
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ፍቅር እንደ ዥረት ይፈስባታል፣ ደግነት ይፈልቅባታል፣ ኢትዮጵያዊነት ተሞሽሮ ይኖርባታል። ፈጣሪ ምድሯን አድሏታል፣ የፍቅር ካባ አላብሷታል፣ በፍቅር ውቅያኖስ ከቧታል፣ በደግነት ባሕር አስውቧታል፣ በመልካምነት ምንጭ ያረሰርሳታል። ፀዳው በማያድፍ፣ በዘመን ብዛት በማያረጅ የአንድነት ሸማ ያላብሳታል። መልኩ ያማራው፣ ውበቱ ከሩቅ የሚጣረው፣ ማዕዛው ልብን የሚያውደው ያ መልካም ሸማ በአንድነት ያለብሳል። ለሁሉም ይደርሳል። ሁሉንም ያስውባል፣ ያሳምራል።
በዚያ ምድር ክፋት ተቀብሯል፣ ምቀኝነት በዚያ ምድር መድረሻ ካጣ ሰነባብቷል፣ ምድሩን የሞላው ደግነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ አብሮነት፣ አንድነት፣ አሸናፊነትና አርቆ አሳቢነት ነው። ደግነት የመላብሽ፣ ፍቅር የፀለለብሽ፣ ፈጣሪ የሚከብርብሽ፣ መለያየት የማይታወቅብሽ፣ ምድርሽን የረገጠ በስስት የሚያይሽ፣ ያላየሽ በአሻገር ኾኖ የሚናፍቅሽ፣ ለማየት የሚመኝሽ፣ እድል ረድታው ለማየት የሚጓጓልሽ፣ ከአጠገብሽ የራቀው በትዝታ የሚባዝንልሽ፣ አድባር የሚከበርብሽ፣ ሰላም የሚሰበክብሽ፣ ስለ ሰላም የሚፀለይብሽ፣ በሁሉም የታደልሽው የፍቅሯ መሶበ ወርቅ እንደምን ከርምሻል? ቂምና በቀል የሚቀበርብሽ፣ ደስታ በረከት የሚተከልብሽ፣ ቅንና ደግ የሚወለድብሽ፣ ኩሩና ሀገር ወዳድ የሚያድግብሽ፣ ለሀገር ሟች የሚዳብርብሽ የፍቅሯ ንግሥት እንደምን ሰንብተሻል?
ፈተናው ቢበዛብሽም፣ ጠላቶች ቢበራከቱብሽም የፍቅርሽ፣ የአንድነትሽና የመቻልሽ ወሰን፣ የጽናትሽ ልክ የከበደ የመሰለውን አቅልሎታል፣ የችግሩን ጊዜ አሳልፎታል፡፡ የጨለመ የመሰለውን በብርሃን ለውጦታል፣ የአደፈ የመሰለውን አንጽቶታል፡፡ ጠላት ከቦሽ የመቸገርሽ ነገር ሲሳማ አንቺን ያሉ ሊደርሱልሽ ወደ አለሽበት ገስግሰዋል፣ አንቺን ከጠላት መንጋጋ ለማላቀቅ ለሚገሰግሱት ስንቅ ይዘው ከኋላ ተከትለዋል፣ አይዞህ በርታ ጠላትን ምታ እያሉ አበረታተዋል፣ ካለሽበት መድረስ ያልቻሉት፣ አቅምና ጊዜ ያልፈቀደላቸው ደግሞ በአሉበት ኾነው አስበውሻል፣ የፍቅር እመቤት፣ የደነግነት ንግሥት፣ የአብሮነት ልዕልት ነሽና ብዙዎች ደስታሽን ይሻሉ፣ ስለ ሰላምሽና ስለደስታሽ ያለ እረፍት ያስባሉ፡፡
የሚስማማሽ ፍቅር፣ ክብር፣ አንድነት፣ አብሮነት፣ ኢትዮጵያዊነትና ደግነት ነውና የከፋሽ ቀን ብዙዎች ተከፍተዋል፣ የከፋሽ ቀን ያስከፉሽን ሊቀጡ ብዙዎች ተሰውተዋል፣ ነብሳቸውን ሰጥተዋል፣ ለፍቅር እመቤት መሞት፣ ለደግነት ንግሥት መሰዋእት፣ ለአብሮነት ልዕልት ራስን መስጠት፣ ለኢትዮጵያዊነት ምልክት መከራን መርሳት ክብር ነውና ለክብርሽ ያላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ባደረጉት ነገር ሁሉ ይኮራሉ፣ ይመካሉ እንጂ አይጸጸቱም፡፡ በከፈሉት ዋጋ አሸናፊነትን ተሸልመዋል፣ ድልን ተሰጥተዋል፣ ሰላምን መልሰዋል፣ ክብርን ከፍ አድርገዋልና ደስ ይሰኛሉ፡፡
