
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ 99 ነጥብ 3 በመቶ የየብስና ቀሪው ዜሮ ነጥብ 7 በመቶ ደግሞ በውኃ ክፍል የተዋቀረች ሀገር ናት። በ2010 ዓ.ም የወጣው ሀገራዊ የመስኖ ልማት ሥርዓት ፍኖተ ካርታ በጥናት እንዳስቀመጠው ከየብሱ የሀገሪቱ ክፍል ውስጥ ለመስኖ ልማት ሊውል የሚችል 42 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አለ። ይህንን ለማልማት ደግሞ እንደየአካባቢዎች ቆላማነትና ደጋማነት የሚለያይ ኾኖ አማካኝ ዓመታዊ የመስኖ ውኃ ፍላጎት እስከ 25ሺህ ሜትር ኪዩብ በሄክታር እንደሚደርስ ተጠቁሟል።
ሀገሪቱ ከከርሰ-ምድር እና ከገፀ-ምድር የምታገኘው አጠቃላይ የውኃ መጠን በመስኖ ሊለማ ከሚችለው የመሬት ሀብቷ ጋር ሲነጻጸር የውኃ ኃብቷ በእጅጉ ያነሰ ነው። በዓመት የምታገኘው ከ1ሺህ 7 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የሚደርስ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ቢሆንም ለጥቅም ከሚውለው ይልቅ የሀገሬውን ዜጋ የበይ ተመልካች እያደረገ ገደብ በሌላቸው ወንዞች ጋልቦ እየወረደ ለጎረቤት ሀገራት ሲሳይ የሚኾነው ይበልጣል።
የፌዴራል የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማእከል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ የሠራው ጥናት እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ካላት የውኃ ሀብት ውስጥ ከ70 እስከ 75 በመቶ የሚኾነው ውኃ ያለምንም ጥቅም ድንበር እየጣሰ ቁልቁል የሚነጉድ የባዕድ ሀገራት እና መብራት ነው።
በርካታ ሀገራት በመስኖ ዘርፍ አዋጭ ቴክኖሎጅዎችን እየተገበሩ ባለጸጋ ኾነዋል። ሰፋፊ መሬቶችን እያለሙ ከዜጎቻቸው ፍጆታ አልፈው የገቢ ምንጭም አድርገውታል።
የኢትዮጵያ ገበሬ ግን የኑሮ መሠረቱ ባህላዊ እርሻ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ለዘመናት የቆየና ከዚህ ግባ የሚባል የቴክኖሎጅ ማሻሻያ ሳይጎበኘው በሻው የሚረግጥ ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ በተለይም ከውጭ ሲገባ የነበረውን የስንዴ ምርት አስቀርቶ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ሰፊ የበጋ መስኖ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ግድቦችንና የከርሰ-ምድር ውኃን በመጠቀም በየክልሎች የሚገኝ ሰፋፊ የስንዴ ማሳም በመስኖ እየለማ ነው።
እንደ አማራ ክልል በተለይም በዚህ ዓመት በነበረው የጦርነት ዓውድ ምክንያት 2013/2014 የምርት ዘመን መደበኛው የዝናብ እርሻም ቢኾን በብዙ የክልሉ አካባቢወች ውጤታማ አልነበረም። ይህንን ለማካካስ ብሎም ዘላቂ የሕይወት ለውጥና ሀገራዊ እድገት ለማምጣት መሥኖ አማራጭ የሌለው ምርጫ ይኾናል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው የክልሉ አርሶ-አደር በመስኖ ኑሮውን መቀየር እንደሚችል ሰፊ ግንዛቤ አለው ብለዋል። ዳይሬክተሩ የአማራ ክልልን የመስኖ ፀጋ ሲገልጡ:-
✍🏻ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት ባለቤት ነው፡፡
✍🏻ሰፊ የከርሰ-ምድርና ገፀ-ምድር የውኃ ሀብት አለው፡፡
✍🏻ለመስኖ ተስማሚ አፈርና አየር ያለው ነው፡፡
✍🏻በመስኖ ራሡንና ሀገሩን ለማሳደግ የሚታትር አርሶ-አደር ያለበት ክልል መሆኑ ተስፉ ሰጭ ነው ይላሉ።
