
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ)የጭንቅ ቀን ደራሽ፣ የእናት ሀገር ደም መላሽ፣ ከልጅነቱ እስከ ሞቱ ድረስ ኢትዮጵያን ያለ፣ በንግሥናው እረፈት ያጣ፣ እንደ ንጉሥ ያልተቀናጣ፣ ለሀገር ዘብ የተፈጠረ፣ ለሀገር ክብር የኖረ፣ ታላቅ ታሪክ፣ ድንቅ ገድል ለልጅ ልጅ ያኖረ፡፡ ገና በለጋ እድሜው ጥበብን የመረመረ፣ ሩቅ በሚያራምድ ራዕይ የከበረ፣ ለራዕይ መሳካት፣ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ጽናት እና አይደፈሬነት ሲኳትን የኖረ ኃያል ንጉሥ፡፡
የቁጣውን ድምጽ የሰሙት ይንቀጠቀጣሉ፣ የኃያልነቱን ነገር የተረዱት ይርዳሉ፣ ሽፍታ የደበቁት ጫካዎች፣ ወንበዴ ያጠራቀሙት ዋሻዎች ያ ኃያል ሰው መጣ ሲባል ይገለጣሉ፣ የደበቁትን አሳልፈው ይሰጣሉ፣ በእርሱ ፊት የሚቆም ከቶ አይገኘም፡፡ ሀገር ለመበተን የሚታትሩት ባንዳዎች ሲሰሙት ብርክ ይዛቸዋል፡፡ ተኩሶ የማይስተው፣ ጎራዴው የሚቀላው፣ የሀገር ድንበርና ክብር ለመንካት የሚጥረውን ጠላት የሚቀጣው፣ የሀገርን አንድነት የሚያልመው፣ ለሀገርም አንድነት ያለ ድካም የሚሰራው ኃያሉ ንጉሥ፡፡
ለሀገሩ ተፈጥሮ፣ ለሀገሩ ኖሮ፣ ለሀገሩ የሞተ፣ ለሀገር ክብርና አንድነት የተንከራተተ ይሉታል፡፡ በዚያ ዘመን የዙፋን አቅም ተዳክሞ፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ ጉልበት አውጥተው፣ የራሳቸውን ግዛት አስፍተውና ለክተው ይኖሩ ነበር፡፡ አንደኛው መሥፍን ከሌላኛው መሥፍን አለመግባባት በፈጠረ ቁጥር ጦርነት እያነሱ፣ ጎራ ለይተው ይጋጩ ነበር፡፡ አንተም ተው አንተም ተው የሚል ኃያል ንጉሥ አልነበረምና እማማ ኢትዮጵያ በልጆቿ ጠብ ትታመስ ነበር፡፡
አራሹ ገበሬ በመሥፍኖች አለመስማማት መከራው ጸንቶበታል፣ በደሉ አይሎበታል፣ አንደኛው አሸንፎ ወደሌላኛው ቀየ በዘለቀ ቁጥር ሀብትና ንብረቱ እየተዘረፈበት፣ ቤቱ እየተቃጠለበት መከራው አይሎበታል፡፡ ከሁሉም በቀደመች፣ በተከበረችና በታፈረች ሀገር የሚያስፈራ ንጉሥ ከሚያስፈራው ዙፋን ላይ ይቀመጥ ዘንድ ተፈልጓል፡፡ ታቦቱን ከመንበሩ፣ ንጉሡን ከወንበሩ አታሳጣን እያለ የሚጸልየው የሀገሬው ሰው የሚያስፈራ፣ አንተም ተው አንተም ተው እያለ በእኩልነት የሚመራ፣ ኃያል ንጉሥ ይሻልና እንባውን ወደ ጸባዖት ይረጫል፡፡ ፈጣሪ አንድነታቸውን የሚመልስላቸው፣ የስቃይ ዘመናቸውን የሚቋጭላቸው፣ ሰላማቸውን የሚያመጣላቸው፣ አርሰውና አፍሰው እንዲበሉ የሚያደርጋቸው ንጉሥ ይሰጣቸው ዘንድ ጸሎት ላይ ነበሩ፡፡
