ከአንድ ዓመት በላይ ያለኤሌክትሪክ ኀይል የዘለቁት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ነዋሪዎች መፍትሔ እንዲሰጣቸው አኹንም እየጠየቁ ነው፡፡

190

ሑመራ : ሚያዝያ 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን የግዞት ዘመን የተላቀቁት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ነዋሪዎች በሽብር ቡድኑ ጥፋት ምክንያት ከኤልክትሪክ ኀይል አገልግሎት ውጭ ከኾኑ ከአንድ ዓመት በላይ ተቆጥሯል፡፡ ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ተመትቶ ተከዜን የተሻገረው የሽብር ቡድኑ ለዞኑ የኤልክትሪክ አገልግሎት ይሰጥ የነበረውን መሥመር ሽሬ ላይ አቋረጠው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በሽብር ቡድኑ የኤልክትሪክ ኀይል የተቋረጠባቸውን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ነዋሪዎች ጥያቄ ሳይፈታው ከአንድ ዓመት በላይ ተቆጥሯል፡፡
የኤሌክትሪክ ኀይል እጦቱ የነዋሪዎቹን ኑሮ አክብዶታል፡፡ እናም የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኀይል እንዲቀርብላቸው በተደጋጋሚ እየጠየቁ ነው፡፡ በሌሎች አካባቢዎች የሽብር ቡድኑ ውድመት ያደረሰባቸውን የኤሌክትሪክ ኀይል ማስተላለፊያዎችን በፍጥነት እየጠገነ ነዋሪዎቹን ተጠቃሚ እያደረገ ያለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል የወልቃይትን ጥያቄ ለመመለስ ግን ተስኖታል፡፡
ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን በተጨማሪ የላልይበላ እና የዋግኽምራ የኤሌክትሪክ ኀይል ምላሽ ያጡ ጥያቄዎች ኾነዋል፡፡
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በክልሉ የሚነሱ የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ጥያቄዎችን እንዴት ነው የሚፈቱት ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይልን ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ በሽብር ቡድኑ ምክንያት አላማጣ ላይ ኀይል ከተቋረጠ በኋላ ላልይበላ እና ሰቆጣ የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኙ አይደለም ብለዋል፡፡ ላልይበላን በጄኔሬተር መብራት ለመስጠት የተደረገው ሙከራ በነዳጅ አቅርቦት ምክንያት መስጠት አለመቻሉንም አስታውቀዋል፡፡
አቶ አሸብር ላልይበላ፣ ሰቆጣ እና ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ኀይል የሚያገኙት በሽብር ቡድኑ በተያዙ አካባቢዎች ከሚነሱ መሥመሮች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የተቋረጠውን ኀይል መሥራትና ማስተካከል አለመቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡ ወልቃይት ጠገዴ ከሽሬ ከሚነሳ የኤሌክትሪክ ኀይል ያገኝ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ችግሩን በቀላሉ ለመፍታት መቸገራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ አላማጣ ያለውን መሥራት እስካልተቻለ ድረስ ሰቆጣን የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ እንደማይቻልም ነው ያስታወቁት፡፡
ለላልይበላ ሌሎች አማራጮችን እያዩ መሆናቸውን እና በቅርብ ሊፈቱት እንደሚችሉም ተናግረዋል ዋና ስራ አስፈፃሚው፡፡ ለወልቃይት ጠገዴ መፍትሔ እንስጥ ብንል እንኳን ረጅም ጊዜ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡ ሊሰጥ የሚችለው መፍትሔ ከጎንደር ኀይል በመዘርጋት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በአጭር ጊዜ ግን መፍትሔ መስጠት እንቸገራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የወልቃይት ጠገዴን ችግር እንገነዘባለን ያሉት ሥራ አስፈጻሚው ምን ማድረግ እንዳለብን ተቸግረናል፤ የሚፈልገው ኢንቨስተመንት በጣም ትልቅ ነው፤ ኢንቨስትመንቱም ቢገኝ ለግንባታ ጊዜ ይወስዳል፤ የአጭር ጊዜ መፍትሔ የለውም፤ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ሊኖረው የሚችለው በጄኔሬተር ኀይል ማቅረብ ወይም በሶላር ያለውን ኃይል መጠቀም ሲቻል ነው ብለዋል፡፡
አቶ አሸብር አጭርና የተቀላጠፈ መፍትሔ የሚሰጥ ከሆነ ከመተማ መውሰድ የሚቻልበትን መንገድ በድጋሜ ልናየው እችላለንም ብለዋል፡፡ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለመፈፀም የበጀት ችግር እንዳለም አስታውቀዋል፡፡ ዘላቂው መፍትሔ እስኪመጣ ድረስ በጄኔሬተር መፍትሔ ለመስጠት ከክልሉ መንግስት ጋር መነጋገር ይጠበቅበናልም ነው ያሉት፡፡ የዶላር አቅርቦት ካለና ገንዘቡ በፍጥነት ከተሳካልን ከጎንደር የሚሄደውን ፕሮጄክት ማሳካት እንችላለንም ብለዋል፡፡ ለበጀትና ለዶላር ጉዳይ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ትልቅ ድርሻ አለበት ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንዲሁም የጤና ሥርዐት ለመዘርጋት ካናዳ እገዛ እንደምታደርግ ገለጸች።
Next articleከ58 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ መጀመሩን በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ማሕበራዊና ልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