዳዘዛቸው ቅዱስ መጽሐፍ ያትታል፡፡
መሪው ክርስቶስ ከበጎቹ እንደ ታናሹ በመኾን ሲያገለግላቸው እና ዝቅ ብሎ ከፍ ማለትን ሲያስተምራቸው እነሱም ይህንኑ ሲተገብሩ ዘመናት አልፈዋል፡፡ ይህ ሥርዓት በባሕላዊው መንገድ ሲቀየርም በየአንዳንዱ ቤት ጉልባን እና ዳቦ ሰርቶ የሚጠጣውን አዘጋጅቶ እንዲሁ ሲደረግ ይስተዋላል፡፡ ጎረቤት እና ቤተዘመድ ተጠራርተው በመብላት እና በመጠጣት አብሮነታቸውን የሚያጎለብቱባት የተለየች ዕለት መኾኗ ሲዘከር ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በቤተ እግዚአብሔርም ዕለቷን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ሲዘክሩ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡
አሁን ላይ በዘመናዊው የመንግሥት ሥርዓት ተመሪው መሪውን ማክበርን፣ ዝቅ ብሎ ማገልገልን መሪውም ተመሪውን ከታናናሹ እንዳንዱ ኾኖ በንጹህ ሕሊና የማገልገልን ሥርዓት እየከወነ ይኾን? ለሚታዩ ችግሮቻችን መውጫው መንገድ አገልጋይ ለተገልጋይ ራስን አሳልፎ እስከመስጠት፣ ተገልጋይም አገልጋዩን ማድመጥ፣ መከተል እና መተግበር ከጸሎተ ሐሙስ የምንማረው ነው፡፡
መልካም የምስጢር ሐሙስ በዓል
በምሥጋናው ብርሃኔ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/