የጥይት ድምጽ ሰልችቷቸዋል፡፡ መሳደድና ጉልበት ባወጣ መስፍን መገፋት አስመርሯቸዋልና በምድሯ ኃይል ንጉሥ ተናፍቋል፡፡ የመሥፍኖች ዘመን ልትቋጭ ቀረበች፣ መሣፍንቱን የሚያስደነብር፣ ሀገር የሚያስከብር ኃያል ሰው የመወለጃው ዘመን ደረሰ፡፡ እረኞች በዋሽንታቸው እያዜሙ፣ ከከብቶቻቸው ሥር ሥር እየተከተሉ፣ በጋራውና በሸንተረሩ እየወጡ ኃያል ንጉሥ እንደሚነሳ ትንቢት ይናገሩ ጀምረዋል፡፡ ለወትሮው የእረኞች ትንቢት እውን እንደሚሆን ይታመናልና፣ የሀገሬው ሰው ፈጣሪ ልመናችንን ሰማን ሲል መደሰት ጀምሯል፡፡
ትንቢቱ እንደሚደርስ፣ ኃያሉ ንጉሥ ሁሉንም አሸንፎ እንደሚነግሥ፣ የመሳፍንቱን ዘመን እንደሚገረስስ የገባቸው መስፍኖች ጭንቀት ይዟቸዋል፡፡ የትንቢቱ መፈጸሚያ ዘመን እንደቀረበ ተረድተዋልና ውስጥ ወስጡን መጨነቅ ጀምረዋል፡፡ ገሚሶቹ ደግሞ ማነው ወንዱ እኛ እያለን የሚነግሥ እያሉ ከትንቢቱ ለመራቅ ይሞክራሉ፡፡ በጉጉት ለሚጠብቁትም፣ በፍርሃት ለተዋጡትም ምላሽ የሚሰጥበት ዘመን ደረሰ፡፡
እመቤቷ አትጠገብ ዘጠኝ ወር ያረገዙትን ልጃቸውን ሊገላገሉ ምጥ ይዟቸዋል፡፡ ጎረቤት ሁሉ ምጥ ወደ ተያዙት እናት ቤት አቅንቷል፡፡ ከምጥ በኋላ ደስታ ቢኖርም በምጥ ጊዜ ጭንቀት አለና ጭንቅ ብለዋል፡፡ የደስታው ጊዜ ደረሰ፡፡ ሲያስጨንቅ የነበረው ልጅ ምድርን ተቀላቀለ፡፡ እልልታው ቀለጠ፡፡ እረኞች በትንቢታቸው ገፉበት፣ ትንቢተኛው ልጅ እንደተወለደ ያለ ማቋረጥ ዘመረ፣ ተናገሩ፡፡ የተበደለችውን ሀገር የሚክስ ልጅ ነበርና አዲስ የተወለደው ልጅ ካሳ ተባለ፡፡ ካሳ በእናቱ ጥበብ አደገ፡፡ የቤተክህነቱን ትምህርት በሚገባ ተከታተለ፡፡ በዚያም ጊዜ የሀገሩን በደልና መከራ ተገነዘበ፡፡ ለእማማ ኢትዮጵያ ይደርስላት ዘንድ ራዕይ ሰነቀ፡፡ እናቱም ራዕይ አስታጠቀችው፡፡ ከሹርባው ጋር ቃል ኪዳን አሥሮ ሀገሩን አንድ ያደርግ ዘንድ ተነሳ፡፡
