“23 ፕሮጀክቶች መሬታቸውን በመንጠቅ ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስና ለሌሎች አልሚዎች እንዲተላለፍ ተደርጓል” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር

190

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በከተማ አሥተዳደሩ የሚስተዋሉ የማኅበረሰብ ችግሮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ ያልገቡ 72 ፕሮጀክቶች በወሰዱት ውል መሰረት ባለመሥራታቸው የተሰጣቸው መሬት መነጠቁን ገልጸዋል። ይኹን እንጂ ፕሮጀክቶቹ ቅሬታ ካስገቡ በኋላ የገጠማቸው ችግር ተለይቶ የእያንዳንዳቸው ሰነድ ከተፈተሸ በኋላ 23 ፕሮጀክቶች የወሰዱተን መሬት በመንጠቅ ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ መደረጉን ጠቁመዋል። ቀሪዎቹ ፕሮጀክቶች ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ድረስ የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት አሟልተው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አስረድተዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የኮንቴነር አጠቃቀምን በተመለከተም መግለጫ ሰጥተዋል። ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ኮንቴነር ሲሰጥ መቆየቱን ዶክተር ድረስ አስረድተዋል። በሥራ እድል መፍጠሪያ መሰረት ኮንቴነር ለ5 ዓመታት የሚያገለግል ቢኾንም በተያዘው ጊዜ ያለማሸጋገር ችግር መኖሩን ተናግረዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ 2ሺህ ኮንቴይነሮች ከመመሪያ እና ከሕግ ውጭ የተላለፉ መኾኑንም አንስተዋል። እነዚህን ኮንቴይነሮች ሕጋዊ መልክ እንዲይዙ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይ አምስት ዓመታት በከተማ አሥተዳደሩ በልማት ላይ የማይውል መሬትን በመለየት ለሥራ እድል ፈጠራ እንዲውል እንደሚደረግ የጠቆሙት ዶክተር ድረስ ከአምስት ዓመታት በኋላ ደግሞ የሽግግር ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በየክፍለ ከተማው የተደራጀው የሥራ ፈላጊ ግብረኀይል ትክክለኛ የሥራ አጥ ዜጎችን የመለየት ተግባር ይፈጽማል ብለዋል። ኅብረተሰቡ ከኮንቴነር ጋር ተያይዞ አላስፈላጊ አሉቧልታዎችን መስማት እንደሌለበት ያሳሰቡት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ማንኛውም ተግባር በመመሪያና ሕጋዊ በኾነ መልኩ እንደሚሠራ አስገንዝበዋል። ሕግን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ኅብረተሰቡ ትብብር ማድረግ እንዳለበት ነው የተናገሩት። ማንኛውም ዜጋ በሕጋዊ መሰረት የሥራ እድል ይፈጠርለታል ብለዋል።
ሌላው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በመግለጫቸው ያተኮሩት የመኖሪያ ቤት ማኅበርን በተመለከተ ነው። ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ተደራጅተው የቆዩ ማኅበራት ቦታ ሳይሰጣቸው መቆየቱን ተናግረዋል። በ2013 ዓ.ም ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት ቢደረግም ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ሊዘገይ እንደቻለ ዶክተር ድረስ ገልጸዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንዳሉት በዚህ ዓመት ሕጋዊ እውቅና ላገኙ የቤት ማኅበራት ሁሉ ቦታ ለመስጠት እየተሠራ ነው ብለዋል። ለተፈጻሚነቱ ባለሙያዎች በርብርብ እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። “380 የሚኾኑ መምህራን በየማኅበራቱ የተደራጁ መኾናቸው እና መምህራኑ የካሳ ክፍያ አለመፈጸማቸው ተጨማሪ ችግር ሆኗል” ብለዋል። በመኾኑም መምህራን በዝግ አካውንት የቆጠቡት 10 በመቶ ገንዘብ ተመልሶላቸው የሚጠበቅባቸውን ካሳ እንዲከፍሉ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በመግለጫቸው እንዳሉት ሪል ስቴት ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጨው መረጃ ትክክለኛ አይደለም። ከተማ አሥተዳደሩ የሪል ስቴት ልማት እቀበላለሁ ብሎ ማስታወቂያ አለማውጣቱን አረጋግጠዋል። ከተማ አስተዳደሩ መሬትን ከሦስተኛ ወገን ነፃ አድርጎ በሊዝ እና በጨረታ ለባለሀብቶች የሚያስተላልፍበት ሞዳሊቲ መኖሩንም አስረድተዋል።
ኅብረተሰቡ ወደ መንግሥት ተቋም መጥቶ መረጃዎችን ማግኘት ሲገባው በደላላ የሚጠለፍበት አካሄድ ሊቆም ይገባል ብለዋል። ኅብረተሰቡ ሕጋዊነቱን ትቶ የሕገ ወጥ ሰዎች ተባባሪና ተጎጂ መኾን እንደሌለበት ነው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ያሳሰቡት።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለማስተዋወቅ የሚያስችል የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል አቋቋመ።
Next articleየሃይማኖት አባቶች ትልቅ ተሰሚነት ስላላቸው የሃይመኖት መቻቻልና መልካም ሰብዕናን በትውልዱ ላይ ለማስረጽ በትኩረት እንዲሠሩ ተጠየቀ።