ራስን ዝቅ የማድረግ የትህትና በዓል (ሆሳዕና በዓርያም)

373

ሚያዝያ 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ይኽ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ዘንድ የትህትና በዓል እንደኾነ ነው የሚታወቀው፡፡ በሆሳዕና በዓል መሪው ተመሪውን ዝቅ ማለትን ያስተማረበት ከመኾኑም በላይ ተመሪውም የሚመራውን ጨርቁን እያነጠፈ እና ዘንባባ እየጎዘጎዘ ያከበረበት የትህትና እና የፍቅር በዓል ነው፡፡

የሆሳዕና በዓልን ታሪካዊ ዳራ ስንመለከት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ “ሆሳዕና በዓርያም ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው” በማለት የሚከተሉት አማኞች ፈጣሪያቸውን መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው።

ሆሳዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሁዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ሲኾን ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ ነው። ሆሳዕና ከረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተክርስቲያን የበዓል ቀንም ነው፡፡

በዚኹ በዓለ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‘ሆሳዕና በዓርያም’’ ‘ሆሳዕና ለወልደ ዳዊት’’ ‘ዕለተ ሆሣዕናሁ አርዓየ እና ሌሎችንም በመዘመር ራሱን ዝቅ አድርጎ በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ለመጣው ንጉሥ ክብር ይሰጣሉ፡፡

አስቀድሞም በነቢየ እግዚአብሔር ዘካሪያስ ዘካ.9፣9 እንደተነገረው “አንቺ የጽዮን ልጅ ኾይ እጅግ ደስ ይበልሽ ፣ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ኾይ እልል በይ እነኾ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሁትም ኾኖ በአህያይቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፤ ሰላምንም ይናገራል፤” በማለት እንደሚመጣና የሰላምንም ብሥራት እንደሚያበስር ተናግሮ ነበር። ይኽን ትንቢት የሚያውቁት ሲመጣ ኹሉም ፈጥነው ልብሳቸውን ወሰዱ በሰገነቱም መሰላል እርከን ላይ ከእግሩ በታች አነጠፉት አከበሩትም።

አኹን ላይ ታዲያ ክርስቲያኖች ያን ጊዜ ለማስታወስ ዘንባባ በመያዝ “‘ቡርክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው” እያሉ ዘንባባ ያነጥፋሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ያን ጊዜ ታሳቢ አድርጋ ዘንባባን ለሕዝበ ክርስቲያኑ ታድላለች። በቤተክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት ይህን በዓል የሚመለከቱ ወንጌሎች እንዲነበቡም ታደርጋለች፡፡

ለመኾኑ አሁን ላይ ኢትዮጵያዊያን መሪዎቻችንን ራሳችንን ዝቅ በማድረግ እናከብር ይኾን፤ መሪዎቻችንስ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ለሕዝብ ክብር ይሰጡ ይኾን? ለማንኛውም ሆሳዕና የትህትና በዓል በመኾኑ ራሳችንን ዝቅ አድርገን እርስ በርሳችን በመከባበር ሀገራችንን ከጥፋት እንጠብቅ ዘንድ ኀላፊነት ተጥሎብናል፡፡

መልካም የትህትና በዓል ተመኘን

በምሥጋናው ብርሃኔ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

Previous article“ኑ የፍቅር ካባ እናልብሳችሁ፣ ከደግነት ምንጭ እናጠጣችሁ”
Next articleየዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እና ምቹ የኢኖቬሽን ሥነ ምህዳር መፍጠር ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ተናገሩ።