“የውስጥ ማንነትን የሚያስፋ እና ራስን ማዳመጥ የሚያስችሉ የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች ለትውልዱ ያስፈልገዋል” ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ

252

ሚያዝያ 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር በጦርነት እንደምትከበረው ኹሉ በጦርነት ግን አትጸናም፡፡ ጦርነት ለሀገረ መንግሥት ምስረታ የመጨረሻ አማራጭ እንጅ የተሻለ እና ተመራጭ ምርጫ ኾኖ አያውቅም፡፡ እርግጥ ነው ኹሉም የዓለም ሀገራት በአስከፊ ጦርነት ውስጥ አልፈዋል፡፡ ምዕራባዊያን ከ1618 እስከ 1648 ለሦስት አስርት ዓመታት በጦርነት ፍዳ አይተዋል፡፡ ከተሞቻቸው ወደ ድንጋይ ዘመን ተቀይረዋል፡፡

ከስምንት ሚሊየን በላይ ዜጎቻቸው መራር የሕይዎት መስዋእትነትን ከፍለዋል፡፡ የዚያ አስከፊ ጦርነት መውጫ መንገድ ግን ጦርነት ኾኖ አልተገኘም፡፡ ጦረኞቹ ከጦርነቱ መውጣት ወደ ጦርነቱ የመግባትን ያክል ቀላል ኾኖ አላገኙትም፡፡ ኀይል ቀይረው፣ መሳሪያ ወልውለው እና ድንጋይ ተወራውረው መፍትሔ ያላገኙት ምዕራባዊያኑ ባልረጋ የጦርነት ቀጣና ውስጥ የረጋ ብዕር እና እሳቤ ተወልዶ “ዌስት ፋሊያ” የተሰኘውን ስምምነት የጦርነቱ ፍጻሜያዊ መፍትሔ አድርጎ አመጣላቸው፡፡ እርስ በርሳቸው ትከሻ ተለካክተው የጀመሩትን ጦርነት እልፎችን ገብረው ቀሪዎቹ በስምምነት ቋጩት፡፡ “ይብላኝ ለሟች!” ይላል የእኛ ሰው፡፡

አኹናዊቷ ኢትዮጵያ ባልረጋ እና ባልሰከነ ድባብ ውስጥ ትገኛለች፡፡ አኹንም ድረስ ወጥቶ መግባት ብርቅ የኾነባቸው አካባቢዎች ብዙ ናቸው፡፡ ሥርዐት አልበኝነት የበላይነቱን የወሰደበት የሚመስሉ አዝማሚያዎች ከዚኽም ከዚያም ይታያሉ፡፡ ያለፉት ሦስት ዓመታት ምስቅልቅሏን በሽግግር ያስታመመችው ኢትዮጵያ ከድኅረ ምርጫ ሽግግሯም በኋላ የሰከነ አየር የሚነፍስባት አትመስልም፡፡

ኢትዮጵያዊ ሞራል፣ የሕግ የበላይነት እና መደማመጥ እየተሸረሸሩ ቋፍ ላይ ቆመዋል፡፡ ውጣልኝ፣ እገታ፣ ግድያ፣ ማሳደድ፣ ማፈናቀሉ እና ብሽሽቁ ለመራቢያ ምቹ ከባቢን ያገኙ ይመስላሉ፡፡

በአንጻሩ የአሳቢያን ዝምታ፣ የተባ ብዕር መቀጨጭ እና የደቦ እሳቤ መበራከት ከዛሬ በላይ ነገ አብዝቶ ለሚያስጨንቃቸው ሰዎች ትልቁ ምክንያት ነው፡፡ አሳቢዎች ሀገር የምትገነባው ከሐሳብ ድርና ማግ ተፈትላ ነው ይላሉ፡፡
ስለነገው እና ስለሀገራቸው እርግጠኛ መኾን ያልቻሉት ዜጎች በርካታ ቢኾኑም የሦስተኛው ዓለም ሀገራትን የፖለቲካ ተለዋዋጭ ባህሪ እንደ ምክንያት ጠቅሰው ክፉ ሐሳባቸውን ሊያመክኑ ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡ ነገሩ “ሕልም እልም” እንደሚሉት ዓይነት መኾኑ ነው፡፡

