ግዞተኛው ልዑል!

205

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) “ምስኪኑ ልጅ ፍርሐቱ አለቀቀውም፡፡ የመቅደላውን እልቂት እና የአባቱን ሞት ስላየ ሁነቱ በአዕምሮው ይመጣበታል” ንግሥት ቪክቶሪያ የባለ ራዕይ ልጅ መኾን መከራው ብዙ ነው፡፡ የንጉሥ ልጅ መሆን ተድላ እና ደስታ የበዛበት ቅንጡ ሕይዎት ቢመስልም ንግሥናቸው ለሀገራቸው እንጂ በሕዝባቸው ላይ ካልኾኑ መሪዎች ዘንድ ለሚወለዱ ልጆች ያን ያክል ምቹ አይደለም፡፡ እንደዛሬው ሳይኾን የተወሰኑ የነገሥታት ልጆች የወላጆቻቸውን ፍቅር ስለሀገር ሲባል መስዋእት ያደርጋሉ፡፡ በአብዛኛው ነገሥታት ልጆች ርሃባቸው ምግብ ሳይሆን ሰው ሰው የሚሸት ተራ ኑሮ ነበር፡፡

የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ አንጥረኛ የነበሩት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ከሴቫስቶፖል እና ከልዑል ዓለማየሁ ማንን እንደሚያስበልጡ እንጃ እንጂ ልጅ ነበራቸው፡፡ ልጁን የሚጠላ ኢትዮጵያዊ ወላጅ ይኖራል ተብሎ ባይታሰብም ንጉሡ ልጃቸውን አብዝተው እንደሚወዱት ይነገራል፡፡ ከተዋበች የቀረው የልጅ ፍቅር በጥሩወርቅ እውን ሆኖላቸው ደስታቸው ብዙ ነበር አሉ፡፡
ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ከአባቱ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ እና ከእናቱ ወይዘሮ ጥሩወርቅ ውቤ ሚያዚያ 5/1853 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ ተወለደ፡፡ የልዑሉ መወለድ ደስታው ለቤተሰቦቹ ብቻ ሳይሆን ስለመወለዱ ሲባል ከእስር ለተለቀቁት እስረኞችም ጭምር ነበር፡፡ በደብረ ታቦርም የደስታ መገለጫ በርከት ያለ መድፍ እና ጥይት ተተኩሷል፡፡

በወላጆቹ ፍቅር በአካል እና በሞገስ እየጎለመሰ የመጣው ልዑል አባቱ ባለ ራዕይ ነበሩና በአንድ አካባቢ እረግቶ የሚያድግበት ዕድል ግን አላገኘም፡፡ አባቱ ሽፍታን ከማሳደድ፣ ቴክኖሎጂን ከማላመድ እና ሀገራዊ እርቅን ከማውረድ በተረፈቻቸው ትንሽ ጊዜ ኹሉ ከልጃቸው ጋር ማሳለፍን እንደሚመርጡ ግን ይነገራል፡፡ ከጋፋት እስከ መቅደላ በተዘረጋው የንጉሡ የለውጥ ውጣ ውረድ ውስጥ አካሉ ያልጠናው ብላቴና ልዑል ከአባቱ ጋር አብሮ ብዙ ወጥቶ ወርዷል፡፡

የልዑሉ አባት አባ ታጠቅ ልጃቸው በእድሜ እና በአካል ሲጎለምስ እንግሊዝን ጎብኝቶ እና ሥልጣኔን አሽትቶ እንዲመለስ ምኞታቸው ነበር፡፡ የልዑሉ እንግሊዝን ማየት እውን ቢሆንም የሄደበት መንገድ ግን አባቱ እንደሚሹት እና እርሱ በፈለገው መንገድ የተገኘ አልነበረም፡፡ ልዑሉ እንግሊዝን የጎበኛት አባት እና እናቱን በሞት ተነጥቆ እና ምርኮኛ እና ግዞተኛ ልዑል ሆኖ ነበር፡፡

አባቱን በጦርነት ምክንያት፤ እናቱን ደግሞ በስደት ወቅት በሞት ያጣው ልዑል “ሰማይ ተደፋበትና” ሃዘኑ በረታ፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ የስዊዝ ካናልን እንደተሻገሩ የእናቱ ጠባቂ ገብረመድህን እና መምሕሩ አለቃ ዛራት መጥፋታቸው ልዑሉን ባይተዋር አደረገው፡፡ በወቅቱ ለልዑሉ ያሉት ብቸኛ ሰው ካፒቴን ስፒዲ ነበሩ፡፡ ከሰባት ዓመታት ያልበለጠ እድሜ ያለው ልዑል የመከራ ቀንበር ተደራርቦ ወርዶ ሃዘን ቢያጎብጠውም ከካፒቴን ስፒዲ ጋር የነበረው ፍቅር ግን ልዩ እንደነበር በርካታ ጸሐፍት ይናገራሉ፡፡

