
ሚያዝያ 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ በቀጣይ ሣምንት ጀምሮ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት እንደሚጀምር የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
ግብርና ሚኒስቴር በ2014/15 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ሥርጭት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
በዚህ ዓመት 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ተጠቁሟል። ከዚህ ውስጥ 4 ሚሊዮን ኩንታሉ እስካሁን ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ.ር) እንደገለጹት መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት ግዥ ፈጽሟል።
በምርት ዘመኑ 19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ፍላጎት መኖሩን ጠቁመው በምርት ዘመኑ ከ15 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርብ ተናግረዋል።
እስካሁን ያልገባውና በተደጋጋሚ ጨረታ የወጣው ከፍተኛ መጠን ያለው የዩሪያ ማዳበሪያም ጅቡቲ ወደብ እየደረሰ መኾኑን ጠቁመው በቀጣይ ሳምንት ወደ ሀገር ቤት መግባት ይጀምራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ያብባል አዲስ በበኩላቸው፤ እስካሁን 4 ሚሊየን ኩንታል ከወደብ ወደ ሀገር ቤት እየተጓጓዘ መኾኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በርካታ መጠን ያለው የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ እየደረሱ መኾኑንና ማዳበሪያውን ወደ ሀገር ውስጥ ለማጓጓዝ በቂ ዝግጅት ተድርጓል ብለዋል።
በዚህም በየዕለቱ ከ8 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን በላይ የሚኾነውን በጭነት እንዲሁም 1 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶኑን ደግሞ በባቡር እንዲጓጓዝ ለማድረግ መታቀዱን ነው የጠቆሙት።
ለዚህም ከ11 የከባድ ተሽከርካሪዎች ድርጅቶችና ከባሕርና ሎጅስቲክስ ድርጅት ጋር ውል መፈጸሙን ጠቁመው የማጓጓዝ ሂደቱ ከእነዚህ ተቋማት አቅም በላይ ከኾነ ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ልንጠቀም እንችላለን ብለዋል።
ጭነቱን ለማጓጓዝ ውል የወሰደው የብራይት ድንበር ተሻጋሪ ደረቅ ጭነት ባለንብረቶች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ንጉሥ በበኩላቸው በጉዞ ላይ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ማኅበሩ ግብዓቱን በወቅቱ ለማሰራጨት ቅድመ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ያገመጠው የጸጥታ ችግር፣ በአውራጅና ጫኝ በኩል የተፈጠረ የተጋነና ዋጋ፣ ሕገ-ወጥ ኬላዎች፣ መጋዘን ላይ በፍጥነት ያለማራገፍ ከገጠሟቸው ችግሮች መካከል ጠቅሰዋል።
የግብዓት አቅርቦትና ሥርጭቱ እንዳይስተጓጎል መሰል ችግሮችን የሚመለከተው አካል ሊፈታ ይገባል ብለዋል።
በፌዴራል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የኅብረት ሥራ ግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋለም እንየው ከወደብ ተጓጉዞ ወደ ማኅበራቱ መጋዘን የሚደረሰውን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለማሰራጨት ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
በዚህም እስካሁን በየመጋዝኑ ያሉ ግብዓቶች ለተጠቃሚውን እንዲሰራጩና መጋዝኖቹ ክፍት ኾነው እንዲጠብቁ፤ ግብዓቱ ከደረሰ በኋላም መጨናነቅ እንዳይኖር በፍጥነት እንደሚከፋፈል መግለጻቸውን የዘገበው አዜአ ነው።
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/