“ኹሉም ያለው ምንም እንደሌለው ኾነ፣ ድረሱልኝም አለ”

183

ሚያዝያ 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጨርሶ ጀመረ፣ ዓለትን በጥበብ አሳመረ፣ የእግዚአብሔርን ቅዱስ መንፈስ በሠራው ድንቅ ሕንጻ ውስጥ አሳደረ፣ ከእርሱ ውጭ ጨርሶ የጀመረ፣ ተመርምሮ ያልተደረሰበት ጥበብ በዓለት ላይ ያኖረ አልተገኘም፡፡

ዓለት ታዘዘለት፣ እንደ ሰበዝ ተሰነጠቀለት፣ በእጆቹ ጥበብ እንደ አሻው አሳመረው፣ እንደ ፈለገ አዥጎረጎረው፣ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን፣ በቅድስናው ያየውን በዓለት ላይ ተገበረው፣ ቀረጸው፣ አሳመረው፣ በጥበብ አኖረው፡፡ እርሱ ጠቢብ ነው በጥበብ የሚኖር፣ እርሱ ንጉሥ ነው በዙፋን የሚከበር፣ እርሱ ቅዱስ ነው በቅድስና የሚዘከር፣ ረቂቅ ነው የሠራው ድንቅ ሥራ የማይመረመር፣ እርሱ ምስጢር ነው ምስጢሩ ያልተፈታ ድንቅ፡፡

ንጉሥ ወቅዱስ የኾነ፣ ንግሥናን ከቅድስና፣ ጉብዝናን ከትህትና፣ ጀግንነት ከትዕግስት ጋር አጣምሮ የተሰጠው ለምድርም ለሰማይም የተመቸ ሰው ፈልጉ ከተባለ የሚገኘው በዚሕች በታላቋ ሀገር በኢትዮጵያ ነው፡፡

እፁብ ድንቅ መቅደስ ያነጸው፣ ጥበብ የተቸረው ላልይበላ ንጉሥ ነው፡፡ በታላቁ ዙፋን ተቀምጦ ታላቋን ሀገር ያሥተዳደረ፣ ቅዱስ ነው ለሰማዩ ክብር ተገዢ ኾኖ የኖረ፡፡ ዓለም ቅዱስ ወ ንጉሥ ላልይበላ እንዳነጻቸው፣ እንደ ቀረጻቸው፣ የተሰጠውን ጥበብ እንደገለጠባቸው ዓይነት አብያተ መቅደሶችን ከኢትዮጵያው ውጭ በየትም ሥፍራ አላየችም፡፡ በኪነ ሕንጻ ተራቅቄያለሁ፣ የሰውን ልጅ በሙሉ እጹብ ድንቅ የሚያስብል ሥራ እሠራለሁ ያለችው ዓለም እንደ ላልይበላ ግን መሥራት አልቻለችም፡፡ ጨርሳ መጀመር አልተቻላትም፣ ዓለትን ፈልፍላ አብያተ መቅደስ ማነጽን አልኾነላትም፡፡ እርሱ ዓለም ከደረሰበት ጥበብ ርቆና ተራቅቆ የሄደ ጠቢብ ነውና፡፡

የረቀቀ ጥበብ የሚገኘው በኢትዮጵያ ነው፣ የረቀቁ ጠቢባን ያሉት በኢትዮጵያ ነው፣ የረቀቁ ጀግኖች ያሉት በኢትዮጵያ ነው፣ ኢትዮጵያ ረቂቁን የወለደች፣ ረቂቁን ያሳደገች፣ የረቀቀውን የታቀፈች፣ የረቀቀውን ያደረገች፤ የምታደርግ ናትና፡፡ በምድር በጥበብ የላቀውና፣ የረቀቀው ነው የሚባልለት የቅዱስ ላልይበላ የጥበብ ሥራ ብዙዎችን ስቧል፡፡ ውበቱን፣ ግርማውን፣ ቅድስናውንና የጥበቡን ልክ ለማየት የፈለጉት ሰዎች ዓይናቸውን ከአብያተ መቅደሱ ላይ ተክለው ኖረዋል፡፡

