
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለብዙኃን መገናኛ ተቋማት መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ የክልሉ መንግሥት ተቀዳሚ ትኩረት ነው ያሉት የቢሮ ኅላፊው አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮችም የ90 ቀናት እቅድ ተዘጋጅቶላቸው እየተከናወኑ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡
አቶ ግዛቸው እንዳሉት የሽብር ቡድኖች እና ግብረ አበሮቻቸው ለአማራ ሕዝብ የሰጡት የተሳሳተ የሃሰት ትርክት አማራን እረፍት እንደነሳው ገልጸዋል። ዘርን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች የክልሉ መንግሥት እሳት ማጥፋት ላይ እንዲጠመድ አድርጎት ቆይቷል ያሉት ኀላፊው አኹን ላይ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በከፈተው ወረራ አኹንም ድረስ በክልሉ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ወገኖች እና አካባቢዎች እንዳሉ አቶ ግዛቸው በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት እና የሽብር ቡድኑን የጥፋት ባህሪ ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የውስጥ አንድነትን ማጠናከር፣ መደራጀት እና አደረጃጀትን መፈተሸ የክልሉ መንግሥት እያከናወነው ያለው የትኩረት አቅጣጫ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡
አቶ ግዛቸው በክልሉ ውስጥ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን እና ምክንያቶቻቸውን በመለየት ከሕዝቡ ጋር በጋራ ለመፍታት የፀጥታ ኀይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
አንጻራዊ ሰላም አለ ማለት ስጋቶች የሉም ማለት ስላልሆነ በትብብር መሥራትን ይጠይቃል ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሰከነ እና አማራጭ የመፍትሔ ሃሳቦችን የያዘ በሳል አካሄድን እንደሚጠይቅም አንስተዋል፡፡
አቶ ግዛቸው በመግለጫቸው እንዳነሱት ከዘላቂ ሰላም ጎን ለጎን የክልሉን አቅም ተጠቅሞ ለማምረት እና በጦርነት የተጎዳውን ምጣኔ ሃብት ለመደጎም የግብርና ሥራዎች በተለየ ትኩረት እየተሠሩ ነው፡፡ በዚኽም
•ክልሉ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በእርሻ ለመሸፈን እየተሠራ ነው፡፡
• የአፈር ማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር እጥረትን ለመፍታት አማራጭ መፍትሔዎችን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
• የሥራ እድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር፣ የክልሉን የገቢ ግብር ማሳደግ፣ የማሕበራዊ ተቋማት መልሶ ግንባታ እና ሕገ ወጥነትን ለመከላከል ሌላው በትኩረት እየተሠራበት ያለ ዘርፍ ነው፡፡
• ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች የፈጠሩት የኑሮ ውድነት መቋቋም እንደተጠበቀ ሆኖ ሕገ ወጥ የገበያ ሥርዓቱ የፈጠረውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት የጋራ ርብርብን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት የሰከነ የፖለቲካ መንገድን መከተል ይጠይቃል ያሉት አቶ ግዛቸው የክልሉ ሕዝብ በቂ መረጃ እንዲያገኝም በየ15 ቀኑ መረጃ የማድረስ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/