
ሚያዚያ 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር እና የአማራ ባንክ በሳይበር ደኅንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸዉን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ አሥተዳደሩ የሀገሪቱን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት ካላቸው ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት አንጻር በከፍተኛ ሁኔታ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ በመኾናቸው ከባንኮች ጋር በቅንጅት መሥራት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።
የአማራ ባንክ ቴክኖሎጂ ለባንኮች እጅግ ወሳኝ ግብዓት በመገንዘብና የተጋላጭነቱም መጠን ከፍተኛ መኾኑን ተረድቶ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ጋር ለመሥራት ዝግጅነቱን ማሳየቱ የሚደነቅ ነዉ ብለዋል።
ባንኩ በሰው ኀይል፣ በፖሊሲ፣ የቴክኖሎጂ ድጋፎችን እና ትብብሮችን ለማድረግ የሚያስችለዉን የውል ስምምነት መፈረሙ ለሌሎች ባንኮችም በአርዓያነት የሚጠቀስ ተግባር መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የአማራ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ሄኖክ ከበደ ባንካቸዉ የፋይናንስ ሥራዉን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሥራዎች ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄና ደኅንነት የሚያስፈልጋቸዉ ናቸዉ ብለዋል። በዚህ ረገድ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር በኩል የምናገኘዉ ሙያዊ እገዛ ለባንኩ ሥራ ስኬት አጋዥ ይኾናል ነው ያሉት፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር በሳይበር ደኅንነት አሥተዳደር ዙሪያ ከባንኩ ጋር አብሮ ለመሥራት ላሳየዉ ፍቃደኝነት ምሥጋና ያቀረቡት ፕሬዚዳንቱ ሌሎች ከአሥተዳደሩ የሚገኙ የቴክኒክ እገዛዎች ለባንኩ እድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለዉ ተናግረዋል።
በስምምነቱ መሠረት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር በሳይበር ደኅንነት አሥተዳደር ፣ በአይሲቲ አገልግሎት የማማከር፣ የሳይበር ደኅንነት ኦዲት ሥራ የመሥራት፣ በአይቲ ስትራቴጂና ፍኖተ ካርታ ፣ በአይሲቲ አሥተዳደር ፣ ፖሊሲ ማልማት ፣ በሳይበር ደኅንነት ዙሪያ በሚዘጋጁ መመሪያዎች እና ደንቦች ላይ የማማከር ሥራ እንዲሁም የቴክኒክ ስልጠናዎችን ለባንኩ እንደሚሰጥ መገለጹን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/