አብያተ መቅደሱ ካለበት ሥፍራ ለመድረስ ባሕር ሰንጥቀው፣ የብስ አቋርጠው ገስግሰዋል፣ በደጁ ደርሰው በጥበቡ ተደንቀዋል፣ ባዩት ነገር ኹሉ ተገርመዋል፡፡ ላልይበላ ድንቅ ነገርን አደረገ ሲሉ ተገርመዋል፣ እፁብ ድንቅ ብለዋል፡፡ እውን ይኼ በሰዎች ልጆች ተሠራን? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ አዎን ይህስ እውነት፣ ምልክት ነው፡፡

በኢትዮጵያዊው ቅዱስ ወ ንጉሥ የቅድስና የጥበብ እጆች የተፈከፈለ የተቀረጸ ድንቅ ጥበብ ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተፈቀደ፣ በኢትዮጵያውያን ብቻ የተሠራ፣ የቅዱስ መንፈስ ማደሪያ፣ የቅዱሳን መናኸሪያ፡፡

ላልይበላን የመሰለ የምድር በረከት፣ ሃይማኖት፣ የዓለም ውበት ያላዩ ኹሉ አንድ ነገር አጉድለዋል፡፡ ለምን ካሉ በዘመናቸው ማየት የሚገባቸውን ታላቁን ጥበብ፣ ከጥበቦች ኹሉ የላቀውን፣ ሰው ኹሉ በሚያውቀው በኪነ ሕንጻ ሕግ የማይገዛውን፣ ጨርሶ የጀመረውን ጥበብ ሳያዩ ቀርተዋልና፡፡ እርሱን አለማየት ብዙ ነገርን ያጎድላል፡፡ ጥበብን ለማድነቅ ላልይበላን ማየት ግድ ይላልና፡፡ ላልይበላን ያዩ ዓይኖች የተባረኩ ናቸው፣ ስለ ላልይበላ የሰሙ ጀሮዎች የተመረጡ ናቸው፣ አብያተ መቅደሱን የረገጡ እግሮች እድለኞች ናቸው፣ አብያተ መቅደሶቹን የዳሰሱ እጆች ንዑዳን ክቡራን ናቸው፣ ስለ ላልይበላ የሚያውቁ ሰዎች የረቀቁ ናቸው፣ በአብያተ መቅደሶቹ ውስጥ ለአገልግሎት እየተፋጠኑ የሚኖሩት አበው የተቀደሱ ናቸው፡፡

ስለ ላልይበላ የሚናገሩ የሚመሰክሩ አንደበቶች ብሩካን ናቸው፣ ይህ ዓለምን ያስደመመው ጥበብ የበዛበት፣ መንፈስ ቅዱስ ያረፈበት ድንቅ ቅርስ ብዙዎች ስቧል፣ ብዙዎችን በቤቱ ሰብስቧል፣ ብዙዎችን በመንፈስም በስጋም መግቧል፡፡ እርሱ የነብስም የስጋም መና እና በረከት ኾኖ ዓመታትን ተሻግሯል፡፡ ዛሬ ግን ነገሩ ሌላ ኾኗል፡፡

በደብረ ሮሃ ቅድስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና እና ገዳማት ሥር ብዙዎች ተጠልለው ኖረዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱን ብለው በሚመጡት ጎብኚዎች የሚተዳደሩትና ኑሯቸውን የሚደጉሙት ብዙዎች ናቸው፡፡ ለከተማዋ ነዋሪዎች ላልይበላ የሚሳለሙበት፣ የሚጸልዩበት ብቻ አይደለም፡፡ ሕይወታቻው ጭምር እንጂ፡፡ ላልይበላን ብለው በሚመጡ ጎብኚዎች በሚገኝ ገንዘብ ሕይወታቸውን ይመራሉ፣ ለአብያተ ክርስቲያናቱ አገልጋዮች መደጎሚያ፣ አብያተ ክርስቲያናቱ ለሚፈልጉት ኹሉ የነዋይ ምንጭ ይሄው ቅዱስ ሥፍራ ነው፡፡

ይህ ታላቁ ቅርስ ለላልይበላ ከተማ ነዋሪዎች ብቻ ሳይኾን ለኢትዮጵያም በቱሪዝም ዘርፉ መደጎሚያ የኾነ ቅርስ ነው፡፡ ታዲያ ቀደም ሲል በኮሮና ቫይረስ፣ በአሻባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ምክንያት ላልይበላ ከጎብኚዎች ያገኘው የነበረውን ኹሉ አጥቷል፡፡ መሠረታቸውን በጎብኚዎች ላይ ያደረጉት የከተማዋ ነዋሪዎች ተቸግረዋል፡፡ ያለ ማቋረጥ ይጎርፍ የነበረውን ጎብኚ ማየት ናፍቀዋል፡፡ ከራሱ አልፎ ለሀገር ደጓሚ የነበረው ቅዱስ ሥፍራ ዛሬ ላይ ድረሱልኝ ብሏል፡፡

