
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአውራ አምባ ማኅበረሰብ 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በባሕር ዳር ከተማ ተከብሯል።
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ግዛቸው ሙሉነህ የአውራምባ ማኅበረሰብ ሌብነትን፣ መጥፎ ተግባርንና መጥፎ አስተሳሰብን የሚያወግዙ እሴቶች ያለው ማኅበረሰብ በመኾኑ ተግባሩን ማስፋት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአውራምባ ማኅበረሰብ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኀላፊ ወይዘሮ እናናዬ ክብርት የአውራምባ ማኅበረሰብ ለሰው ልጅ ክብርና እኩልነት ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ፣ ሰውና ሰውነት ላይ በትኩረት የሚሠራ እንደኾነ አስገንዝበዋል።
የማኅበረሰቡ መሥራች ክቡር ዶክተር ዙምራ ኑሩ የአውራምባ ማኅበረሰብ መልካም የሥራ ባሕል እና የሰውልጆችን እኩልነት የሚሰብኩ እሴቶች ባለቤት እንደኾነም ገልጸዋል።
ክቡር ዶክተር ዙምራ እንደሚሉት አስተሳሰቡን ለማሥረጽና በማኅበረሰቡ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ብዙ አስቸጋሪ ፈተናዎች ታልፈዋል። “አስተሳሰባችን ለሰውልጆች ህይዎት፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ የትምህርት፣ የእውቀት እና የሥራ ባሕል ላይ ዋጋ ያለው ተግባር ማበርከት ነው” ብለዋል።
ይህን ለመድረግ ያለፉትን 50 ዓመታት የተሻገሩት አልጋባልጋ እንዳልኾነ ያስረዱት ክቡር ዶክተር ዙምራ ‟የሰው ልጅ ትልቁ ሃብቱ ሰው ነው ብለን እናምናለን፣ ፍቅር መተሳሰብና አንድነት ደግሞ በምድር ላይ ለሰው ልጅ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው” ነው ያሉት፡፡ አስተሳሰቡን ለማስረጽ የሚገድብ ነገር መኖር እንደሌለበትም ገልጸዋል። ‟እንደ ሀገር ለገጠመን ችግርም መፍትሄው በእጃችን እንደሆነ ገልጸዋል።
በምስረታ ክብረ በዓሉ “የማኅበረሰቡ 50ኛ ዓመት ጉዞ ከየት ወደየት” በሚል ርዕሰ-ጉዳይ አወደ ጥናቶች ቀርበዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅና ፋሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ሰይድ ሙሐመድ (ረዳት ፕሮፌሰር) “የአውራምባ ማኅበረሰብ እሴቶችና መርኾዎች ለእውነተኛና ዘላቂ ልማት ያላቸው ፋይዳ” በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ጥናታዊ ጹሑፍ አቅርበዋል።
በጥናታቸውም የአውራምባ ማኅበረሰብ ፍልስፍና መነሻውም መድረሻውም ሰው ነው፤ ለሰው ልጅ ክብር፣ ፍቅር፣ መቻቻልና አንድነት ለተሻለ ህይዎት ብለው ያምናሉ ብለዋል።
ለሰው ልጆች ምቹ ምድር መፍጠር፣ ሰላምና ፍቅር መገንባት፣ በተግባር የሚገለጽ እውነት እንደኾነ ባቀረቡት ጹሑፍ አመላክተዋል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ የአውራምባ ማኅበረሰብ መስራቹን ክቡር ዶክተር ዙምራ ኑሩን ስለሥራ ባለቸው አስተሳሰብ፣ ‘ሥራ ህይወቴ ካልኾነ መኖር ሞቴ ነው’ ካሉት የፈረንሳዩ ፈላስፋ ቮቴር ጋር ያመሳስሏቸዋል።