አቶ ይበልጣል በ2014 ዓ.ም የመኸር ወቅት 232 ሺህ 127 ሄክታር መሬት በመሥኖ እየለማ እንደሆነ ገልጸው ይህም መልማት ካለበት መሬት ውስጥ ከ20 በመቶ በታች እንደኾነ ተናግረዋል።
መስኖን በሙሉ አቅም ለማልማት አስቸጋሪ ሁኔታወችን ሲያብራሩም የመስኖ መሰረተ-ልማት አለመሟላት ትልቁ ማነቆ ነው ይላሉ። የውኃ ሀብት በየወንዙ ቢኖርም ወደማሳ ጠልፎ ለማስገባት የጀነሬተርና የቱቦ እንዲሁም የነዳጅ ዋጋው የአርሶ-አደሩን አቅም ይፈትናልም ይላሉ።
አርሶ-አደሩ ያመረተውን ምርት በቅርብና በቶሎ ሸጦ ለመጠቀም የገበያ ትስስርርና ለምርቱ እሴት የሚጨምሩ ፋብሪካወች አለመኖር ለመስኖ ማደግ እንቅፋቶች ናቸው ብለዋል። ወደ ግብርናው ክፍለ-ኢኮኖሚ በተለይም ድህረ-ምርት ማቀነባበር ላይ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሃብቶችን ወደ አካባቢው የመሳብ ሥራ እየተሠራ ሲኾን ይህም ለክልሉ የመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ትልቅ እድል ይፈጥራል” ብለዋል አቶ ይበልጣል።
“የአርሶ-አደሩን ሕይወት ለመቀየር መስኖ ላይ በትኩረት እየሠራን ነው” ነው ያሉት አቶ ይበልጣል፡፡ በክልሉ ውስጥ በግንባታ ላይ የሚገኙ እንደ ርብ፣ መገጭ እና አጅማ ጫጫ ያሉ ትልልቅ የመስኖ መሰረተ-ልማቶች በፍጥነት መጠናቀቅ አለባቸው እንደሚገባቸውም አስረድተዋል፡፡
በዘርፉ ላይ ስልጡን የኾነ እና በቴክኖሎጅ የላቀ ደጋፊ የሠው ኀይል ማሰማራት በመስኖ ልማት ሀገርን ለመለወጥ ወሳኝ ነገር ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት።
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የመስኖ ምሕንድስና መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሳይ አስረስ “እኛ የመስኖው ዘርፍ ምሁራን በተግባር ወደ አርሶ-አደሩ ወርደን በእውቀትና ቴክኖሎጅ ከመደገፍ ይልቅ በክፍል ውስጥ በጽንሰ-ሃሳብ ትምህርት ብቻ ተጠምደን ነው የምንውል” ብለዋል። ይህ ትክክል እንዳልኾነ የገለጹት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሳይ መስኖን የሚያዘምኑ የፈጠራ ሥራዎችን መሥራትና ወደማሳ በመውረድ ተግባራዊ ማድረግ ከምሁራን ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በቦይ በማጥለቅለቅ የሚሠራው ውኃ አባካኝ አጠቃቀም መሻሻል እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡
የመስኖ ሥራን በመርጨትና “ጠብታ” በመባል የሚታወቀውን የማጠጣት ዘዴ መጠቀም አዋጩ መንገድ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት።
“የመስኖ ሥራ ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ ከፖለቲካ ወጥቶ በባለሙያ መመራት አለበት” የሚሉት ምሁሩ “ኢትዮጵያ የውኃ ማማ ናት” እየተባለ የሚነገረውን እውነት ሰምቶ ከማፍሰስ በዘለለ ማማውን ፈትሾ የመስኖ ሥራን ውጤታማ ለማድረግ ከድኅነት ጋር ተቆራርጦ መሥራት አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው ብለዋል። የመስኖ ልማት ሥራ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋወች እንዲሁም ድርቅን ተከትሎ ለሚመጣ የምግብ እጥረትም ሁነኛው ማምለጫም እንደኾነ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሳይ አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡-አሚናዳብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/