ኹሉም ያለው ምንም እንደሌለው ዛሬ ላይ እጁን ለእርዳታ ዘርግቷል፡፡ ኹሉም ያለው ምንም እንደሌለው ኾኗል፡፡ በመልካሙ ጊዜ ያደነቁት፣ ያከበሩት፣ ሊያዩት የጓጉለት፣ ባሕርና የብስ አቋርጠው ስፍራውን ለመርገጥ የተፋጠኑት ዛሬ ግን ዝም ብለዋል፡፡ እነዚያ እግር እያጠቡ የሚቀበሉትን፣ ከአልጋ ወርደው የሚያስተኙትን፣ የደከመውን የሚያሳርፉትን፣ የተጠማ የሚያጠጡትን፣ የታረዘ የሚያልብሱትን፣ እንግዳ ከራሳቸው በላይ የሚወዱትን እነዚያን ደጋግ ሰዎች ረስተዋቸዋል፡፡

የእነርሱ ደስታና በረከት በእንግዶቻቸው ላይ ነበርና ዛሬ ላይ ግን ተቸግረዋል፡፡ ለስጋም ለነብስም የሚሰጠው ዛሬ ላይ ምንም እንደሌለው ኾኗል፣ ዓይኖች ኹሉ ወደ ቅዱስ ላልይበላ እንዲያዩ፣ እግሮች ኹሉ ወደ ቅዱስ ላልይበላ እንዲጓዙ፣ አንደበቶች ኹሉ ስለ ቅዱስ ላልይበላ እንዲናገሩ አበው ጥሪ እያቀረቡ ነው፡፡ መመኪያ፣ መኩሪያ፣ የሃይማኖት፣ የእሴት፣ የጥበብ፣ የታሪክና የምስጢር ባለቤት የኾነውን ቅዱስ ሥፍራ የመደገፍ ጥሪ ቀርቧል፡፡ እርሱ ለዘመናት ሰጥቷል፣ ዛሬ ዘመን ገፍቶት እጁን ዘርግቷል፡፡ ልጆቹን ድረሱልኝ ብሏል፡፡

ታዲያ ጥበብን የሚያደንቁት፣ መስጠት የሚያውቁት፣ የተራበን የሚያጎርሱት፣ የተጠማን የሚያጠጡት፣ የታረዘን የሚያለብሱት፣ ካዘነው ጋር አብረው የሚያዝኑት፣ ከተደሰተው ጋር የሚደሰቱት ኢትዮጵያውያን ምን ይሉ ይኾን ? ታላቁ ቤተመቅደስ ሲጣራ፣ አበው እጃቸውን ሲዘረጉ ዝም ይላሉ ወይስ በሚታወቁበት ደግነት ልክ ይገኛሉ?

ኹሉን የሰጠው፣ ዛሬ ላይ ድረሱልኝ እያለ ዝም ከተባለ ታሪክ ይታዘባል፣ በመልካም ጊዜ ማወደስ፣ ማሞገስ ከንቱ ይኾናል፡፡ ኹሉን የሚሰጠው እጁን ሲዘረጋ ማየት ስሜቱ ከባድ ነው፣ ለሰዎችም ታላቅ ትርጉም አለው፡፡ ለላልይበላ መድረስ አንድም በረከት መቀበል፣ ኹለትም ታሪክ መሥራት ነው፡፡ ኹሉን ለሚሰጠው ትንሽ ሰጥቶ ብዙ መቀበል፡፡ የሚቻለውን አድርጎ በትህትና አበውን ማገልገል፣ የቤተ መቅደሱን ክብርም ማስቀጠል ነው፡፡

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous articleበ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና 50 በመቶ እና በላይ ውጤት አምጥተው ወደ ዩኒቨርስቲዎች መግባት ያልቻሉ ተማሪዎች በክልሉ መምህራን ኮሌጆች እንዲሠለጥኑ ተጨማሪ ውሳኔ ተላለፈ።
Next article“ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ የክልሉ መንግሥት ተቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ ነው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