በፍቅር የመጡትን በፍቅር፣ በጦር የተነሱትን በጦር እያስተካከለ ጉዞውን ጀመረ፡፡ እስከ ሞት ድረስ የሚታመኑ፣ እንደ አንበሳ የጀገኑ፣ እንደ ነብር የፈጠኑ ታማኞች ተከተሉት፡፡ ይባስ ብሎ አይዞህ ካሳ የምትለው የራዕዩ ታጋሪ የሆነች እመቤት ለግራ ጎኑ ተሰጠችው፡፡ ልዕልቷ ተዋበች ካሳን አበረታችው፡፡ አይዞህ ሂድ አለችው፡፡ ብልህ ሚስት፣ ጀግና የጦር ባለሟሎች ፈጣሪ ስላደለው ካሳ ደስ አለው፡፡ በአሸናፈነት ብቻ ገሰገሰ፡፡ በእረኞች ትንቢት አስቀድመው የተጨነቁትም ሆነ የተሳለቁት መስፍኖች አንድ ባንድ ወደቁ፡፡ ካሳን የሚያቆመው ጠፋ፡፡ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ራዕይም ሰነቀ፡፡ ምኞት ያለ ሥራ አይሳካምና ሳይሰለች ለፋ፣ ደከመ፡፡ መሳፍንቱን ገርስሶ፣ የመከፋፈሉን ገመድ በጣጥሶ ካሳ ተዋበችን ከጎኑ አድርጎ፣ በእነ ገብርዬ፣ በእነ አለሜ፣ በእነ ገልሞና በብዙ የጦር አበጋዞቹ ተውቦና ታጅቦ በደረስጌ ማርያም ንጉሠ ነገሥት ኾኖ በአስፈሪው ዙፋን አስፈሪው ሰው ተቀመጠበት፡፡ ስሙም ቴዎድሮስ ተባለ፡፡ ዘመነ መሳፍንት ተፈጸመ፡፡
የአንድነቱ መሠረት ዳግም ቆመ፡፡ ቴዎድሮስ እንደ ንጉሥ ሳይኩራራ፣ አባቶቹ ባሰሩት በጎንደር ቤተ መንግሥት በክብር መቀመጥን ሳይመርጥ ለሀገር አንድነትና እድገት በየሀገሩ ተንከራተተ፡፡ በእርሱ ዘመንም አያሌ አዳዲስ ነገሮችን አስጀመረ፡፡ የኢትዮጵያን የዙፋን መዳከም አይተው ኢትዮጵያን ለመውረር፣ ሕዝቧንም ለማስገበር ሲከጅሉ የነበሩት የውጭ ኃይሎች እጃቸውን ሰበሰቡ፡፡ እንደ እሳት የሚያቃጥል፣ እንደ አንበሳ ሰባብሮ የሚጥል ንጉሥ ተነስቶላታልና እርሷን ማን ነክቷት፡፡
ቴዎድሮስ ከውስጥና ከውጭ የሚነሳውን ጠላት እያስታገሰ ራዕዩን እውን ያደርግ ዘንድ ያለ እረፍት ደከመ፡፡ በጠላት የተከበበች ሀገር ጠንካራ ሠራዊትና ዘመናዊ መሳሪያ ይኖራት ዘንድ ግድ ይል ነበርና በሚወዳት ሀገሩ ዘመናዊ መሳሪያ አሠራ፡፡ አዲስ የሆኑ ለውጦችንም አሳየ፡፡ ዳሩ ጠላቶች እንደ አሸን እየበዙበት፣ ጊዜ እያሳጡት ሄዱ፡፡ አይዞህ እያለች የምታበረታታው፣ የልብ አውቃ የሆነችው ባለቤቱ ተዋበች የሞት መላእክን ተከትላ ሄደችበት፣ ከአጠገቡ ተለየችው፡፡ በተዋበች መሞት የቴዎድሮስ ልብ አብዝታ አዘነች፡፡ ጀግናው እንባ አውጥቶ አለቀሰ፡፡ ሰው ቢሆን የወሰዳት አጣድፎ ባስመለሳት ነበር፣ ዳሩ ፈጣሪ ነውና ቴዎድሮስ አዝኖ ዝም አለ፡፡ ሀዘን የገባው ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ከመሥራት ግን አልቦዘነም ነበር፡፡ የውስጥ ጣላቶች ከውጭ ጠላት ጋር ተመሳጥረው ጠላት አስገቡበት፡፡ ለሀገራቸው ንጉሥ ለዚያውም ባለ ራዕዩን መደገፍ ሲገባቸው እነርሱ ግን ውድቀቱን ተመኙ፡፡ ጠላት ጠሩበት፣ ጠላት ሆነውም ተነሱበት፡፡ ራዕዩን እንዳይኖር ሥራ አበዙበት፣ ጦር አዘመቱበት፡፡
ወረሃ ሚያዝያ ደርሷል፡፡ የሀገሬው ሰው የሁዳዴን ( የዐቢይ) ጾም ሲጾም ከርሞ የትንሳኤውን በዓል ለማክበር ዝግጅት ላይ ነው፡፡ የሀገሩ ነገር እንልቅፍ የነሳው ኃያሉ ንጉሥ ሀገሩን ልቡ ላይ ጽፎ መቅደላ አፋፉ ላይ ተቀምጧል፡፡ መላም እየዘየደ ነው፡፡ ብዙዎች እየከዱ ከእርሱ ተለይተዋል፡፡ ብዙዎች መንገድ መሪ ሆነው መጥተዋል፡፡ ከነብሱ አስበልጦ የሚወዳት ሀገሩ አሳዘነችው፡፡ ላይከዳት ቃል አለውና ነብሱን ጭምር ሊሰጣት በልቡ ድጋሜ ቃል ገባላት፡፡
የእንግሊዝ ሠራዊት በሀገር ውስጥ ባንዳዎች እየተመራ ወደ መቅደላ ቀርቧል፡፡ ጦርነቱ ተጀመረ፡፡
በወረሃ ሚያዝያ በ6ኛው ቀን ረፋድ አካባቢ ጸሐይ ዙሪያዋን በጥቁር ክበብ ተከባ አየ፡፡ ይህ ነገር ደም የመፍሰስ ምልክት ነው ብሎ ተናገረ፡፡ የባለራዕዩ ንጉሥ ጀንበር ያዘቀዘቀች መስላለች፡፡ በገብርየ የሚመራው ሠራዊት እየተዋጋ ነው፡፡ በዚያም ጊዜ የቴዎድሮስን ልብ የሚሰብር ዜና ከጦር ሰፈር ደረሰው፡፡ ቃሉን የማያብለው፣ ለጦር ስልት የታደለው፣ ማተቡን የማያላለው፣ ፍርሃት ያልፈጠረበት፣ ጠላት የሚበረግግለት፣ ማሕተቡን ማንም ያላላበት ታማኙ ገብርየ፣ ለሀገሩ ክብር፣ ለሠንደቁ ፍቅር፣ ለእምነቱና ለማንነቱ ሲል እንዳሸለበ ሰማ፡፡ ገብርዬ ወይኔ ጌታየ፣ ወይኔ ጓዴ፣ ወይኔ ማዕረግ የልብህን መሻት ሳልሞላ ጥየህ መሄዴ ነው ብሎሃል አሉት፡፡
ታማኝን እንደማጣት ምን የሚያሳዝን ነገር አለ? ተዋበች ያሳዘነችውን የቴዎድሮስ አንጀት ገብርየ አባሰው፡፡ ቴዎድሮስ በዚያ ጀግና መሞት አብዝቶ አዘነ፡፡ አብዝቶ አለቀሰ፡፡ በንጉሡ የሚደነቅ፣ ጀግንነቱ የረቀቀው ገብርየ ካሳን ያለ ሰው ጥሎት አሸለበ፡፡ ጀንበር ጠለቀችበት እንጂ እርሱስ ቴዎድሮስን ጥሎ መሄድ አያውቅም ነበር፡፡ ዳሩ ሞት ቀደመው፡፡