የአውራምባ ማኅበረሰብ ጥሩ የሥራ ባሕልን በተግባር ያስመሰከረ ነው። የሥራ እኩልነት መርሃቸው ነው። ሰርቶ መለወጥን በተግባር ያሳያሉ፣ የይቻላል መንፈስን የወረሱ ናቸው፣ ሥራን በጾታ አይከፋፍሉም።
ሌብነትን፣ ሳይሠሩ መብላትን ደግሞ ይጸየፋሉ። ካለመሥራት ሞት ይሻላል የሚል አስተሳሰብን ያነበሩ ድንቅ ሰዎች ስለመኾናቸው መመስከር ግዴታዬ ነው ባይ ናቸው።
አውራምባዎች ስለሰው ልጆች ፍቅር፣ስለሰውልጆች መዋደድና እንድነት ያላቸውን ፍልስፍና ድግሞ ከታላቁ ቻይናዊ ፈላስፋ ኮንፊሼስ ጋር ያዛምዱታል። ኮንፊሼስ “እውነት ምንድን ነው” ቢሉት ” ወንድምን መውደድ ነው” አለ የሉናል። “እውቀት ምንድን ነው” ለሚለው ጥያቄም ” እውቀት ወንድምን ማወቅ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥቷል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ አውራምባዎችም ከዚህ ባደገ መልኩ ‘ሰውነትን’ በተግባር አሳይተውናል ይላሉ። የሰው ልጅ ሁሉ ከአንድ የዘር ፍሬ የመጣ ነው ብለው ያምናሉ፤ ስለዚህ ሰው ለሰው ፀጋው፣ ወንድሙ እንጂ እንዴት በሌላ ሊታሰብ ይችላል ባይ ናቸው አውራምባዎቹ።
የፍልስፍና ጥያቄ የሚነሳው ከሰው ልጆች ህይዎት ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሰይድ ችግር ማለት ሃሳብ ያጣ እድል ማለት ነው ይሉታል። የአውራምባ ማኅበረሰብ ደግሞ ይህን ምስጢር በልኩ የተረዳ ነው።
“አውራምባዎች ለ50 ዓመታት ያለግጭትና ያለ መጥፎ ግንኙነት ነው ያለፉት ስንል እነሱ ለሰውልጆች ባላቸው ክብርና ፍቅር ነው ሰላምን ማንበር የተቻላቸው፤ በመተሳሰብና በመረዳት ባሕላቸው ነው፣ ያነን የተሻገሩት” ይላሉ።
ረዳት ፕሮፌሰር ሰይድ ሙሐመድ የአውራምባ ማኅበረሰብ ጥሩ የሥራ ባሕልን፣ የሰው ልጆች ፍቅርና ክብር እሴት ለመገንባት፣ የነበረውንም አጽንቶ ለማቆየት መሰረት ያስቀመጠ እንደሆነ ተናግረዋል።
የይቻላንን መንፈስ የወረሱ፣ በራስ አቅም የመፈጸምን፣ስልጣኔን ከራስ፣ ከአካባቢ አስተሳሰብና ሃብትን ማበልጸግን በተግባር ያሳዩ፣ እንደ ሀገርም ምሳሌነትን የሚወስዱ ናቸው።
ሀገር ዛሬ ላይ የገጠማትን ቀውስና የሰው ልጆችን ክብር ዝቅታ ችግር ለማለፍ ከአውራምባ ማኅበረሰብ ፀጋ መጋራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በትምህርት፣ በጥሩ የሥራ ባሕል፣ በእውቀት፣ በሰውልጆች ፍቅር፣ አንድነትን አምብረው ችግርን ተሻግረዋል ብለዋል። ይህን መልካም እሴቶቻቸውን በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች ማስፋት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአውራምባ ማኅበረሰብ ሰላም፣ ፍቅርና መቻቻል አውራምባ ላይ ብቻ ታጥሮ መቅረት የለበትም መልካም መልካሙን ማብዛትና ማሻገር ያስፈልጋል ብለዋል በምክረ-ሃሳባቸው።
ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/