
መጋቢት 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምሥራቁ ክፍል በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው የልማት ሥፍራዎች የመስኖ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድሙ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት አርሶ አደሩ በደረሰበት ወረራና ውድመት ሳይበገር በአንደኛው ዙር መስኖ ልማት ሥራ መረባረቡን አስረድተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደነገሩን
👉ክልሉ በአንደኛ ዙር መስኖ 239 ሺህ 383 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እቅድ ይዞ ተንቀሳቅሷል፡፡
👉በአንደኛው ዙር መስኖ 232 ሽህ 127 ሄክታር መሬት በማልማት አርሶ አደሩ አይበገሬነቱን አሳይቷል፡፡
👉ክልሉ በሁለተኛው ዙር መስኖም 100 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
👉እስካሁንም ባለው ሥራ 42 ሺህ 818 ሄክታር መሬት በሰብል እንዲሸፈን ተደርጓል፡፡
👉በሥራው 347 ሺህ 588 አርሶ አደሮችን በልማቱ ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
👉እስካሁን ባለው ሥራ 150 ሺህ 988 አርሶ አደር ማሳተፍ ተችሏል፡፡
አቶ ይበልጣል እቅዱን ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ስለመኾኑ ነግረውናል፡፡
ምሥራቅ አማራ በወረራ ቢቆይም ካለው የመስኖ ልማት አቅም አኳያ ሥራውን ለመፈጸም በከፍተኛ ወኔ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የማዳበሪያ እጥረት ያለ ቢኾንም ያለውን ማዳበሪያ ለመስኖ ሥራ እንዲውል በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደኾነ አቶ ይበልጣል አስረድተዋል። አሁንም ማዳበሪያ እየገባ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት የደረሰበትን የቆቦ ጊራና ሸለቆ የመስኖ ልማት ፕሮጀክትንም ያለበትን የኤሌክትሪክ ችግር ቀርፎ በሁለተኛው ዙር መስኖ ሥራ ለመጠቀም ክልሉ እየሠራ እንደኾነ ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡
የቆቦ ጊራና ሸለቆ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ሞላ መለሰ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የክልሉ የመስኖ ልማት የጀርባ አጥንት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ
👉ፕሮጀክቱ 2 ሺህ 880 ሄክታር በማልማት ክልሉን በመሥኖ ልማቱ ሲደግፍ ቆይቷል፡፡
👉በሥሩ ከ43 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግም ነው፡፡
👉በዓመት 3 ጊዜ ያለማም ነበር፡፡
👉ሰሜን ወሎ፣ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሽዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞኖችን አካቶ እንዲያለማ የታሰበ ፕሮጀክት ነው፡፡
የቆቦ ጊራና ሸለቆ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በተለያዩ የፕሮጀክቱ ቦታዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ተናግረዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ የቆቦ ጊራና ሸለቆ የመስኖ ፕሮጀክት በዋናነት ያለበትን የኀይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ስለመኾኑ አረጋግጠዋል፡፡
አቶ ሞላ እንደነገሩን የኀይል አቅርቦቱን ለመፍታት ሥራ መጀመሩን አረጋግጠዋል፡፡ የኢንስታሌሽን እና የጥገና ሥራዎች መጠናቀቁንም ያላቸውን መረጃ መሠረት አድርገው ነው አቶ ሞላ ያስረዱት፡፡
የኀይል አቅርቦቱ እስኪጀምር አርሶ አደሮች የማሳ ዝግጅት እንዲጀምሩ እና የፍራፍሬ ልማት በሚያለሙ አካባቢዎች በጀነሬተር እና በሶላር የኀይል አማራጮች የሚሠራበት መንገድ መፈጠሩን ሥራ አስኪያጁ አስገንዝበዋል፡፡
ለዚህም የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የጀኔሬተር እና የሶላር አማራጭ ኀይል እገዛ ማድረጉን ነው የተናገሩት፡፡
ሥራ አስኪያጁ አሁን ባለው ርብርብ የቆቦ ጊራና ሸለቆ መሥኖ ልማት ያለበት ችግር ተቀርፎ ወደ ሁለተኛ ዙር መስኖ ልማት ሥራ ሊገባ የሚችልበት እድል እንዳለ ነው ያስገነዘቡት፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
