
ሑመራ: ሚያዚያ 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በየጊዜው እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነት ዜጎች ኑሮአቸውን ለመምራት አዳጋች ሆኖባቸዋል። በተለይም የወር ደሞዝ ጠብቀው ሕይወታቸውን የሚመሩ የመንግሥት ሠራተኞችና በገቢ ዝቅተኛ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ውድነቱ ገፈት ቀማሽ ኾነዋል።
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን በሑመራ ከተማ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ በወቅቱ እየተከፈላቸው ባለመኾኑ በኑሯቸው ላይ ጫና እያሳደረባቸው እንደሚገኝ ለአሚኮ ገልጸዋል።
አቶ ተከታይ ረዳ እና ገነት ፍታለሁ በሑመራ ከተማ የመንግሥት ሠራተኞች ሲኾኑ በ45 ቀን አለፍ ሲልም በኹለት ወር አንዴ የወር ደሞዝ እየተከፈላቸው መኾኑን ገልጸው ደሞዝ በወቅቱ ባለመከፈሉ በኑሮአቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረባቸው መምጣቱን ተናግረዋል።
በተሠማሩበት የሙያ መስክ ማኅበረሰቡን በትጋት እያገለገሉ እንደኾነ የሚናገሩት የመንግሥት ሠራተኞቹ የበጀት አለመኖርና ደሞዝ በወቅቱ አለመከፈሉ በሥራቸውና በኑሮአቸው ላይ ፈተና እንደኾነባቸው ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ለልማት ከሚያውለው በጀት እየቀነሰ ከአንድ ዓመት በላይ በዞኑ ላሉት የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ እየከፈለ እንደሚገኝ የገለጹት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደጋለም ሲሳይ የፌዴራል መንግሥት ለዞኑ በጀት ባለመመደቡ የሠራተኞችን ደሞዝ በወቅቱ ለመክፈልና ልማት ለማልማት እንዳልቻሉ ነው ያስረዱት።
ለዞኑ በጀት እንዲለቀቅ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ አቅርበን ምላሽ አላገኘንም ያሉት ኀላፊው አሁንም ዞኑ በጀት እስኪመደብለት ድረስ ጥያቄያቸውን ማቅረብ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥትም በቅርቡ ምላሽ ይሰጣል ብለው ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የአማራ ክልል መንግሥት ለዞኑ እያደረገ ላለው ድጋፍም በሕዝቡ ስም አመስግነዋል።
ዘጋቢ፡-ያየህ ፈንቴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/