በዚያ ምድር በአንድ ማድ ላይ በአንድ በኩል ቄሱ በሌላ በኩል ሼሁ ይቀርባሉ። ሼሁ ቢስሚላህ ብለው ይቆርሳሉ፣ ቄሱም በስመ አብ ብለው ይባርካሉ፣ እንደ እምነታቸው ቆርሰው፣ እንደ ፍቅራቸው ይጎራረሳሉ፣ ʺለአላህ ብለው ይጉረሱ፣ በእመብርሃን ብለው ይቅመሱ” እየተባባሉ ከሚጠጣው ይጎነጫሉ፣ ከሚበላው ይጎርሳሉ፣ ወሎ ውስጥ ከሁሉም በፊት ሰውነት ይቀድማል፡፡ ወደ ወሎ ያቀና ሁሉ እንኳን ደህና መጣህ እንጂ ከየት መጣህ ተብሎ አይጠየቅም፡፡ ልብን በፍቅር በሚያቀልጠው ፈገግታቸው፣ ወሰን በሌለው ደግነታቸው እያቀማጠሉ፣ የተራበውን ያጎርሳሉ፣ የተጠማውን ያጠጣሉ፣ የታረዘውን ያለብሳሉ፣ የደከመውን ያሳርፋሉ፡፡
በቀያቸው ሰንብቶ፣ በቤታቸው አርፎ ወደ መጣበት መመለስ የከጀለውን ደግሞ ስንቅ አስይዘው፣ መንግድ አሳይተው ይሸኙታል፡፡ ያ መልካም ነገር የመላበት፣ ሳይቋረጥ ሶላት የሚሰገድበት፣ አዛን የሚደረስበት፣ ቅዳሴ የሚቀደስበት፣ ምህላ የሚቆምበት የወሎ ምድር በረከቱ ብዙ ነው፡፡ የፈጣሪ ስም ሳይመሰገንበት፣ ፍቅር ሳይነገርበት፣ ደግነት ሳይወጋበት፣ መልካምነት ሳይደረግበት ውሎና አድሮ አያውቅም፡፡
የወሎ ማደሪያው ፍቅር ነው፣ የወሎ መገለጫው ደግነት ነው፣ ከፍቅር የሚያጎድላቸው፣ ከደግነት የሚያወርዳቸው የለም፡፡
የከፋውን ዘመን በብልሃት ያልፉታል፣ የጨለመ የሚመስለውን ወቅት በፍቅር ይሻገሩታል፣ የተቆጣውን ያበርዱታል፣ የተከፋውን ያጽናኑታል፣ የታረዘውን ያለብሱታል፣ የተጨነቀውን ያረጋጉታል፣ ተስፋየ ጨለመ ያለውን ተስፋ ይሰጡታል፣ ብርሃን አጣሁ ያለውን ብርሃን ያሳዩታል፣ ወደ ወሎ አቅንቶ መልካምነት ገብይቶ፣ ሰው አክባሪነት፣ እንግዳ ተቀባይነትን አይቶ የማይመጣ የለም፡፡
ወሎዮዎች ለሚወዷት ሀገራቸው፣ ለሚያከብሯት ሠንደቃቸው የሚሰስቱት ነገር የለም፡፡ ሀገር የሚደፍር፣ በግፍ ወንዝ የሚሻገር ካለም ቁጣቸው ይገነፍላል፣ ፍቅር እንደሰጡት፣ ደግነታቸውን እንዳሳዩት ሁሉ ክንዳቸውን ያቀምሱታል፣ ከደግነት ጋር ጀግንነት፣ ከፍቅር ጋር ጦር አጣምረው እንደያዙ ያሳዩታል፡፡ ሀገራቸውን አብዝተው ይወዷታል፣ ይሳሱላታል፣ ሕይወታቸውን ይሰጡላታል፡፡ እማማ ኢትዮጵያን ከነብሳቸው በላይ እየወደዷት፣ ስሟን ከአንደበታቸው ሳያወጧት፣ እማማ ኢትዮጵያ እያሉ ደጋግመው እየጠሯት፣ ሠንደቃቸውን በልባቸው ጽፈዋት፣ ቃል ለምድር ቃል ለሰማይ ብለው ቃል ሰጥተዋት አይጠግቡም፡፡
