
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከሚያዝያ 7/2014 ዓ.ም ጀምሮ ከ2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት የልጅነት ልምሻ ክትባት ሊሰጥ መኾኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡
ለዘመቻው ስኬታማነት የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና እና ወላጆች ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ቢሮው ጥሪ አቅርቧል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት አማካሪ ባለሙያ ሙሉጌታ አድማሱ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) በሽታ ጎረቤት ሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን አንስተዋል፡፡ በአማራ ክልልም ምዕራብ ጎጃምና ሰሜን ወሎ ዞኖች እንዲሁም ኦሮሚያ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባለፈው ዓመት ተጠርጣሪዎች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በመኾኑም በክልሉ 12 ዞኖች ኹለተኛው ዙር የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ክትባት በዘመቻ መስጠት አስፈልጓል ነው ያሉት፡፡
በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ምክንያት የመጀመሪያው ዙር ክትባት በደሴ ከተማ አሥተዳደር፣ በደቡብ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች እና በዋግኽራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባለመሰጠቱ በኹለተኛው ዙርም እንደማይሰጥ ነው ባለሙያው የነገሩን፡፡
በእነዚህ ዞኖች የወደሙ የክትባት ማስቀመጫ ማቀዝቀዣዎችን ወደ ነበሩበት የመመለስ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ባለሙያው በሀገር አቀፍ ደረጃ ፕሮግራሙ እንደወጣ ራሱን አስችሎ አንደኛ እና ኹለተኛ ዙር ክትባት ይሰጣል ብለዋል፡፡
አቶ ሙሉጌታ እንደነገሩን:–
•የክትባት ማስቀመጫ ማቀዝቀዣዎችን ከቦታ ቦታ በማዘዋወር ክትባቱ ይሰጣል፡፡
•316 ማቀዝቀዣዎችን የጥገና ሥራ ተሠርቷል፡፡
•ከዚኽ ውስጥ ደግሞ 75 ከመቶው በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች ናቸው፡፡
• አስቸኳይ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ 350 የሚኾኑ ማቀዝቀዣዎችንም የጤና ሚኒስቴር የተከላ ሥራ ሠርቷል፡፡
• ክትባቱ ከሚያዝያ 7/2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ቤት ለቤት በዘመቻ ይሰጣል፡፡
• በዘመቻው ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ይከተባሉ፡፡
• ሕፃናት በሰውነታቸው በሽታውን የመከላከል አቅም እንዲፈጥሩ ሙሉ ክትባቱን (አራት በመደበኛ፣ አራት ደግሞ በዘመቻ ተጨማሪ ክትባት) መሥጠት ያስፈልጋል፡፡
በመኾኑም ከአምስት ዓመት በታች የሚገኙ ሕጻናት መደበኛ ክትባት ቢከተቡም እንኳ በዘመቻ የሚሰጠውን ክትባት ማስከተብ እንደሚገባ አቶ ሙሉጌታ አሳስበዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት እና ሌሎች አጋር አካላት የተሳተፉበት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተሠርቷል፤ እየተሠራም እንደሚገኝ አቶ ሙሉጌታ አንስተዋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር ዘመቻም ከታቀደው 98 በመቶ ክትባት መሰጠቱን ነው ባለሙያው የነገሩን፡፡
ባለሙያው እንዳሉት ፖሊዮ ከፈንጣጣ ቀጥሎ በዓለም ላይ እየጠፋ የሚገኝ በሽታ እንደኾነ ነው፤ ይኹን እንጅ በሽታው በቀላሉ ተላላፊ እንደመኾኑ አንድ የፖሊዮ ምልክትም ከተገኘ ‹‹ወረርሽኝ›› ተብሎ እንደሚገለጽም ባለሙያው አንስተዋለ፡፡
ክትባቱ በኢትዮጵያ መሰጠት ከጀመረ 42 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/