
ዘመናዊ የግብር አሰባሰብ አሠራር መጀመሩን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።
የደረጃ ሀ እና ለ ግብር ከፋዮች በማሽን የታገዘ የግብር ክፍያ እንዲጀምሩ ማድረጉን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታውቋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የግብር አሰባሰቡ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ቢኖረውም እቅዱን ግን ማሳካት እንዳልተቻለ ነው መምሪያው የገለጸው።
በዞኑ በ2012 በጀት ዓመት ከመደበኛ እና ከከተማ አገልግሎት ገቢ 407 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው። በዕቅዱ መሠረት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 25 በመቶ ግብር መሰብሰብ ነበረበት። ይሁን እንጂ እስካሁን የተሰበሰበው 87 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ገቢዎች መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደሴ ጥሩነህ ለአብመድ እንደገለፁት ኀብረተሰቡ ስለግብር ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑ እንዲሁም በዞኑ በተለይም በአይከል፣ በሁለቱም የጭልጋ ወረዳዎች አና አጎራባች ቀበሌዎች በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ባለሙያዎች ተረጋግተው ግብር መሰብሰብ አለመቻላቸው ለአፈፃፀሙ ማነስ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
ምንም እንኳን በየጊዜው ለግብር ከፋዮች የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሀ ግብሮች ቢዘጋጁም ውጤታማነቱ በሚፈለገው ልክ አይደለም ያሉት አቶ ደሴ ይህን ለማሻሻልም በዞኑ ዘመናዊ የግብር አከፋፈል ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በዚህም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከሚገኙ 16 ወረዳዎች መካከል በ14ቱ የደረጃ ሀ እና ለ ግብር ከፋዮች በማሽን የታገዘ የግብር ክፍያ እንዲጀምሩ ተደርጓል። ይሁን እንጂ ዘመናዊ የግብር አስተዳድር ስርዓቱ በተለያዩ ምክንያቶች ውጤታማ እየሆነ አይደለም ብለዋል። ከምክንያቶች መካከል የሰራተኞች የክህሎት አናሳ መሆን እና ከቴክኖሎጂው ጋር አለመላመድ እንዲሁም የመብራት እና የኔትወርክ መቆራረጥ ተጠቅሰዋል። እነዚህን ችግሮች በሂደት አንደሚፈቱም ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል።
በ2011 በጀት ዓመት ምንም እንኳን በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች የሰላም እጦት የነበረ ቢሆንም በዓመቱ መጨረሻ አካባቢ በትኩረት በመሰራቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው በላይ ግብር ተሰብስቧል። ማሳያውም 402 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 416 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉ ነው። ዘንድሮም በተጠቀሱት እና በሌሎችም አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታውን በማሻሻልና ውስንነቶችን በማስተካከል እቅዱን ለማሳካት እንደሚሰሩ አቶ ደሴ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