የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመጉዳት የተዘጋጁት ‘ኤች አር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ የዲያስፖራው ሁለገብ ጥረት ያስፈልጋል።

153

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ለመጉዳት እንዲሁም ከዓለም የፋይናንስ ስርዓት ለማስወጣት የተዘጋጁት ‘ኤች አር 6600’ እና ‘ኤስ 3199′ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ ዳያስፖራው ሁለገብ ጥረት እንዲያደርግ ተጠየቀ።

በቨርጂኒያ ግዛት የሚገኘው የ’ፑሽ ስታርት’ ሚዲያ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ቤቲ ተከስተ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራት ቆይታ እንዳለችው ረቂቅ ሕጎቹ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የምታገኛቸውን የልማትና የደህንነት ድጋፎች የሚያስቆሙ ናቸው።

በተለይም የልማት ድጋፎች መቆም በተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ በሆነው ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ትናገራለች።

አሜሪካ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን በማስተባበር ለኢትዮጵያ እርዳታና ድጋፍ እንዳያደርጉ ተጽእኖ የሚያሳድር መሆኑንም ገልፃለች።

በረቂቅ ሕጉ ላይ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ መሳሪያና የመሳሪያ መለዋወጫዎችን እንዳትገዛ ጭምር የሚከለክሉና ከዓለም የፋይናንስ ስርዓት ውጪ የማድረግ አላማ ያላቸው መሆናቸውንም ጋዜጠኛዋ ተናግራለች።

ከሌሎች ሀገራት መሳሪያ ከገዛች ደግሞ አሜሪካ በሻጭ ሀገራት ላይ ማዕቀብ እንድትጥል ድንጋጌ የሚያስቀምጥ ስለመሆኑ ጠቁማ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ጭምር ጫና የሚያሳድር ነው ብላለች።

የረቂቅ ሕጎቹን ይዘት መንግሥትን ከመደገፍና ከመቃወም ጋር የሚያያዝ ሳይሆን አጠቃላይ በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ችግር የሚጋርጥና ሕዝብን የሚጎዳ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ነው ያለችው።

በመሆኑም ረቂቅ ሕጎቹ ከጸደቁ ኢትዮጵያን ከዓለም የፋይናንስ ስርዓት የሚያስወጡ እና በሉዓላዊነቷ ላይ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ ሁሉም በጋራ ተቃውሞውን ሊያሰማ ይገባል ብላለች።

በተለይም የዳያስፖራው ማሕበረሰብ የኢትዮጵያን ትክክለኛ እውነታ ለዓለም በማስረዳትና ረቂቅ ሕጎቹን በፅኑ መቃወሙን አጠናክሮ መቀጠል አለበት በማለት መልዕክቷን አስተላልፋለች።

ረቂቅ ሕጎቹ በአሜሪካ ምክር ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን ባላቸው የ’ዴሞክራት’ና የ’ሪፐብሊካ’ን ፓርቲ አባላት ድጋፍ ማግኘታቸውን አንስታለች።

ከዚህም አልፎ ሕጎቹ በአግባቢ ድርጅቶች ግፊት ወደ ሕግ አውጪው ምክር ቤት እንዲደርሱ መድረጉን ጋዜጠኛ ቤቲ አስታውሳለች።

በተለይም ‘ኤች.አር 6600’ ረቂቅ ሕግ በኮንግረሱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ድጋፍ በማግኘቱ በኮንግረሱ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ መታየት ቢኖርበትም እሱን አልፎ በቀጥታ ለኮንግረሱ መድረሱን አክላለች።

በአሁኑ ሰዓት ሁለቱን ረቂቅ ሕጎች ኮንግረሱና ሴኔቱ እንዲያያቸው በኮሚቴዎች መመራታቸውንም ጠቅሳለች።

ይህም ቢሆን በዚህ ጊዜ ሕጎቹ በቀጥታ ድምጽ ሊሰጥባቸው እንደማይችልና ቀሪ የሕግ ሂደቶች እንዳሉ ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል ብላለች።

በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎችና የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ረቂቅ ሕጎቹ ድምፅ እንዳይሰጥባቸው ተሰሚነት ያላቸውን የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች የማሳመን ሥራ እየሠሩ መሆኑንም ጠቁማለች።

በተለይ የአሜሪካ ኮንግረስ አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲን በስልክ በማነጋገርና ደብዳቤ በመጻፍ በእጇ ላይ የሚገኘው የኤች.አር 6600 ለኮንግረስ በአጀንዳነት እንዳታቀርበው ጥረት እየተደረገ ነው ብላለች።

የአሜሪካ የሕግ አስፈጻሚው አካል ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ግንኙነት ማሻሻል እንደሚፈልግ እየገለጸ ባለበት ወቅት ረቂቅ ሕጎቹ መውጣታቸው ግራ የሚያገባ መሆኑንም ጋዜጠኛ ቤቲ ተናግራለች።

በመሆኑም ዲያስፖራው ግራ ሳይጋባ በአንድነት ሕጎቹ ሊጸድቁ የሚችሉበትን እድሎች ለመዝጋት ሁለገብ ትግል እንዲያደርግ ጠይቃለች።

ኤች.አር 6600 ረቂቅ ሕግ የአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወያይቶበት ለኮንግረሱ መምራቱ የሚታወስ ነው።

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleቺርቤዋ ሜጋቢት 30-7-2014 ም.አ
Next articleግዞተኛው ልዑል!