የሕዝቡን የቀደመ አንድነትና ትስስር ለማስቀጠል አልሞ የሚሠራ አሥተዳደራዊ አማካሪ ምክር ቤት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተቋቋመ።

167

መጋቢት 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝቡን አንድነትና ትስስር ለማስቀጠል አልሞ የሚሠራ 19 አባላት ያሉት አማካሪ ምክር ቤት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዛሬ ተቋቁሟል።
ይህ ምክር ቤት በዞኑ ባሉ 7 ወረዳዎች ማለትም ሁለቱ ጭልጋ ወረዳዎችን ጨምሮ፣ ላይ አርማጭሆ ወረዳ እንዲሁም ችግር ተፈጥሮባቸው በነበሩ አካባቢዎች ደግሞ ወገራ፣ ጎንደር ዙሪያ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ደምቢያ ወረዳዎች ላይ ዘላቂ የኾነ ሰላምንና ልማትን ለማምጣት አልሞ የሚሠራ እንደኾነ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ገልጿል።
በአሥተዳደራዊ አማካሪ ምክር ቤት ማቋቋሚያ መርኃግብሩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ወርቁ ኃይለማርያም እንደተናገሩት የአማራና ቅማንት ወንድማማች ሕዝብ በአንድነት የተጋመደና መቸውንም የማይነጣጠል ሕዝብ ነው ብለዋል።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን አካባቢውን ለማተራመስና የስጋት ቀጣና እንዲኾን የተጠቀመውን አጀንዳ ለማስቀረትና መቸውንም የማይቆራረጠውን አንድ ሕዝብ ወደ ቀደመ ክብሩና የወንድማማችነት እሴቱ እንዲመለስ ለማድረግ ምክር ቤቱ የበኩሉን እንደሚሠራ ተናግረዋል።
መንግሥት የሕዝቡን ግንኙነት ከዚህ በፊት ከነበረው የበለጠ ለማጠናከር በቀዳሚነት እንደሚሠራና የተፈናቀሉትንም ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ እንደሚያደርግም ተገልጿል።
በተለያየ ምክንያት ወደ ጫካ የገባ ማንኛውም አካል እጁን ለጸጥታ አካላት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
በዞኑ ከአማራና ቅማንት ሕዝብ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ችግሩ ተፈጥሮባቸው በነበሩ አካባቢዎች ኹሉ በመንግሥት ሠራተኞችና አመራሮች እንዲሁም በኹሉም ቀበሌዎች ደረጃ ሕዝባዊ ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ታውቋል።
ይህ አማካሪ ምክር ቤት በተመሳሳይ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ እንደሚቋቋምም ተገልጿል።
ዛሬ ከተለያዩ ወረዳዎች በተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተቋቋመው 19 አባላት ያሉት ይህ አሥተዳደራዊ አማካሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ እና ጸሓፊውን ሰይሟል።
አማካሪ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አድርጎ የሰየማቸው አቶ ድርጅት አድማስ የሕዝቡን ሰላምና አንድነት በጽኑ መሠረት ላይ እንዲቆም ለማድረግ እንዲሁም ለጋራ እድገትና ልማት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የጎንደርን ቀጣናዊ ትስስር ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግና ወደ ልማት ለማስገባት በአጭርና መካከለኛ ጊዜያት ውስጥ ይህ አማካሪ ምክር ቤት ውጤታማ ተግባርን እንደሚያከናውን አቶ ድርጅት አስረድተዋል።
የአማካሪ ምክር ቤቱ አባላት ከዞኑ አሥተዳደር ጋር በመኾን ሥራቸውን በሚገባ አውቀው የሕዝቡን የቆየ አንድነትና ትስስር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቀጠል ከምንግዜውም በላይ እንዲሠሩና ሕዝቡም ቀና ትብብር እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ዘገባው የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ነው።
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አማራ ሕዝብ ላይ በአሸባሪው ህወሃት የተፈጸመውን ግፍ ዓለም ሊያውቀው ይገባል” በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አጥኝ ቡድን
Next articleበአዲስ አበባ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሴቶችና ሕጻናት የአልሚ ምግብ ተደራሽ ለማድረግ ሥምምነት ላይ ተደረሰ።