
የቡና ገለፈትን ከበካይነት ወደ ማዳበሪያነት የሚቀይር የምርምር ውጤት ለቡና አብቃዮች ተዋወቀ።
የቡና ገለፈትን በስነ ህይወታዊ ዘዴ ወደ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያነት የሚቀይረው የምርምር ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ተመርቋል።
ምርምሩ የተሰራው በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ነው። የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ደግሞ ለምርምር ሥራው ድጋፍ አድርጓል። ሥራውም በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ሦስት ቀበሌዎች ላይ የተካሄደ ነው።
የምርምሩ ባለቤት ገዛኸኝ ደግፌ (ዶክተር) እንደገለጹት የምርምር ውጤቱ የአካባቢው ቡና አምራቾች ለማስወገድ ችግር የሆነባቸውን የቡና ገለፈት በትሎች በማስበላት (በስነ ህይወታዊ ዘዴ) ወደ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያነት መቀየር ያስቻለ ነው።
የቡና ገለፈት ቡና ለሚያመርቱ አርሶ አደሮች ለማስወግድ ችግር ሆኖባቸው የቆየ ከመሆኑም ባሻገር መርዛማት ስላለው አካበቢውን ሲበክል የቆየ እንደነበረም ነው ዶክተር ገዛኸኝ የተናገሩት።
ገለፈቱ ውሃን በመመረዝ በእንስሳት ላይም ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱንና ምርምሩ ይህንን ችግር እንደፈታ ተመራማሪው አስረድተዋል። ከዚህ ባለፈም በተፈጥሮ ማዳበሪያነት እያገለገለ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የምርምሩን መተግበሪያ ለሲዳማ ዞን ማስረከባቸውም ታውቋል።