
ባለቤት ያጣው የረጅም ርቀት መንገደኞች የአካባቢ ብክለት እና መፍትሔው!
በተጓዦች የሚፈፀሙ ብክለቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አለመሥራቱን የአማራ ክልል አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን አስታወቀ።
በሀገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የሚጓዙ መንገደኞች ለረጅም ሰዓታት ስለሚጓዙ በየተወሰኑ ርቀቶች እረፍት ያደርጋሉ። በመሆኑም መንገደኛች በየዕለቱ ጉዟቸው እረፍት ለማድረግና ለመፀዳዳት ከተሽከርካሪዎች ይወርዳሉ።
በጉዞ ላይ የተለየ ክስተት ካልተፈጠረ በስተቀር እረፍት የሚያደርጉባቸው ቦታዎችም የተለመዱ ናቸው። በአካባቢዎቹ ደግሞ መፀዳጃ ቤቶች አልተገነቡም። ይህ በመሆኑም ዓመቱን በሙሉ በየዕለቱ በተመሳሳይ ቦታዎች ላይ መንገደኞቹ የውኃ መያዣ ፕላስቲኮችን ይጥላሉ፤ በአካባቢውም ይፀዳዳሉ።
ይህ ደግሞ አካባቢን በመበከል በኩል ትልቅ ድርሻ አለው።
በአማራ ክልል አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያው ዘላለም መኮንን ለአብመድ እንደተናገሩት በጉዞ ላይ በሚደረጉ እረፍቶች ያለማቋረጥ የሚወገዱ ቆሻሻዎች መሬትን፣ ውኃን እና አየርን ይበክላሉ። በተለይ ፕላስቲክ ደግሞ ለረጅም ዓመታት ስለማይበሰብስ አካባቢን በመበከል ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል። ሌሎች ቆሻሻዎችም ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ ወደ ወራጅ ምንጮች በመግባት እንደ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውኪያ፣ አንጀትን ለሚያቆስሉ ትላትሎችና ሌሎች የጤና እክሎችን ይፈጥራሉ ነው ያሉት፡፡
በባለስልጣኑ የአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ዳይሬክተር አበባው አባይነህ በጉዞ ላይ የሚካሄዱ በካይ ተግባራትን ለመከላከል በኩል በትኩረት እንዳልሰሩ ነው የተናገሩት፡፡ ከክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በጋራ ለመሥራት ጥረት ማድረጋቸውንም አስረድተዋል። ከአሽከርካሪ ባለንብረቶች ጋር ስለመፍትሔው መመካከር እንደሚፈልጉ በስልክና በደብዳቤ መጠየቃቸውን፣ ምላሽ ግን አለማግኘታቸውንም ነው የተናገሩት።
አሠራርን በማስተዋወቅ የውኃ መያዣ ፕላስቲኮች ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ እና ወጣቶችን አደራጅቶ መናፈሻዎችን በመክፈት የስራ እድል መፍጠርን አማራጭ በማድረግ መፍትሔ መስጠት እንደደሚገባም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ውቤ አጥናፉ “በክልሉ አካባቢ ጥበቃ ቢሮ በኩል በጉዞ ላይ በተጓዦች የሚፈጠር ብክለትን ለመከላከል ተባበሩን የሚል ጥያቄ በደብዳቤ፣ በአካልና በስልክ ቀርቦልን አያውቅም (አልደረሰንም)፤ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ ነን” ብለዋል፡፡ ቢሮው ለመፍትሔው ለመሥራት ዝግጁ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
የክልሉ አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣንም ሆነ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ችግሩን ከመናገር ያለፈ ተግባራዊ ሥራ እየሰሩ አለመሆናቸውን አብመድ ታዝቧል። የሁለቱ ተቋማት መገፋፋትም መፍትሔ በመስጠት በኩል አሠራርም ሆነ መናበብ አለመኖሩን ያሳያል።
በኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 159/2001 እንደተመላከተው ማንም አካል አካባቢውን መበከል አይችልም፤ ጉዳት ካደረሰም እንዲያገግም የማድረግ ኃላፊነት አለበት። የአካባቢ ብክለት አዋጅ ቁጥር 300/1995 ደግሞ ወደ አካባቢ የሚለቀቁ በካይ ነገሮች አካባቢው ከሚሸከመው በላይ መሆን እንደሌለባቸው ይጠቅሳል።
በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ከ 517 እስከ 521 ያሉት አንቀፆችም የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮችን እና የሚያስከትለውን የሕግ ተጠያቂነት የሚያብራሩ ናቸው፡፡ በኃላፊነት ደረጃ ያሉ አካላት በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚጠበቅባቸውን ካላከናወኑ የገንዘብ ቅጣትን ጨምሮ የእስራት እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም በህጉ ተጠቅሷል፡፡
ዘጋቢ፦ ኪሩቤል ተሾመ