ከሦስት ወራት የባሕር ላይ ጉዞ በኋላ በሀገረ እንግሊዝ የደረሰውን ልዑል በመጎብኘት ቀዳሚዋ ሰው ንግሥት ቪክቶሪያ ነበሩ፡፡ ንገሥቷ በጉብኝታቸውም ወቅት “ምስኪኑ ልጅ ፍርሐቱ አለቀቀውም፡፡ የመቅደላውን እልቂት እና የአባቱን ሞት ስላየ ኹነቱ በአዕምሮው ይመጣበታል” ሲሉ ማናገራቸው ተከትቧል፡፡ ስደት ያልተመቸው፣ ሃዘን ያሰቃየው እና ናፍቆት ያናወዘው ልዑል የእንግሊዝ ቆይታውም ውጣ ውረድ የበዛበት እና ውዝግብ የበዛበት እንደነበር ይነገራል፡፡
ከካፒቴን ስፒዲ ጋር የጠበቀ ፍቅር እና ቁርኝት የነበረው ልዑል ቤተ መንግሥት ሲገባ እንኳን እንዲለየው አይፈልግም፡፡ አብረው ይመገባሉ በአንድ ላይም ይተኛሉ፡፡ ከጊዜ በኋላ ልዑሉን ማሳደግ የከበደው ካፒቴን በኑሮ ትደጉመው ዘንድ ወይዘሮ ኮታንን እስከማግባት ደርሷል፡፡ ከጥቂት ጊዜ የእንግሊዝ ሀገር ቆይታ በኋላ ካፒቴን ስፒዲ ወደ ሕንድ አዛዥ ሆኖ በመሾሙ ልዑሉን እና ወይዘሮ ኮታን ይዞ ወደ ሕንድ አቀና፡፡

ከሀገረ ሕንድ ውስን ጊዜ ቆይታ በኋላ ቻንስለር ሮበርት ሉዊ ልዑሉን አስመልቶ ያቀረበው ምክረ ሃሳብ የዓለማየሁን የሕይዎት መስመር እስከ ወዲያኛው አበላሸበት፡፡ ልዑል አለማየሁ ከካፒቴን ስፒዲ ተነጥሎ በቤተ መንግሥት አካባቢ ተቀምጦ ወታደራዊ ትምሕርቱን እንዲከታተል ተወሰነ፡፡ ይኽ ውሳኔ ግን ለዓለማየሁም ኾነ ለስፒዲ ከባድ ነበር፡፡ ስፒዲ እና ኮታ ዓለማየሁን አሳልፎ ላለመስጠት ጥረት ቢያደርጉም ውጤት ግን አላመጣላቸውም ነበርና ስፒዲ ልዑሉን ለማድረስ ወደ እንግሊዝ ሄደ፡፡
የልዑል ዓለማየሁን እና የካፒቴን ስፒዲን ፍቅር ያውቁ የነበሩት ንግሥት ቪክቶሪያ ኹለቱን በአንድ ጊዜ መነጣጠል አልፈለጉም፡፡ ንግሥቷ ዓለማየሁ ከቀጣዩ ጊዜ አስተማሪው ቄስ ብሌክ ጋር በበቂ እስኪላመድ ድረስ ስፒዲ አብሮት እንዲቆይ አደረጉ፡፡ ልዑል ዓለማየሁ በእንግሊዝ በተማረባቸው ትምሕርት ቤቶች የነበሩ መምሕራን ሁሉ መልካም ወዳጆቹ ቢኾኑም ካፒቴን ስፒዲን እና ወይዘሮ ኮታን የሚተኩ ግን አልነበሩም፡፡ እንዲያውም ልዑሉ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ መመለስን አብዝቶ ይፈልግ እንደነበር ይነገራል፡፡

ሊድስ አካባቢ ይኖር የነበረው ልዑል በመጨረሻም በምግብ መመረዝ ትንሽ ቀናትን በሕመም አሳልፎ በተወለደ በ19 ዓመቱ ኅዳር 5/1972 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ በንግሥት ቪክቶሪያ ፈቃድ በዊንድሶር ቅዱስ ጊዮርጊስ የነገሥታት መካነ መቃብር ሥርዓተ ቀብሩ ተፈፀመ፡፡ በመቃብሩም ላይም “የሃበሻው ልዑል ዓለማየሁ” የሚል መልዕክት ተቀመጠበት፡፡ መልካም ልደት ብለናል፡፡
ምንጭ፡- ዐፄ ቴዎድሮስ እና ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ፡ ታደለ ብጡል ክብረት መጽሐፍ

በታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየኢትዮጵያን ሕዝብ ለመጉዳት የተዘጋጁት ‘ኤች አር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ የዲያስፖራው ሁለገብ ጥረት ያስፈልጋል።
Next articleበኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንዲሁም የጤና ሥርዐት ለመዘርጋት ካናዳ እገዛ እንደምታደርግ ገለጸች።