የሠንደቃቸውን ፍቅር ለዓለም ያሳዩ ዘንድ በልባቸው መሰሶ ላይ ይሰቅሏታል፣ በምድሯ ላይ ከፍ አድርገው ያውለበልቧታል፣ ይህ አልበቃ ቢላቸው በጭሳቸው ሳይቀር ሠንደቋን ያስጌጧታል፡፡ ወሎ ገብቶ እንኳን ሰዎቹን ጭሳቸውን ላየ ይደነቃል፡፡ በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ አሸብርቋልና፣ ኃያሉ የኢትዮጵያ ሠንደቅ በቤታቸው፣ በልባቸው፣ በጭሳቸው በሁሉም ደምቆ ይውላል፡፡ ለፍቅር የተሰጡ፣ ለፍቅር የተመረጡ ድንቆች ናቸው፡፡
ወሎ መከራ ያበዙብሽን ጠላቶችሽን አሸንፍሽ፣ ክንድሽን አሳይተሸ፣ ፍቅርና ሰላምሽን መልሰሽ እንደ ቀደመው ሁሉ በመዲናሽ፣ በመናገሻሽ፣ በፍቅር ከተማሽ ተውበሻልና እንኳን ደስ ያለሽ፡፡ እንደ አዘንሽ፣ እንደተከፋሽ፣ ሰላምሽን እንዳጣሽ ትኖሪያለሽ ብለው ከበሮ የደለቁት ጠላቶችሽ አፍረዋል፣ ጭንቀትሽ ያስጨነቃቸው፣ ሀዘንሽ ያሳዘናቸው፣ ማሸነፍሽ ደስ ያላቸው ወገኖችሽ፣ ወዳጅ ዘመዶችሽ ተደስተዋልና እንኳን ደስ ያለሽ፡፡ ጎዳናዎችሽ በፍቅር ተመልተዋል፣ ልጆችሽ በአንድነት፣ ለሰላምና ለፍቅር ወጥተዋል፡፡
በወሎዋ መዲና፣ በመናገሻዋ በደሴ ጎዳናዎች በሰው ተሞልተው፣ ሰዎች በፍቅርና በደስታ ተውጠው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ በአንድነት ማድ ተጋርተዋል፣ በጋራ አፍጥረዋል፡፡ አንድነታቸውን፣ ፍቅራቸውንና አብሮነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ተሰብረው ይቀራሉ ያሉትን ጠላቶቻቸውን አሳፍረዋል፣ አንገት አስደፍተዋል፡፡ በቀላሉ የማይሰበር፣ በጠላቶች መብዛት የማይሸረሸር፣ እሴት፣ አንድነት፣ ፍቅርና የሀገር ምስጢር በውስጣቸው እንዳለ አሳይተዋል፡፡ ብርታታቸውን፣ አንድነታቸውን፣ አርቆ አሳቢነታቸውንና ደግነታቸውን በድጋሜ አስመስክዋል፡፡
ቀየው ሰላም ውሎ እንዲያደር፣ ፍቅር እንዲዳብር፣ ሀገር እንዲከበር በዱዓቸው ፈጣሪያቸውን ተማጽነዋል፡፡ ወገናቸውን አስደስተዋል፣ ጠላታቸውን ደግሞ አሳፍረዋል፡፡ ዓይኖቻችሁን ወደ ወሎ አነጣጥሩ፣ መልካም ነገር ታያላችሁ፣ ጀሮቻችሁን ወደ ወሎ አዘንብሉ ፍቅርና ደግነት ትሰማላችሁ፣ መልካም አየሩን ሳቡት ድንቅ የጭስ ማዓዛ ትስባላችሁ፡፡ ሀሴትም ታገኛላችሁ፡፡ ኑ የፍቅር ካባ እናልብሳችሁ፣ ከደግነት ምንጭ እናጠጣችሁ፡፡ የፍቅራችን ካባ አያረጅም፣ ከሚያምረው ውበቱ አይቀንስም፣ ግርማው እንደ አማረ፣ እንደተከበረ ይኖራል እንጂ፡፡ ኑ ከደግነት ምንጭ እናጠጣችሁ፣ የደግነቱ ምንጭ ጥም ይቆርጣል፣ ተስፋ ይሰጣልና፡፡
በፍቅር ሀገር በፍቅር ኑሩ፣ በአንድነት ሀገር በአንድነት ታሪክ ሥሩ፣ መልካምነት በበዛባት፣ ታላቅ ነገር በተቸራት ምድር ተደሰቱ፡፡ ወሎ የፍቅር መጠንሰሻ፣ የደግነት መጎልመሻ፣ ደሴ የመልካምነት መናገሻ፡፡ የደሴ ጎዳናዎችን ያየ ሁሉ ተደስቷል፡፡ ፍቅራቸውን አያጉድልባቸው ሲል ተመኝቷል፡፡ እናንተ የሰላም ሰዎች፣ የፍቅር ዘቦች መልካም ነገር ሁሉ ከእናንተ ጋር ይሁን፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/