በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የተገነባው የሎዛ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለምረቃ ዝግጁ ሆኗል።

254

በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በ20 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባው ትምህርት ቤቱ 28 የመማሪያ እና አራት የቤተ ሙከራ ክፍሎች፣ ቤተ መጽሃፍት እና የአስተዳድር ህንጻ የተሟላለት ነው።

ነገ ጥቅምት 6/2012 ዓ.ም የሚመረቀው ትምህርት ቤቱ 300 የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝም የጎንደር ከተማ አስተዳድር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አማረ መስፍን ለአብመድ ገልፀዋል። በቂ ወንበር እና የመማሪያ መጽሃፍትም እየተሟሉ መሆኑን ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቱ መገንባት በአካባቢው ባሉ አምስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲሸጋገሩ በአቅራቢያቸው ለመማር ያስችላቸዋል። ይህም ከዚህ ቀደም ከአምስት እስከ ሰባት ኪሎ ሜትር የሚረዝም መንገድ ተጉዘው እንዲማሩ ይገደዱ ለነበሩ ተማሪዎች እፎይታ ይሰጣል ተብሏል።

አብመድ ያነጋገራቸው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎችም ከዚህ ቀደም ታላላቆቻቸው ረጅም ርቀት ተጉዘው ወይም ቤት ተከራይተው ለመማር ይገደዱ እንደነበር፤ ይህም በትምህርታቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድርባቸው እንደነበር አስታውሰዋል። የትምህርት ቤቱ በቅርበት መገንባት ደግሞ ገንዘብ፣ ጉልበት እና ጊዜ እንደቆጠበላቸው ተናግረዋል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ፈንታ ጽህፈት ቤቱ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 20 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እያስገነባ መሆኑን ገልፀዋል። ሎዛ ብርሃንን ጨምሮ አራት የሁለተኛ ደረጃ እና አንድ ቅድመ መደበኛ ትምህር ቤቶች በዚህ ዓመት ለመማር ማስተማር ሥራው ዝግጁ እንደሆኑም ነው ያስታወቁት።

በጎንደር እየተገነባ ያለው ሎዛ ብርሃን ትምህርት ቤት በጥሩ የግንባታ ፍጥነት እየተጠናቀቀ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ የመንገድ መሰረተ ልማት አለመሟላቱ ጫና እንዳሳደረባቸው አስታውቀዋል።

ምንም እንኳን ትምህርት ቤቱ ነገ ጥቅምት 6/2012 ዓ.ም የሚመረቅ ቢሆንም የመሰረተ ልማት አለመሟላቱን እና ያልተጠናቀቀ የግንባታው አካል መኖሩን በመስፍራው የተገኝው የአብመድ የጋዜጠኞች ቡድን ተመልክቷል።

የጎንደር ከተማ አስተዳድር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አማረ መስፍን ወደ 10 በመቶ የሚጠጋው የግንባታው አካል አለመጠናቀቁን ገልጸው ቀጣይ ግንባታው ሙሉ በሙሉ እንዲጠናቀቅ እና የመንገድ መሠረተ ልማት እንዲሟላ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ከሚገነቡ 20 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል አራቱ በአማራ ክልል ውስጥ በጎንደር፣ ደባርቅ፣ ዋግ ኽምራ እና ደቡብ ወሎ ዞን ነው የሚገኙት።

ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ

Previous articleበቀጣዩ ሃገር አቀፍ ምርጫ ላይ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሴቶች ተሳትፎ ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ፡፡
Next articleዜና መፅሔት ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 05/2012 ዓ/ም (አብመድ)