የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ተገልጋዮችን እርካታ በመዳሰስ ያሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ለማሻሻል የሚረዱ የመፍትሄ ሀሳቦችን የሚጠቁም ጥናት ይፋ ተደረገ።

277

ባሕር ዳር : ሚያዝያ 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዩኤስ ኤድ ፍትሕ ተግባራት በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥና የተገልጋዮች እርካታ ጥናት ግኝትን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር ውይይት እያደረገ ነው፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አብዬ ካሳሁን የዩኤስ ኤድ ፍትሕ ተግባራት በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ለኅብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት አሻሽለው ዘመናዊ አገልግሎት እንዲሰጡ እገዛ አድርጓል ብለዋል።
የክልሉ ፍርድ ቤቶች በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ያላቸው የተገልጋይ እርካታ ምን ይመስላል? የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ በጥናት ላይ ተመስርቶ ምላሽ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ነው ያነሱት።
በዩኤስ ኤድ ፈንድ አድራጊነት የተቀረፀ የፍትሕ ተግባራት በኢትዮጲያ ፕሮጀክትና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በክልሉ የፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ሲያደርጉ እንደቆዩ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
አቶ አብዬ እንዳሉት የዳሰሳ ጥናቱ ዋናው ትኩረት የክልሉ ፍርድ ቤቶች ተገልጋዮች እርካታን በመዳሰስ ያሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ለማሻሻል የሚረዱ የመፍትሄ ሀሳቦችን መጠቆም ነው፡፡
ጥናቱ የፍርድ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነት፣ ተደራሽነት፣ ቅልጥፍና፣ ግልጸኝነት፣ መልካም ሥነ-ምግባር፣ የቅሬታ አፈታት መሻሻል ማሳየት እና አለማሳየታቸውን የሚያመላክት መኾኑን ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል።
የጥናቱን ግኝት በግብዓትነት በመጠቀም የእቅዳቸው አካል በማድረግ የበለጠ ለመሥራት እንደሚያግዛቸውም አቶ አብዬ ተናግረዋል።
የፍትሕ ተግባራት በኢትዮጵያ ኀላፊ ዴቪድ ዲ ጃይልስ በኢትዮጵያ ለፍትሕ አካላት የቴክኒክ ድጋፍ ሲያደርግ እንደቆየ ተናግረዋል። የፍትሕ ተግባራት በኢትዮጵያ ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። የፍትሕ ተግባራት በኢትዮጵያ በክልሉ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ጥናትና ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል። የተካሄደው ጥናት ለፍርድ ቤቶች የተሻለ አገልግሎት አሰጣጥ ግብዓት እንደሚኾናቸውም ገልጸዋል።
ጥናቱን ያቀረቡት በጎንደር ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህርና የጥናት ቡድኑ አስተባባሪ በለጠ አዲስ የተካሄደው ጥናት የፍርድ ቤቶች ቅልጥፍና፣ ፍትሐዊነት እና ግልጸኝነት ላይ ተመስርቶ የተካሄደ መኾኑን ጠቁመዋል።
በተካሄደው ጥናት መሰረት ፍርድ ቤቶች የገለልተኝነት ችግር፣ የእውቀት ማነስ፣ ሠፊ የማስቻያ ክፍሎች አለመኖር፣ ዳኞችና ድጋፍ ሰጪዎች በሚጠበቅባቸው ያክል መልካም ሥነ ምግባር አለመኖራቸው፣ አሠራራቸው በቴክኖሎጂ የተደገፈ አለመኾኑ እና የዳኞች ቁጥር ማነስ በጥናቱ የተገኘ መኾኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጣቸው በመቶኛ ሲሰላ 65 በመቶ መኾኑን ያስረዱት አስተባባሪው ፍርድ ቤቶቹ የበለጠ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ማዘመንና ማሻሻል እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየግጭት ነጋዴዎች
Next article“ዓለም አቀፍ ተቋማትና የረድኤት ድርጅቶች በአፋርና አማራ ክልል ያለውን ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ዘንግተውታል” አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ አን ጋሪሰን