ክፉ ሐሳብ ስለተፈራ ብቻ ክፉ ፍሬ ሳያፈራ አይቀርም ይባላል፡፡ ሐሳብ ተንሰራፍቶ ወደ ድርጊት እስከተለወጠ ድረስ የተዘራው ይበቅላል፤ የበቀለውም ይታጨዳል፡፡ ልምምዱ የመልካም ዘር እና መልካም ፍሬ ሳይኾን የእንክርዳድ መብቀያ ወቅት ስለመቃረቡ ማሳያዎቹ ብዙዎች ናቸው፡፡

ከጦርነት ወጥተው እና ራሳቸውን በሚገባ ዓይተው ተጽዕኖ ፈጣሪ እስከመኾን የደረሱ በርካታ የዓለም ሀገራት አሉ፡፡ ከነዚኽ ሀገራት ጀርባ በጣት የሚቆጠሩ አሳቢዎቻቸው እና ጸሓፍቶቻቸው በመልሶ ግንባታው ሂደት ዐሻራቸው ጎልቶ ይታያል ይባላል፡፡ ከጦርነት የተረፉትን ከቁዘማ በማውጣት እና አዲሱን ትውልድ ለሀገር በሚበጅ መልኩ በመቅረጽ በኩል የድኅረ ጦርነት የጥበብ ሥራዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በዓለም የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ዐሻራ ያላቸውን ሥራዎች ካሳረፉ ሀገራት መካከል አንዷ ሩሲያ ናት የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ.ር) ናቸው፤ ለ150 ዓመታት የዘለቀው የብዕር አብዮቷ ለዛሬው ታላቅነቷ አበርክቶው የጎላ ነበር ብለው ያስባሉ፡፡ ያልተረጋጋ ከባቢ የተረጋጋ እና የተባ ብዕርን ይፈጥራል የሚሉት የፍልስፍና ምሁሩ የመጪው ዘመን ኢትዮጵያ በጽኑ ዓለት ላይ እንድትቆም በዚኽ ወቅት ሩቅ አሳቢ የብዕር ውጤት ያስፈልጋታል ይላሉ፡፡

እንደ ዶክተር ዳኛቸው ዕይታ የውስጥ ማንነትን የሚያስፋ እና ራስን ማዳመጥ የሚያስችሉ የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች ለትውልዱ ያስፈልገዋል፡፡ ሀገር የምትገነባው በጠንካራ ወታደራዊ ተቋም፣ ምጣኔ ሃብታዊ አቅም እና ማኅበረሰባዊ ሥሪት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ዶክተር ዳኛቸው “ሥነ ጽሑፍ ግን የበላይነቱን መያዝ ይኖርበታል” ነው የሚሉት፡፡

ትርምስ እና ፈተና ለሥነ ጽሑፍ ሰዎች ምቹ እና ሐሳብ የሚፈልቅበት ወቅት መኾኑን ዶክተር ዳኛቸው ጠቅሰዋል፡፡

ከቁዘማ የሚያወጣ፣ ትውልዱን ከማንነቱ ጋር የሚያቆራኝ፣ ምክንያታዊነትን የሚያለማምድ እና በሐሳብ የሚያምን ትውልድን የሚያዘጋጅ ሥነ ጽሑፍ ኢትዮጵያ በዚኽ ወቅት ያስፈልጋታልም ሲሉ በአጽንዖት መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እና ምቹ የኢኖቬሽን ሥነ ምህዳር መፍጠር ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ተናገሩ።
Next article“ምዕመናን በሰሙነ ሕማማት ክርስቲያናዊ ተግባራትን መፈጸም አለባቸው” ብፁዕ አቡነ አብርሃም