የቴዎድሮስ ጀንበር አዘቀዘቀች፣ በጥቁር ደመና ተሸፍና ጨለማ ልታላብስ፣ ጀርባዋን ሰጥታው ልትገሰግስ ተፋጠነች፡፡ ክንደ ብርቱው ንጉሥ በመቅደላ አፋፍ ላይ ብቻውን አሰበ፡፡ ጠላት እንደ ቆሎ የጨበጠው ነበልባል ክንዱን ማንም እንደማይዛት፣ ማንም እንደማይደፍራት፣ ከልቡ ጋር መከረ፡፡ የቴዎድሮስን ክንድ መንካት፣ እርሱን አሸንፎ ድል መሻት አይታሰብምና፡፡
የፋሲካ ቀን ቀርቧል፣ ሕዝቡ በዓሉን ለማክበር ሽርጉድ ላይ ነው፡፡ ሙክት ያለው ሙክቱን ሊያርድ አስቧል፣ ከጋጡ ሙክት የሌለው ደግሞ ወደ ገበያ ወጥቶ የፋሲካ ቀን የሚጣለውን እርድ እያሰበ ነው፡፡ ቴዎድሮስ ግን እንደሚያምነው እንደጌታው ራሱን ለኢትዮጵያ አሳልፎ ሊሰጥ ወዷል፡፡ ቴዎድሮስ ገብርዬን ሊከተለው ወደደ፡፡ ከወገቡ ላይ የማትለየውን ሽጉጡን ቁልቁል ተመለከታት፡፡ ከሰገባው መዝዞ፣ ለግዳይ አዘጋጅቶ ጨበጣት፡፡ የመቅደላ ሰማይ ሊጨላለም፣ የኢትዮጵያ ራዕይና የማደግ ተስፋ በጉም ሊጋረድ ቀረበ፡፡ ኢትዮጵያየ እወድሻለሁ ሲል ፍቅሩን ገለጸላት፡፡ የጨበጣትን ሽጉጥ አፈሙዟን አቃንቶ ጎረሳት፡፡ ምላጯንም ተጫናት፡፡ ቴዎድሮስ ስለ ክብር፣ ስለ ሀገር፣ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፣ ስለሰጣት የማይሻር እመነት ሲል ራሱን ሰጥቶ ፍቅሩን ገለፀላት፡፡
ታላቁ ዋርካ ወደቀ፡፡ ጀንበር ጠቋቆረች፣ ኢትዮጵያ ባለ ራዕዩ ልጇን አጣች፡፡ ጥላና ከላላዋን ተነጠቀች፡፡ አብዝታም አዘነች፡፡ ʺዓርባ ቀን ጦም ጦሞ ፋሲካ ሲደርስ፣
ባፈር ገደፈ አሉ የአበሻ ንጉሥ” ሲሉ ተቀኙለት፡፡ በፋሲካ ጮማ መቁረጥ፣ ጠጅ መጠጣት፣ በማርና በወተት ዓለምን ማየት አልፈለገም፡፡ ጦም ሲጦም ከርሞ ፋሲካ ሲዳረስ ቴዎድሮስ በአፈር ገደፈ፡፡
ʺአያችሁልኝን የአንበሳውን ሞት፣
በሰው እጅ መሞትን ነውር አድርጎት “በሰው እጅ መሞት፣ ለጀግና እጅ መስጠት ነውር ነውና ቴዎድሮስ ክንዱን ማንም ሳይነካት፣ ሕይወቱን ማንም ሳይደፍራት፣ ወንድነቱን ራሱ ጀምሮ ራሱ ጨረሳት፡፡
ቴዎድሮስ ስጋው ሞተ እንጂ ራዕዩና መንፈሱ ግን ዛሬም አለ፡፡ ዛሬም ልጆቹ ራዕዩን ያስቡታል፣ ዛሬም ልጆቹ በስሙ ይምሉበታል፡፡ ለሀገር አንድት የተከፈለውን ዋጋ አይረሱትም፡፡ ኃያሉ ንጉሥ ስለ ክብር ሞትን የተቀበለው በወረሃ ሚያዝያ በ6ኛዋ ቀን ነበር፡፡ እነሆ ቀኗ ዛሬ ናትና ልናስበው ወደድን፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/