ነጻነታቸውን አስጠብቀው ለመዝለቅ ትጥቃቸው ከወገባቸው ሳይፈታ፣ ዓይናቸው ከጠላት ላይ የማይነቀለው የወልቃይት ጠገዴ ሚሊሻዎች።

401

ሑመራ: ሚያዚያ 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በሥልጣን ላይ በቆየበት ዘመን ወደ ወልቃይት ጠገዴ ምድር ዘልቆ በመግባት የተራቆተ ኅሊናውን አንግቦ፣ የማይሞላ ከርሱን ሊያጠግብ፣ ነጭ ወርቋን ሊቀራመት፣ በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ ሴት ሳይል ወንድ፣ ሼህ ሳይል ካህን ከሊቅ እስከ ደቂቅ የግፍ ጽዋ እንዲጋቱ፣ በመከራ ጅራፍ እየገረፈ የቻለውን አጥፍቶ ያልቻለውን ቤትና ንብረቱን ዘርፎ ለስደት ሕይወት እንዲጋለጡ አድርጓል።

የአሸባሪ ቡድኑ ጭቆና ያልበገራቸው፣ የጨለማ ግዞቱ ያልሰበራቸው፣ አልጠግብ ባይ ሆዱን፣ ስግብግብነቱን የተረዱትና የሕዝባቸውን የምሬት እንባ ማየት የመረራቸው፣ ብሶት የወለዳቸው የበርሃ አናብስቶቹ የወልቃይት ጠገዴ ጀግኖች ውሏቸውን ጫካ ማደሪያቸውን ዋሻ አድርገው ለ30 ዓመታት የታፈነ ማንነታቸውን ባሕልና ወጋቸውን ለማስመለስ በየተራራውና በየሸለቆው ተዋድቀዋል።

የሽብር ቡድኑ ሴራ የገባቸው የወልቃይት ጠገዴ ጀግኖች ለ30 ዓመታት የዘረጉትን ሳያጥፉ ያቀባበሉትን ሳይመልሱ የታጠቁትን ሳይፈቱ ሲታገሉ ኖረዋል።

የእናት ጡት ነካሽ የኾኑት የሽብር ቡድኑ አባላት የሥልጣን ጥማቸው የግፍ ጽዋቸው ሞልቶ ፈሰሰና የኢትዮጵያ አሌንታ፣ የሕዝብ ትርታ በኾነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የክህደት በትራቸውን አሳርፈው በሥልጣን ዘመናቸው በዘር በቋንቋና በጎጥ የከፋፈሉትን ሕዝብ አንድ አደረጉት።

ለ30 ዓመታት ማንነቴ አማራ፣ ደሜ ኢትዮጵያዊ ነው የአባቶቸን ርስት አልሰጥም ብሎ ራስ ምታት የኾናቸው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከወገን ጦር አባላት ጎን በመሰለፍ ወራሪውን የትግራይ ቡድን በመደምሰስ ሙትና ቁስለኛ አድርገው ነጻነታቸውን ተጎናጽፈዋል።

የነጻነት አየርን መተንፈስ ከጀመሩ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠሩት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን የሚሊሻ አባላት ዛሬም ነጻነታቸውን አስጠብቆ ለመዝለቅ ትጥቃቸው ከወገባቸው ሳይፈታ፣ ዓይናቸው ከጠላት ላይ ሳይነቀል፣ አፈሙዛቸው በጠላት ላይ እሳት ሊያዘንብ እንደተነጣጠረ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ።

ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት የሚሊሻ አባል አስማማው ደርሶ የሽብር ቡድኑን የክፋት ሴራ ስለምናውቅ ሳንዘናጋ ቀን ከሌሊት ወራሪውን ቡድን ለመደምሰስ በተጠንቀቅ ላይ ነን ብለዋል።

እባብ ለመደ ተብሎ በኪስ አይያዝም ያሉት የሚሊሻ አባላቱ ወራሪው ቡድን የቻለውን በኃይል ያልቻለውን በፕሮፓጋንዳ አለፍ ሲልም ቅቤ ምላሱን ተጠቅሞ እንደ እስስት ቀለሙን በመቀያየር ከውስጥ ባንዳዎች ከውጭ ጠላቶች ጋር ተመሳጥሮ አማራን ብሎም ኢትዮጵያን ከማጥፋት አይቦዝንምና ይኼን ወራሪ ቡድን ለመደምሰስ በተጠንቀቅ ላይ ነን ብለዋል።

የሚሊሻ አባል ፀሐየ አለምነህ የሽብር ቡድኑን ለ30 ዓመታት ስንታገል ኖረናል አሁን ያገኘነውን ነፃነት አስጠብቆ ለመዝለቅ ቀን ከሌሊት በተጠንቀቅ ላይ ነን ብለዋል።
ጦርነቱ ገና አልተጠናቀቀምና የአማራ ሕዝብ ኹሌም በተጠንቀቅ ላይ ሊኾን እንደሚገባ የሚሊሻ አባላቱ አሳስበዋል።

የሑመራ ከተማ አስተዳደር የሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መቶ አለቃ ወርቁ ጀግኔ የሚሊሻ አባላቱ ከኹሉም የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ግንባር ድረስ በመዝመት፣ በኬላ ፍተሻና የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረጉ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ወራሪውን ቡድን ለመደምሰስ የሚሊሻ አባላቱ በተጠንቀቅ ላይ መኾናቸውን የገልጸዋል። ኀላፊው መላው የአማራ ሕዝብ በአሸባሪው ቡድን የሚደርስበትን ጥቃት ለመመከት ሁሌም ዝግጁ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ፡-ያየህ ፈንቴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች የሚውል 300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አጸደቀ።
Next articleየተፈናቃዮችን የመጠለያ እና የቁሳቁስ ችግር ለመፍታት እየሠራ መኾኑን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